Advertisements

ይህን ሁሉ ጉድ ኢንጅነር ስመኘው ለምን ዝም አሉ?ለብሄራዊ ውርደት ተጠያቂው የሆኑት ለምን ህግ ፊት አይቀርቡም?

አሁን ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው አንድ አበይት ጉዳይ ሁሉንም በፊርማቸው የሚያጸድቁትና አንድም ጉዳይ ሚስጢር የማይሆንባቸው ኢንጂነር ስመኘው ይህንን ሁሉ ጉድ ለምን ዝም አሉ? የሚለው ነው። ይህ ብቻ አይደለም ስመኘው ሁልጊዜ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ማብራሪያ ሲሰጡ ችግር እንዳለ እንኳ ፍንጭ አይሰጡም ነበር።

ከፕሮጀክቱ ብሄራዊ ይዘት ጋር ” ብሄራዊ ጀግና” የተባሉት ኢንጂነር ስመኘው ሞታቸው በሄራዊ ጉዳይ ሆኖ ፍትህ እንዲበየንላቸው በተደጋጋሚ የሚጠየቅላቸው ህዝብ ብሄራዊ ጅግና ስላደረጋቸው ነው። እናም በዚህ ሁሉ የብሄራዊ ጀግንነት ሞገስ ውስጥ ሆነው ይህ ሁሉ ምስቅልቅል ሲደርስ፣ የሃሰት ሪፖርት ሲቀርብ፣ አሁን ባለስልጣናት እንዳሉት ባለቤት አልባ ፕሮጀክት መሆኑንን እያዩ እንዴት አስቻላቸው? ብሎ መጠየቅ ነውር አይሆንም።

በግልብ ስሜት የሚነዱ ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው ይህ ከልጆች ጉሮሮ እየተነጠቀ የተገበረለት ፕሮጀክት በዚህ መልኩ ሲነቅዝና ብሄራዊ ውርደት እስኪሆን ዝምታ የመመረጡ ሚስጢር ከምንም በላይ ይከነክናል። ያማል። ይህን ፕሮጀክት ለመደገፍ ዜጎች ከልጆቻቸው ጉሮሮ እየነጠቁ በከፈሉት ገንዘብ ህግና ደንብ በመጣስ ዝርፊያ የፈጸሙት ለፍርድ ይቅረቡ ቢባል ጉዳዩ ይጥላቻና የብሄር ጉዳይ አድርጎ ማየት ያሳፍራል።

ይፋ ክሆነው አስደንጋጭ ሪፖርት የሚከተለውን ጨምቀን አውጥተናል።

የኢንጅነር ስመኘው በአሳዛኝ ሁኔታ መገደላቸው ይፋ ከመሆኑ ሁለት ቀን በፊት ጥልቅ ውይይት መደረጉንና ቀደም ሲል ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ይውል ከነበረው መረጃ ጋር የማይጣታም እውነተኛ ሪፖርት ቀርቦ እንደነበር የውሃ መአድንና ኢነርጂ ሚኒስትር በዝርዝርም ባይሆን በግርድፉ ተናግሯል።

የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው ይህ ጉዳይ ተይዞ ባለበትና ሁኔታ በቀናት ውስጥ መገደላቸው ከጉዳዩ ጋር ምን ያህል ተያያዥነት እንዳለው በይፋ ፍንጭ የሰጠ አካል ባይኖርም አብዛኞች መላ ምታቸው ግድያው ከዘረፋ ጋር ይገናኛል የሚል ነው። ፖሊስ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት በቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ ቃል በመግባቱ በጉዳዩ ዙሪያ ከዚህ በላይ ማለት አይቻልም።

ይህ በንዲህ እንዳለ በደፈናው ሲነገር የቆየውን ጉዳይ ፋና ቲቪ ገልልጦ አሳይቶታል። በፋና ፕሮፓጋንዳው ሲሰራ እንዳልነበር፣ ዛሬ በራሱ በፋና የህዳሴው ግድብ ” ህዝብን በመዋሸት አዙሪቱ የተመታ” መሆኑንን መስማት ያስገርማል። በርካቶች እንደሚሉት ይህ የሚዲያ ነጻነት ከለውጡ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ያስደስታል።

 

” እኛው እንደጀመርነው እኛው እንጨርሰው” በሚል መፈክር የተጀመረው የህዳሴ ግድብ ከጅምሩ በየደረጃ እንዲከፋፈልና አንዱ ሌላውን እየመገበ እንዲሰራ በዘርፉ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ምክር ለግሰው ነበር። ጉዳዩ ዛሬ ፋና እንዳለው የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስላለበት ሰሚ ጥፍቶ በዚያው በተጀመረበት እንዲቀጥል ተደረገ። 

ይህ ሕዝባዊ መነሳሳትን የፈጠረ ታላቅ ግድብ እያንዳንዱን ቤት የዳሰሰ፣ የሚሊዮኖችን ዜጎች ኪስ ያሸተተ፣ ብርቅና ውድ የሆነ ፕሮጀክት በዜጎች ልቦና ላይ ያሳደረው ኩራት በቀላል የሚነገርም አይደለም። ፰፭ ቢሊዮን ብር ወጪ ይሆንበታል ተብሎ የተጀመረው የህዳሴው ግድብ በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠቃለላል ቢባልም ዛሬ በሰባተኛ ዓመቶ ስራው ስልሳ አምስት በመቶ ብቻ መከናወኑን አማካሪ ድርጅቱ፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት የመንግስት ተቋማትና ባለሙያዎች እየነገሩን ነው።

 

ፋና ሁሉንም ወገኖች አካቶ ባዘጋጀው ዘገባ / ቪዲዮ ፩፣፪/ ይመልከቱ ያለ አንዳች ልምድ የሃ አምስት ቢልዮን ብር ስራ የተረከበው ሚቴክ እንኳን ስራውን ሊሰራ ያልሰራበትን ገንዘብ ሲሰብስብ እንደነበረ ሃላፊዎቹ አረጋግጠዋል። አስራ ሰድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የቆረጠመው ሚቴክ፣ ስልሳ አምስት በመቶ መስራት ሲገባው የሰራው ሰላሳ በመቶ ገደማ ነው። 

እዚህ ላይ የሚገርመው ሚቴክ ያልሰራበትን ሲበላ እየታወቀ የሚናገር አለመኖሩና ክፍያው በትዕዛዝ የሚከናወን መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ ሚቴክ ስራውን አጠናቆ ለማስረከብ የተዋዋለው ሃያ አምስት ቢሊዮን ብር የተዋዋለ ሲሆን የሚቀረው ገንዘብ ስምንት ቢሊኦን ብቻ ነው። ለፋና በግልጽ አስተያየታቸውን የሰጡት ሚኒስትሩ ” ቀሪው ስራ በስምንት ቢሊዮን አይጠናቀቅም” ሲሉ እንቅጩን ተናግረዋል። የሚቴክ ሃላፊም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ላይ ታሪካዊ ወንጀል የፈጸመው ሚቴክ ያልሰራበትን መብላቱ ብቻ ሳይሆን ሳሊኒ በወቅቱ ስራውን ጨርሶ እንዳያስረክብ የሚቴክ እንቅፋት መሆን ሌላ ኪሳራ አስከትሏል። ሳሊኒ ስራውን በወቅቱ አጠናቆ ማስረከብ እየቻለ ሚቴከ እንቅፋት በመሆኑ ሳሊኒ ሰባ ስምንት ሚሊዮን ብር እና አስራ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ካሳ እንዲከፈለው ጠይቋል።

በሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዩሮ አጠቃላይ ክፍያ ስምምነት የገባው ሳሊኒ ስራውን በጊዜው እንደጨረሰ ሪፖርቱ ያስረዳል። ይሁን እንጂ እንቅፋት የገጠመው በሚቴክ በኩል በመሆኑ አሁን ለደረሰው ኪሳራና ጉዳት ተጠያቂው ማን ይሆናል የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው። የሚቴክ ሃላፊ እንዳሉት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው በሚገባው ደረጃ አለመሰራቱ አምነዋል። ሚቴክ ስራውን ሳይሰራ የወሰደው አምስት ቢሊዮን ብር የት ሄደ የሚለው ጉዳይ ታላቅ የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈልግ ይሆናል።

የአገሪቱን የስኳር ፕሮጀክቶ በመቶ ቢሊዮን ብር አውድሞና ፕሮጀክቱን አጨመላልቆ የወጣው ሚቴክ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የፈጸመው ድርጊት ለህዝብ ይፋ ከመሆኑ በፊት ሃላፊዎቹ እንዲነሱ ተደርገዋል። ጉዳዩ በቀጣይ በህግ የሚታይ ይሁን በሌላ በሪፖርቱ አልተጠቆመም። 

በሪፖርቱ ማጠቃለያ የህዳሴው ግድብ ሃይል ለማመንጨት የሚያስችለው ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተደርጎ ሲወራ የነበረው ሃሰት እንደሆነ፣ ያለቀና የተፈጸመ ነገር እንደሌለ፣ ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ከተባለለት ጊዜ ሁለት ዓመት ዘⷝቶም ቢሆን አሁን ያለበት ደረጃ ሥልሳ አምስት በመቶ ግድም በመሆኑ እንዲሁ በቀላሉ በቅርብ ይጠናቀቃል የሚል ግምት የለም። እንደ ሪፖርቱ አቅራቢ ይህ ሁሉ ሲሆን እየታወቀ መንግስት የት ነበር የሚለው ጉዳይ ይጎላል። ከዚያም በላይ ይህ ሁሉም የገብረበት አገራዊ ፕሮጀክት በዚህ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ ኢንጅነር ስመኘውስ በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተያየት ሲሰጡ ምነው ዝም አሉ ቢባል አግባብ ይሆናል።

ከሁሉም በላይ ግን በየደረጃው የህዳሴውን ግድብ አስመልቶ ሲቀርብ የነበረው ፕሮፓጋንዳ እንደ ሪፖርት አቅራቢው ” ሕዝብን መዋሸት ለምን አስፈለገ” ለሚለው ጉልህ ጥያቄ መልስ የሚሰጡት እነማን ናቸው?

elpa

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ ፕሮጀክቱ በባለቤቶቹ የማይታይ፣ ቁጥጥር የማይደርገብት፣ ክፍያ በትዕዛዝ የሚከናውንበት የፕሮጀክት አሰራር ሂደትና የቁጥጥር መርህ ያልተከተል እንደሆን በግልጽ ተናግረዋል። ይህ ሁሉ ገበና የተሸከመው የህዳሴ ግድብ እንዴት ነው የህዝብ ንብረት ነው የሚባለው?


 

Advertisements


Categories: Head News/መሪ ዜና, Video and Audio

Tags:

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: