Advertisements

ከአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት፤ ይናዳል ጅብ የጮኸ እለት!

የቀድሞው ሱማሌ ክልል መስተዳድር ልክ በአፄው ስርዓት ከነበረው ንጉሳዊያን አስተዳደር ጋር ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ያሏቸው ከመሆኑም ባሻገር በዋናነት የሁለቱም ስርአቶች በግለሰብ ስብእና ላይ የተመሰረተ መሆኑ ደግሞ አንድ ያደርጋቿል፡፡ በዚህም መሠረት በሱማሌ ክልል ላለፉት አስርተ አመታት የክልሉ የህግ አውጪ፤ የህግ አስፈጻሚና የህግ ተርጓሚ ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ወደ አንድ ሰው መዳፍ ጓዙን ጠቅልሎ የገባ እንደነበር ይታወቃል፡፡የነሲሆን ይሄውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ አብዲ ኢሌ ከሶስቱ ዋነኛ የመንግስት ስልጣን በተጨማሪ የክልሉን መሪ ድርጅትም በራሱ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ያደረገ ከመሆኑም ባሻገር በክልሉ የመንግስት መዋቅር ውስጥም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ በእውቀትና በርዕዮት አለም ትንተና ከእሱ የተሻሉ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን ሁሉ በኒኮሎ ማኪያቪሊ መጽሐፍ ላይ በተቀመጠው መርህ መሰረት ስልጣኑን እንዳይቀናቀኑት ከአካባቢው በማራቅ ምንም የትምህርት እውቀትትና የርዕዮት አለም ፅንሰ ሃሳብ የሌላቸውን አጨብጫቢ ግለሰቦች በመሰብሰብ የክልል መስተዳድሩን ሙሉ ለሙሉ እንደ አንድ የግል ኩባኒያ እንዲያስተዳድር መንገድ ከፍቶለት ነበር፡፡

አብዲ ኢሌ በሱማሌው ማህበረሰብ ብሎም በሌላው ኅብረተሰብ ዘንድ መገንባት የፈለገው ምስል ቀደም ያሉት መሪዎችም በመንገዱ ተጉዘዋለል፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት አንዱ ኃይለሥላሴ ናቸው፡፡ አጼ ኃይለሥላሴ ፀሐዩ ንጉስ በሚል መወድስ ወደ መለኮታዊነት ለመቀየር ሩብ ዓመት ሲቀራቸው በደርግ ወታደር የተገደሉ ሲሆን ፀሐዩ ንጉስ የሚለው መጠሪያ ለመስጠት የተፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ፀሐይ ለአለም ብቸኛዋ የብርሃን ምንጭ እንደሆነችው ሁሉ አፄውም የኢትዮጵያ መተኪያ የሌላቸውና ተፎካካሪ የማይገጥማቸው የብርሃን ምንጭ ናቸው የሚል የግለሰብ አምልኮን ጣሪያ ለማመልከት ሲሆን በተመሳሳይ ደግሞ አብዲ ኢሌም የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ እራሱን “ኣቦ” በሚል ስያሜ ሰይሞ በዙሪያው የተኮለኮሉት ደቀ መዛሙርቶቹ እንደ አማልክት ሊያመልኩት ጥቂት ግዜ ሲቀረው በክልሉ በተነሳው ህዝባዊ አመጽ ሊወገድ የቻሉ ቢሆንም በህዝቡ ውስጥ “አብዲ ኢሌ ከሌለ የክልሉ ሰላም ይደፈርሳል” በሚል ተራ አሉባልታ ሌላ ተተኪ አመራርም እንዳይገኝ እንዲሁም የስልጣን እድሜውም እንዲራዘም የቻለውን ሁሉ ጥረት አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጦረኛው የፈረንሳይ ንጉስ ናፖሊዮን የፈረንሳይ አጎራባች ሀገራትን በመውረሩ በእንግሊዝ መሪነት የተባበሩት ሀገራት አሸንፈውና ከስልጣን አውርደው በኤልባ ደሴት ባሰሩት ጊዜም ሆነ ህይወቱ ካለፈ በኋላ በርካታ ፈረንሳዊያን “ናፖሊዮን አይሞትም!” በሚል ተስፋ ተመልሶ እንደሚመጣ ይጠብቁት እንደነበር ሁሉ በሱማሌ ክልል የተነሳው ህዝባዊ አመጽ አብዲ ኢሌ ከስልጣን ተወግዶ በአዲስ አበባ ላይ በእስር ላይ የሚገኝ ቢሆንም ደጋፊዎቹ አሁንም አብዲ ኢሌ ተመልሶ እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቁት ነበር። ነገር ግን ይህ ይመለሳል የሚለው ህልም ከቀን ወደቀን እየደበዘዘ እየመጣ ነው -ሰዎች አሁን የመጣላቸውን መሪ የተለየ መሆኑን ሲመለከቱ!

በሌላ በኩል ደግሞ የአፄው መንግስት በርካታ የስልጣን ቦታዎችን በጨካኝነታቸውና በስግብግብነታቸው ለታወቁ መኳንንት ይሰጡ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው እነዚህ መኳንንቶች በጨካኝ አስተዳደራቸው ህዝቡን እንዲያስለቅሱ፤ እንዲያማርሩና በመጨረሻ ደግሞ ጉዳዩ ወደ እርሳቸው ጋር ሲደርስ ትንሽ መፍትሔና ማስተካከያ ለመስጠት እንዲያመቻቸውና ህዝቡ ደግሞ ንጉሱ እኮ ሩህሩህ እና ቅን አባት ናቸው ጨካኞቹ መኳንንቱ ናቸው ብሎ የህዝቡ ቁጣ ከስርአቱ ወደ አስፈጻሚው ለማውረድ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አብዲ ኢሌም በክልሉ በተለያዩ የስልጣን እርከን ላይ ያስቀመጣቸው ግለሰቦች በስግብግብነታቸውና በጨካኝነታቸው የሚታወቁ ቢሆንም ህዝቡ አብዲ ኢሌን አሁንም ቢሆን “ኣቦ ሩህሩህ ነው፤ ኣቦ ቅን ነው!” የምል አመለካከት እንድይዝ አድርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአፄው ስርአት የስልጣን መሠረታቸው እንዳይናጋ ከብቃት ይልቅ ታማኝነትን እንደ መስፈርት ይጠቀሙበት እንደነበር ለምሳሌ ያህል ጋብቻን እንደ ዋና የፖለቲካ መጠበቂያ ማድረግና ይህም አካሄድ ከንጉሱ የዘር ማንዘር ጋር የተጋባ ባለስልጣን ሁሉ ከአማቹ ውጪ የሚቀርበው ስለማይኖር የንጉሱን ስልጣን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ ይሆንበታል፡፡ በተመሳሳይ ደግሞ የአብዲ ኢሌ አስተዳደርም ከእሳቸው የጎሳ አባላት ውጭ ወደ ስልጣን የሚመጡትን በዚሁ የጋብቻ መስፈርት ብቻ ምንም አይነት ብቃት ሳይኖራቸው ወደ ስልጣን በማምጣት ለህልውናቸው ሲሉ የአብዲ ኢሌን ስልጣን መጠበቅ የግድ ይላቸዋል፡፡
በሰሞኑ የሚታየው ለአብዲ ኢሌ ድጋፍ ተደረገ ተብሎ የሚነገረው እንድሁም በፌስቡክ ለሱ መመለስ የሚያጨበጭቡት ከላይ የተሰጠው ማብራሪያ በደንብ ይገልፃቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ ለዝህም ይመስላል አድሱ የሙስጠፋ ኡመር አመራር ከአብዲ ኢሌ ጋር በመስራት የሚታወቀውን ጉሌድ አው አሊን የኮሙኒኬሽን ዘርፉን እንዲመራለት በማድረግ በአንድ በኩል አብዲ ኢሌ የገነባውን የውሸት ካባ እንዲያፈርስለት በሌላ በኩል ደግሞ ሁለተኛ ዕድል በመስጠት ራሱን እንድያፀዳ ለማድረግ የፈለገው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡

rajo

Advertisements

Zaggolenews. የዛጎል ዜና

Editor of zaggolenews.com contact editor - zaggolenews2016@gmail.com

You may also like...

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: