የኦሮሞ ኢትዮጲያዊነት ጠበቃና ምስክር አይሻም!

ሕወሃት/ኢህአዴግን አሁን ካለበት ቋፍ ላይ ያደረሰው ምንድነው? የብሔርተኝነት እሳቤ ነው። በመጀመሪያ የፖለቲካ አመራሩና ልሂቃኑ የፖለቲካ አቋምና አመለካከታቸውን ከሚወክሉት ሕዝብ ጋር ያጣብቃሉ። ከዚያ ከማህብረሰቡ ውስጥ የግለሰባዊነት መንፈስን በመሸርሸር ያጠፉታል። በምትኩ በቡድን እሳቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በሂደት እንዲሰርፅ ያደርጋሉ።

በመጨረሻም የፖለቲከኞችና ልሂቃን አቋምና አመለካከትን የህዝቡ የጋራ አመለካከት እንደሆነ አድርገው ማሰብ ይጀምራሉ። “ሕወሃት ከሌለ የትግራይ ሕዝብ የለም፣ የትግራይ ሕዝብ ከሌለ ሕወሃት የለም” የሚለው አባባል የብሔርተኘነት የመጨረሻው ደረጃ ነው። ይህ በፖለቲካ በፓርቲው አቋምና በሕዝቡ፣ እንዲሁም በማህብረሰቡና በግለሰቦች መከከል ምንም ዓይነት የአመለካከት ልዩነት የለም እንደማለት ነው።

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የተገነባው የፖለቲካ አመለካከት በመጨረሻ ሕወሃት/ኢህአዴግን ከሕዝቡና ከነባራዊ እውነታው እንዲነጠል አድርጎታል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ገለልተኛ ወይም ተቃዋሚ የሆኑ ወገኖች በድርጅቱ ሥራና አሰራር ላይ፣ እንዲሁም የሚወክለውን ሕዝብ አስመልክቶ ምንም ዓይነት የተለየ ሃሳብና አስተያየት እንዳይሰጡ ያደርጋል።

ምክንያቱም፣ በድርጅቱ ወይም መንግስት ሥራና አሰራር ላይ ትችትና ነቀፌታ መሰንዘር፣ ሌላው ቀርቶ ለየት ያለ ሃሳብና አስተያየት መስጠት በሚወክለው ሕዝብ ላይ የተሰነዘረ ጥላቻና ዘረኝነት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ለዚህ ዋና ምክንያቱ ከላይ የተጠቀሰው የብሔርተኝነት እሳቤ ነው። ይህ አመለካከት ያለው የፖለቲካ ቡድን ራሱን በሕዝቡ ውስጥ በመወሸቅ በሥራና አሰራሩ ላይ ምንም ዓይነት ትችትና ነቀፌታ እንዳይሰነዘርበት ይከላከላል።

የዚህ የፖለቲካ ቡድን ጭፍን ደጋፊዎች ደግሞ በፖለቲካ ቡድኑ ላይ የሚሰነዘረውን ትችትና አስተያየት ከሕዝቡ ጋር በማያያዝ አስተያየት ሰጪዎችን በዘረኝነትና ጥላቻ ይፈርጃሉ። በዚህ ምክንያት፣ በድርጅቱና አመራሮቹ ላይ ምንም ዓይነት ሃሳብና አስተያየት እንዳይሰጥ በማድረግ ልክ እንደ ሕወሃት ከሕዝቡና ከእውነት ያቆራርጡታል።

ኦቦ ለማ መገርሳ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እያራመዱት ያለው “የኢትዮጲያዊነት” አጀንዳ “ድርጅታቸው ኦህዴድ ከሕወሃት ጋራ ለገባበት ግብግብና ፍትጊያ የተጠቁሙት ስልት ነው” ማለት ከኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጲያዊነት ጋራ ምን ያገናኘዋል። እንደ ማንኛውም ዜጋ ኢትዮጲያዊነትን ማቀንቀን አንድ ነገር ነው። ነገር ግን፣ ድርጅታቸው ኦህዴድም ሆነ ኦቦ ለማ “ከዚህ ቀደም የኢትዮጲያዊነት አጅንዳን በዚህ መልኩ ሲያራምዱ ነበር” የሚል አካል ካለ ማስረጃውን ያቅርብ።

ከዚህ በተረፈ፣ “የብሔርተኝነት አጀንዳ ከሚያቀነቅነው ሕወሃት/ኢህአዴግ ጋራ ለገጠሙት የስልጣን ግብግብ ኢትዮጲያዊነትን ፖለቲካዊ ንቅናቄና ከብአዴን ጋር ትብብር ለመፍጠር ተጠቅመውበታል” የሚለው አስተያየት ከኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጲያዊነት ጋራ የሚያያይዘው ነገር አለ እንዴ? በጭራሽ የለም። ከዚያ ይልቅ፣ ነገሩ በፅሁፌ መግቢያ ላይ ከጠቀስኩት የጭፍን ብሔርተኝነት እሳቤ የመነጨ ነው።

ሲጀመር እኔ የኦሮሞን ኢትዮጲያዊነት መስጠት ወይም መቀማት፣ አሊያም መንቀፍ ሆነ መተቸት አልችልም። ሲቀጥል እናንተ ስለ ኦሮሞ ኢትዮጲያዊነት ከእኔ በላይ ምስክር መሆን አትችሉም። የኦህዴድን አመራር ከመተቸት በጭራሽ አልቆጠብም። የኦሮሞ ኢትዮጲያዊነት ደግሞ የእናንተን ጥብቅና እና ምስክርነት አይሻም።

– (ስዩም ተሾመ)

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s