ከብድር ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ

  • መንግሥት ከ8.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል ተብለዋል

በቅርቡ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ብድር ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ደርቤ አስፋው ሁሪሳ፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ የብድር ክፍል ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ ኅዳር 12 ቀን 1992 ዓ.ም.፣ ሚያዝያ 12 ቀን 1992 ዓ.ም. እና ሚያዝያ 12 ቀን 1993 ዓ.ም. በተደረጉ ሦስት ውሎች ከተለቀቀ ብድር ጋር በተያያዘ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ቢሮ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ብድሩን የወሰደው ናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑን፣ የተፈቀደለትን 35 ሚሊዮን ብር ብድር የሚመጥንና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 27 ቀበሌ 01 ውስጥ በካርታ ቁጥር 0270 የሚታወቀውን ንብረት ዋስትና አስይዞ እንደነበር፣ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ተበዳሪው ማኅበር በውሉ መሠረት ግዴታውን ባለመወጣቱ አበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመያዣነት የተረከበውን ንብረት በጨረታ እንዲሸጥ ማድረጉንም ፖሊስ ገልጿል፡፡ በመያዣነት በተያዘው ግቢ ውስጥ ሌላ ንብረት ስለመኖሩ የባንኩ መሐንዲስ አስተያየት የሰጠ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው አቶ ደርቤ ግን አስተያየቱን ችላ በማለት ያልተገመተና በጨረታው ያልተካተተ ንብረት፣ ንብረቱን ለገዛው አካል እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መንግሥት ሊያገኝ የነበረውን 8,545,640 ብር ጉዳት እንዲደርስበት ማድረጋቸውንና በፈጸሙት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ቀሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስረድቶ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡

ተጠርጣሪው አቶ ደርቤ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በተገለጸው የሥራ ኃላፊነት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ይሠሩ ነበር፡፡ በ1992 ዓ.ም. ግን በባንኩ ውስጥ አልነበሩም፡፡ ያልተገመተና ያልተሸጠ ንብረት አስተላልፈዋል የተባሉት ለአቢሲኒያ ባንክ መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ተላለፈ የተባለው ንብረት የናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ ንብረቶቹ ቢገመቱ ኖሮ ንግድ ባንክ ሸጦ 8,454,640 ብር ያገኝ ነበር ተብሎ የቀረበባቸው ክስ እንዴት ከዓመታት በኋላ ሊነሳ እንደቻለም እንዳልገባቸው ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንትና የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ ካለባቸው ኃላፊነትና ለአገርም ካደረጉት ትልቅ አስተዋጽኦ አኳያ የፍርድ ሒደቱን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ግን ከመሥሪያ ቤቶች የሚሰበስባቸው ሰነዶች እንዳሉ ገልጾ፣ በዋስ ቢወጡ ሰነድ ሊያጠፋ እንደሚችሉ በማስረዳት ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም መርማሪው ቃል ለመቀበልና ሰነድ ለመመርመር ስድስት ቀናት እንደሚበቁት በማስታወቅ፣ ለግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠት አቶ ደርቤ ያነሱትን የዋስትና ጥያቄ አልፎታል፡፡

Reporter Amharic

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s