opinion/ ምልከታ

የአማራ መደራጀት ጉዳይ – አቻምየለህ ታምሩ

ከሰሞኑ የአማራው በአማራነት መደራጀት ጉዳይ እንደገና ተቀስቅሶ የውውይት አጀንዳ የሆነ ይመስላል። ገራሚው ነገር የአማራውን በአማራነት መደራጀት አጀንዳ እያደረጉ ያሉት ሰዎች በዘውግ ከተደራጁት ቡድኖች ጋር አብሮ ለመስራት ደፋ ቀና እያሉ ያሉ ግለሰቦች ጭምር መሆናቸው ነው። የአማራው በአማራነት መደራጀት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ሆኖም ግን የአማራውን በአማራነት መደራጀትና «የአማራ ብሔርተኛነት» የሚባለውን የሌለ ነገር መለየት ያስፈልጋል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የአማራ ብሔርተኝነት የሚባል ነገር የለም። የአማራ ብሔርተኛነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ያለበትና ሊኖር የሚገባው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ብቻ ነው። ብሔር የግዕዝ ቃል ነው። ትርጉሙም አገር ማለት ነው። ብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል ከህዝብ ጋር የሚያገናኝው ነገር የለም። ብሔር የሚገልጸው ምድሩን ነው። በእንግሊዝኛም ብሔር ማለት Nation ማለት ነው። United Nations የአገራት ህብረት ማለት ነው።

ያ ትውልድ ነገድን ብሔር ወይንም Nation የሚል ስያሜ ሰጥቶ ፖለቲካ ያካሄደው «ዳግማዊ ምኒልክ የተባለ የአማራ ንጉስ የተለያዩ አማራ ያልሆኑ «የአፍሪካ አገሮችን» ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር በመመሳጠር ወርሮ በቅኝ ግዛትነት ይዟል» የሚለውን የትውልዱን የትግል መነሻ ጽንሰ ኃሳባዊ መሰረት ለመስጠት ነበር። በያ ትልውድ ፍልስፍና አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ወዘተ ብሔሮች ወይንም Nations ስለሆኑ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የአገራት ህብረት ወይንም United Nations ናት ማለት ነው። በያ ትውልድ የፖለቲካ ትርጓሜ ኒዮርክ ባለው አለማቀፉ United Nations እና በUnited Nations [of Ethiopia] መካከል ልዩነት የለም።