የኢህአዴግ መንግስት ጨካኝ ወይስ ጨቋኝ?

በአደስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የተቃሄደው ሰላማዊ ሰልፍና በኢህአዴግ መንግስት የተወሰደው ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ

የዴሞክራሲያዊ መንግስት ተግባራዊ አንቅስቃሴ የሚመራው በእኩልነት መርህ ነው። የአምባገነን መንግስት ሥራና ተግባር የሚመራው ደግሞ በፍርሃት ነው። አምባገነኖች ሀገርና ሕዝብ የሚመሩት በፍርሃትና በማስፈራራት ነው። በመሆኑም አምባገነን መሪዎች ያለ ፍርሃት ሀገርና ሕዝብን ማስተዳደር አይችሉም። “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ ስለ መንግስት አፈጣጠርና ዓላማ የተወሰኑ ነጥቦችን እንመለክት።

Image result for Eprdf force

በተወሰነ አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች (ሕዝቦች) የራሳቸውን መንግስት የሚመሰርቱበት መሰረታዊ ምክንያት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው በሕግና ስርዓት እንዲመራ ለማድረግ፣ በዚህም የሁሉም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት የጋርዮሽ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል ነው። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ድርሻና ኃላፊነት የሁሉንም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማክበርና ማስከበር የሚያስችል አስተዳደራዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። ለዚህ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ አዋጆችን፥ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ የሁሉንም ዜጎች መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራና አሰራር መዘርጋት፣ የአፈፃፀም ሂደቱን መከታተልና ማሻሻል አለበት።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የአንድ መንግስት መሰረታዊ ዓላማ የሁሉም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። ስለዚህ፣ የመንግስት ስራና አሰራር በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመንግስት መሰረታዊ ዓላማ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል። ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተለየ አምባገነናዊ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም፣ የአምባገነናዊ መንግስት ከእኩልነት ይልቅ በፍርሃት የሚመራው ነው።

የአምባገነን መንግስት ስራና አሰራር የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን መብትና ነፃነት የሚያረጋግጥና የተሻለ ጥቅምና ተጠቃሚነት እንዲኖረው የሚያስችል ነው። ይሁን እንጂ፣ እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮ ከሌሎች ሰዎች እኩል የመሆን፥ በእኩል አይን የመታየት ፍላጎት አለው። ስለዚህ፣ የተወሰኑ ሰዎችን፥ ቡድኖችን ወይም ማህብረሰብን ከሌሎች የበለጠ ወይም ያነሰ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖለቲካዊ ስርዓት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ይቃረናል። ስለዚህ፣ ዜጎች የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ከተመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓት ጋር መሰረታዊ ቅራኔ አላቸው። በመሆኑም፣ በአምባገነናዊ መንግስት የምትመራ ሀገር ዜጎች በተለያየ ግዜና አጋጣሚ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ይወጣሉ።

ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ የሚቀሰቀሰው “ከሌሎች “እኩል” መብትና ነፃነታችን ይከበር፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር” በሚል እሳቤ ነው። በዚህ መሰረት፣ የአመፅና ተቃውሞ ዓላማ የእኩልነት ጥያቄ ነው። በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአመፅና ተቃውሞ ለሚነሳ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅምና አሰራር ይኖረዋል። የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ ስርዓት ግን የእኩልነት ጥያቄን ለመቀበልም ሆነ ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም አይኖረውም።

በመሰረቱ፣ በአመፅና ተቃውሞ አማካኝነት የሚነሳው የእኩልነት ጥያቄ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማስቀረት ዓላማ ያደረገ ነው። ነገር ግን፣ በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ በዚህ መልኩ የሚነሳ የእኩልነት ጥያቄን ማስቀረትም ሆነ ማስተናገድ አይቻልም። የእኩልነት ጥያቄ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞን ማስቀረት አይቻልም። በተመሣሣይ፣ የአምባገነናዊ መንግስት መሰረታዊ ዓላማ የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደመሆኑ የእኩልነት ጥያቄን ተቀብሎ ማስተናገድ አይችልም። ስለዚህ፣ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በሰው ልጅ እና የአምባገነናዊ መንግስት ተፈጥሯዊ ወይም መሰረታዊ ባህራያት መካከል የተፈጠረ ግጭት ማለት ነው።

በአመፅና ተቃውሞ አማካኝነት በሚፈጠረው ግጭት ከዜጎች እና ከአምባገነን መንግስት አንዱ ወገን ተፈጥሯዊ ባህሪውን ያጣል። ተፈጥሯዊ ባህሪውን ያጣ ማንኛውም ነገር ሕልውናው ያከትማል። ስለዚህ፣ በአመፅና ተቃውሞ ምክንያት ወይ ዜጎች የሕይወትና አካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ወይም አምባገነኑ መንግስት በግድ ተቀይሮ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ወይም ይወድቃል። በዚህ መሰረት፣ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች እና በአምባገነን መንግስት መካከል የሚፈጠረው ግጭት ሕልውናን በማረጋገጥ ወይም በማጣት ውጥረት ውስጥ የሚካሄድ ነው።

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ አምባገነን መንግስት ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በሰላማዊ ዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፡- የእኩልነት ጥያቄ ለአምባገነናዊ ስርዓት የሕልውና አደጋ እንደመሆኑ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞን በጣም ይፈራል። ሁለተኛ፡- ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ከፍተኛ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር በሌላ ግዜና ቦታ ተመሳሳይ አመፅና ተቃውሞ እንዳይቀሰቀስ ያደርጋል። በአጠቃላይ፣ የእኩልነት ጥያቄ በሚያነሱ የሕብረሰብ ክፍሎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ የሚወስደው በፍርሃትና ለማስፈራራት ነው። ለምሳሌ ባለፈው አመት በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍና በመንግስት የተወሰደው እርምጃ እንደማሳያ ሊጠቀስ ይችላል፦


ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ከፍጠኛ ጉዳት የሚደርሰው የኢህአዴግ መንግስት በራሱ ስለሚፈራና ሕዝብን መስፈራራት ስለሚሻ ነው። ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ መንግስታዊ ስርዓቱ የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት በዜጎች ላይ የጭካኔ እርምጃ የሚወስደው ጨቋኝ ስርዓት በመሆኑ ነው።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s