Advertisements

NUTI TOKKO” እኛ አንድ ነን “- አገራዊ እርቅ ቢደረግና ሁሉም ከቂም ፖለቲካ ነጻ ቢወጣስ?

“ኦሮሞና አማራ አንድ ነው/ እኛ አንድ ነን፤ Nuti Tokko” የሚለው መፈክር ያስደስታል። ይህንን ሃሳብ ማራመደ የጀመሩትም በጎ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል። በአገራቸው ወቅታዊ ሁኔት ከክርስ በላይ ለሚያስቡ፣ ለሚጸልዩ ደግ ዜና ነው። ግን ከድሮም አማራና ኦሮሞን ማባላት ለምን አስፈለገ ለሚለው አጥጋቢ መልስ አይሆንም? በመንግስትና በህዝብ መገናኛዎች፣ አቶ መለስን ጨምሮ ጭፍሮቻቸው ምን ሲሉ ኖሩ? ይህ እነሱ የዘሩት፣ በሁዋላም አማራን ” ጡት ቆራጭ” አድርገው ሃውልት በማስቆም አዲሱን ትውልድ በፈጠራ ታሪክ የጥላቻ መርዝ የጋቱት ዛሬ ይህን ሲሉ ያማል። በቅርቡ እንኳን ጌታቸው ረዳ ” እሳትና ጭድ እንዴት ተስማማ?” ብሎ ሲያላዝን ለሰሙ ዜጎች ጉዳዩ ይጎፈንናል።

ትናንት ለሃጫም አማራ፣ ሆዳም አማራእንዳላሉ፣ እነሱ እስከ አፍንጫቸው እንዳልታጠቁ ነፍጠኛ እያሉ ሲራገሙ፣ ይህ ህዝብ አስተዋሽ አጣ በሚል ለመደራጀት የተነሱትን የገደሉ፣ ያሰሩ፣ ማንነቱ ላይ በጀት በጅተው የተነሱ ዛሬ ፍቅር ሊሰብኩ ሲነሳ ይበልጥ ያበሳጫል። ድሮም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም አማራና ኦሮሞ አንድ ነው። የጥቂት ፖለቲከኞች ሃሳብ ካልሆነ በስተቀር ህዝብ ህዝብ ላይ ስለመነሳት አስቦ አይውቅም። እናም እኒህ ክፍሎች መድረኩ ላይ ሆነው ዛሬ አማራና ኦሮሞ…. የሚሰብኩ ከሆነ ከግድያና እስር በላይ ይቀፋል።

ዛሬም አምራና ኦሮሞ፣ እንዲሁም ሌሎች በሄሮች ጋብቻ እየፈጸሙ፣ እየወለዱ፣ በፍቅር እየኖሩ ነው። በዚህ እርስ በርስ የማባለት ስልት የተደረገው ሙከራ ዞሮ ወደ ራስ ሲመጣ፣ ይህ አብሮ ለዘመናት የኖረን ህዝብ ” አንድ ነህ” ብሎ መንገር ” የስድብ ያህል ነው። ይልቁኑ አማራና ኦሮሞ ብቻ ሳይሆኑ በመላው አገሪቱ አጥፊዎችን ጭምር ነጻ የሚያወጣ፣ የፈሰሰውን ደም የሚጠርግ፣ አገር አቀፍ እርቅና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠሩ የሚበጅ ይሆናል።

እንደ ኤሌክትሪክ ቆጣሪ ሲፈልጉ ማባላት፣ ሲፈልጉ ” አንድ ናችሁ” ማለት የትም አያስኬድም። ህዝብ ሁሉን ያውቃል። ከመሪዎች አስተሳሰብ በላይ የህዝብ ግንዛቤ የላቀ ነው። መሪዎች በሚዲያ መናገራቸው አዋቂ ያሰኘናል ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸው ካልሆነ በስተቀር በርካታ የተቀረቀረባቸው አዋቂዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ አሉ። ከአገር ውጪም የሚያቀርባቸው ነጻ መድረክ ቢያገኙ ተአምር የሚሰሩ ዜጎች አሉ።

አሁን መታሰብ ያለበት የቀለም ቅብ ፖለቲካ ሳይሆን ቀናነት የተሞላበት እርምጃ ነው። አቶ ለማ መገርሳ እና ምክትላቸው ዶክተር አብይ በየመድረኩ ካንደባታቸው እየወጣ ያለው ሃሳብና ቁም ነገር ያስደስታል። ከሃያ ስድስት ዓመት በሁዋላ ሰው የሚሰማው ንግግር ማግኘት መልካም ነው። ንግግራቸው ለዛ አለው። መለስ ስሟን ላለመጥራት ” ይህቺ አገር” እያለ  ሲያኮስሳት እንዳልሰማን ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ወጣት መሪዎችን ማየት ልብ ይጠግናል። ሆኖም ግን ይህ የተገደለ፣ የታሰረ፣ የተገረፈ፣ የተጎዳና የታፈነ ህዝብ ከዚህ በላይ ለላቀ ፖለቲካዊ ውሳኔ ይመጥናልና አገሪቱን ፍትህ በሚያሰፍን የእርቅ ፖለቲካ ለማደስ ካሁኑ መስራቱ ግድ ነው። መጠጋገን እያደረ የከፋ ጣጣ እንጂ መፍትሄ ይዞ አይመጣምና!! ፋና ከዚህ በታች ያለውን ዘግቧል።

የኦሮሞና አማራ ህዝቦች ትስስር መድረክ ተሳታፊዎች ወደ ባህር ዳር ከተማ በማቅናት ላይ ናቸው። የኦሮሞና አማራ ህዝቦች ትስስር መድረክ ኮንፈረንስ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል።

የሁለቱ ክልሎች የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና አቶ አዲሱ አረጋ የምክክር መድረኩን ዓላማና ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም የምክክር መድረኩ “አብሮነታችን ለሰላማችን፤ ሰላማችን ለአብሮነታችን!” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

በኮንፍረንሉ ላይ ለመካፈልም ከ20 የኦሮሚያ ዞኖችና ከ18 ከተሞች የተወጣጡ ከ250 በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና አርቲስቶች ዛሬ ማለዳ ወደ ባህር ዳር ከተማ ጉዞ መጀመራቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።

በኮንፍረንሱ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አንድነት፣ ለሀገራችን ሰላምና ሉዓላዊነት ስለከፈሉት የጋራ መስዋዕትነትና ስለፈፀሙት አኩሪ ገድሎች ተነስተው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ገልፀዋል።

እንዲሁም የሁለቱን ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኦኮኖሚያዊ መስተጋብር የሚያሳዩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ እቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ የውይይት መነሻ ፅሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም አቶ አዲሱ አብራርተዋል።

ኮንፍረንሱን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ እና የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋችዉ በጋራ ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፥ የአማራ ህዝብ በኮንስረፍሱ ላይ ለመካፈል ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ እንግዶችን የአባይ ድልድይ ላይ ለመቀበል ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። በፍኖተ ሰላም፣ በእንጀባራ እና በባህር ዳር ከተሞችም ለእንግዶቹ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አቶ አዲሱ፥ የክልሉ መንግስት ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ጋር የህዝቦችን ወንድማማችነት እና አንድነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ቀጣይነት ያላችው ኮንፈረንሶች እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል።  በዚህም የሀገሪቱ ህዝቦች ትስስር፣ ሰላም እና አንድነት ብሎም ለዘመናት የቆየውን የህዝቦችን መስተጋብር በማጠናከር ረገድ የበኩሉን በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚያስችሉ ስራዎችን አቅዶ በመስራት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

You may missed

%d bloggers like this: