Advertisements

የተፎካካሪዎች ከኢሕአዴግ አለመሻል

ጌታቸው አስፋው (የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)
በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት የኢኮኖሚ አስተዳደር መንቀፍ አይከብድም፤ ስህተትን ነቅሶ ማውጣትና ስህተት አለመሥራት አንድ አይደሉም፡፡ የተፎካካሪ ድርጅቶች ሁሌም የሚሉት፣ መንግሥት እነዚህን ስህተቶች ሠርቷል፤ እኛ ብንሆን ኖሮ አንሠራም ነበር የሚል ነው፡፡ መንግሥትም እስቲ ልትሠሩ ያሰባችሁትን አሳዩኝና የእናነንተ ከእኔ ይበልጥ እንደሆነ እንመልከት ይላቸዋል፡፡ እነርሱም የምንፈፅመውን ወደ አደባባይ የምናወጣው ወደ ተግባር ለመቀየር ስንችል ብቻ ነው የሚል አቋም ይዘውም ይሆናል፤ ስለማይገደዱበትም እኛ የምንፎካከረው ሥልጣን ተወዳድርን ለማሸነፍ እንጂ ለኢሕአዴግ አስተዳደራዊ ጉድለት መድሃኒት ልንቀምም አይደለም ይላሉ፡፡

መንግሥት ራሱ ሆን ብሎ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንዳይቻል ሥልጣን ተወዳድሮ የማግኘት ዕድል ሳይሰጣቸው ተፎካካሪዎችን አደናቅፎ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓል ብሎ ለማውገዝ ምን ዓይነት አማራጮች ቀርበው ነበር ወይም ለማቅረብ ታስቦ ነበር ብሎ መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ የተሻለ መኖሩ ካልታወቀ የሚያውቁት ሰይጣን ከማያውቁት መልአክ ይሻላል የተባለውን ተረት መድገም ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶችን ደካማና ጠንካራ ጎንም በመጠኑ መፈተሸ አቅማቸው ለማነሱ ውስጣዊና ውጪያዊ ምክንያቶች መኖር አለመኖራቸውን መርምሮ ማወቅ የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ለመረዳት ከሚደረግ ጥረት አንዱ ክፍል ነው፡፡

የሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመውጣት አገር ለመምራት ባላቸው ጽኑ ፍላጎት ቡድናዊ ፖለቲካዊ ዴሞክራሲን ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና ከሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያስቀድሙ የፖለቲካ ሰዎች ያላወቀ፣ ያልተረዳ፣ በቤተሰብና በጎሳ አመለካከት ስሜታዊ የሆነና በጠባብ የዘረኝነት ፍቅር የታወረ፣ በኢኮኖሚ በማኅበራዊ በፖለቲካና በመንፈሳዊ ጥቅል ሕይወቱ ያልለማ ሰው፣ ከራሱ ኋላ ቀር አስተሳሰብም ነጻ ያልወጣ ሰው በባለማወቅ ዕውቀቱ ለገዢነት ሥልጣን እንዲወክላቸው የሚፈልጉ ናቸው፡፡

የኢሕአዴግ ነባር ታጋዮች እንደሚናገሩት ደርግን ለመጣልና ለስኬት የበቁት የብሔር ብሔረሰብን ጥያቄ የትግላቸው ዓላማ በማድረጋቸው ነው፤ ምክንያታቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና የከፋ ስለነበረ ነው ይላሉ፡፡ መልሰው ደግሞ ጨቋኝ ብሔር አልነበረም የነበሩት ከአንድ ብሔረሰብ የወጡ ጥቂት የገዢ መደቦች ናቸው ይላሉ፡፡ ማንኛውም ትግል ከኋላው ደጀን የሚሆነው አጋር እንደሚፈልግ የታወቀ ነው፡፡ በኋላቀር ኅብረተሰብ ውስጥ ደግሞ ከመደብ ትግል ይልቅ የብሔር ትግል ደጀን ለማግኘት የተመቻቸ ሁኔታ አለው፤ ምክንያቱ ደግሞ ዘር ከልጓም ይስባል እንደሚባለው ነው፡፡ ስለሆነም የብሔረሰብ ትግል ለጥቂቶች የሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመቀመጥ የትግል ስልት እንጂ የብዙዎችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር የሚፈታ ግብና ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ አልሆነም፡፡

ኢሕአዴግ በዚህ መልክ አባላቶቹን በብሔር መልክ አደራጅቶ አታግሎ ደርግን ሊያሸንፍ ችሏል፡፡ ግንባሩ ሥልጣን ለመያዝ የተጠቀመበትን ሥልቱን በሥልጣን ለመቆየትም እየተጠቀመበት ነው፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩት የአንድ ብሔረሰብ ገዢ መደቦችን ታሪክ እያነሱ የትግል ዓርማ እንዲያደርጉ ፈቅዶ ፀብ እንዲጋጋል ሁለትና ሦስቱ እርስ በርሳቸው ሲጣሉ ሰላም አግኝቶ ያለተቀናቃኝ የመግዛት ስልት አድርጓል፡፡ “ውሻ በቀደደው ጂብ ይገባል፤” እንዲሉ፣ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን ባይታወቅም፣ የኢሕአዴግን ፈለግ የተከተሉ ጠባብነት የሚያጠቃቸው ተፎካካሪ በብሔረሰብ የተደራጁ ፖለቲከኞችም ሕዝብ ለማበጣበጥ አልቦዘኑም፡፡ ሳያስቡት የኢሕአዴግ ፖለቲካ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ሕዝብ እንዲበለጽግና መሠረታዊ መብቶቹ እንዲከበሩ ስለ ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ውድድራዊ ሥርዓትና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከመናገር ከመጻፍ ከመደራጀት የመሳሰሉ የግል ኢኮኖሚና የሕዝባዊ ዴሞክራሲ መገለጫዎች ይልቅ በውክልና ዴሞክራሲ የፓርላማ መቀመጫ ሥልጣን ከያዙ በኋላ እነርሱ ለሕዝብ የፖለቲካ ነጻነት እንደሚሰጡ አድርገው ይሰብካሉ፡፡ አዲስ ሐሳብ እንደማፍለቅ፣ በኢሕአዴግ ድክመቶች ላይ ብቻ አነጣጥረው ይተኩሳሉ፡፡

እነኚህ በአንድ በኩል በንባብ እውቀታቸውን አለማበልጸግ፣ የተማሩ ሰዎችን በአባልነት አለመመልመል፣ ለአባሎቻቸው ወቅታዊ ሥልጠና አለመስጠት፣ የራሳቸው ውስጣዊ ድክመትና በሌላ በኩል ከኢሕአዴግ በሚሰነዘርባቸው ከሐሳብ አንስቶ እስከ የጉልበት ውጪያዊ ዱላ ምክንያት ከእጅ አይሻል ዶማ የኢሕአዴግ ድክመት ግልባጮች ሆነዋል፡፡ የኢኮኖሚ ነጻነት ካላገኘ ኅብረተሰብ ውስጥ በቂ የፖለቲካ ሞጋች ሰው እንደማይወጣ ያልተገነዘቡ፣ ባጣ በነጣ ኅብረተሰብ ውስጥ የኢኮኖሚ ነጻነትን ከፖለቲካ ነጻነት አሳንሰው የሚመለከቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ኢሕአዴግ አንድ ቀን ተነስቶ በፖለቲካው ሊበራል ቢሆንና ሰብአዊ መብትንም ቢያከብር ምርጫም ተወዳደሩና አሸንፉ ቢል አሸንፈው ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ እንኳ የማያውቁ ሰዎች ስብስብ ምን ይውጣቸው ይሆን? “ብርሌ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ በእጅ ሲይዙት ያደናግር፤” የሚለውን ብሂል አያውቁም ይሆን? ሥልጣን ምርቃት ብቻ ሳይሆን እርግማንም ጣፋጭ ብቻ ሳይሆን መራራም እንደሆነ አያውቁም ይሆን፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ኀይለ ማርያም በአንድ የተበሳጩበት ወቅት “የድሃ አገር መሪ ከመሆን የሀብታም አገር ሆቴል ሥር አስኪያጅ መሆን ይሻላል፤” ያሉትን አያስታውሱም ይሆን?

የዘውዳዊውን መንግሥት ለመጣል እዚህና እዚያ በራሳቸው በዘውዳዊው ሥርዓት አባሎች ንጉሠ ነገሥቱን ለመግደል በነ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት ፈንጂ እስከማጥመድ ድረስ የተካሄዱት አመጾች እያደጉ መጥተው የ1953ቱን የመንግሥቱ ንዋይን አመጽ ቢቀሰቅሱም ሕዝቡን ለማኅበራዊ ለውጥ ፍላጎት አነሳስተው እንደ አምላክ ይፈራቸው የነበሩትን ነገሥታት እንዲከዳ ያደረጉት ለረጅም ዓመታት የተካሄዱ የተማሪዎች ሕዝቡን የማንቃት እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን በደርግ ዘመን ዐሥራ ሰባት ዓመት ከካፒታሊዝምም አልፎ ሶሻሊስት ፍልስፍና ውስጥ ገብቶ በሠርቶ አደር ጋዜጣ የእነ ማርክስን እና የእነ ሮዛ ሉክዘምበርግን ዓለም ዐቀፋዊ ሕዝባዊ የወዛደር ኅብረትን ሲያነብ ሲሰማና ሲጠመቅ የኖረን ሕዝብ ኩባዊ በዓለም ዐቀፋዊ ወዳጅነት በኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት እንደተማገደለት የሚያውቅን ሕዝብ ወኋላ በመጎተት በመንደር ልጅነት አሰባስበው የምክር ቤት ውክልና ሥልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የቸኮሉ ሰዎች የቡድን ውክልና ፖለቲካን ከዳቦና ከሕዝባዊ ሰብአዊ መብቶች ያስቀድማሉ፡፡ ሕዝቡ በሥራ ማጣት፣ በዋጋ ግሽበት፣ ፍትሐዊ ባልሆነ የሀብትና የገቢ ክፍፍል፣ ነጋዴው በውጭ ምንዛሪ እጦት፣ በግል እየተሰቃዩና በሰብአዊ መብት ገፈፋ አኩርፎ ባለበት ጊዜ የኢኮኖሚና የሰብአዊ መብት ሕዝባዊ ዴሞክራሲ ጉዳይ ወደ ጎን እየተገፋ የቡድን ውክልና ፖለቲካ ያውም በጠባብነት አስተሳሰብ የተከፋፈለ የውክልና ዴሞክራሲ ጥያቄ ዋናው የአገሪቱ ጉዳይ ተደርጎ ይነገራል፡፡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማና ግብ ከኢሕአዴግ ሥልጣን ተረክቦ ለመተካት ሳይሆን የኢሕአዴግ ተለጣፊ ባለሥልጣን ለመሆን ነው፡፡

ለግል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነት በጋራና በኅብረት ከመታገል ይልቅ የውክልና ፖለቲከኞች የኩባን ትግል አብሮ መርቶ ፊደል ካስትሮ ሥልጣን እንደያዙ ሁለተኛውን የሥልጣን እርከን የፕላን ሚኒስትርነትን ሹመት ቢሰጡት ትግሌ ለዓለም ጭቁኖች ሁሉ ነው ብሎ ቦሊቪያ ሄዶ መንግሥት ለመጣል ሲታገል ተይዞ ከተገደለውና የ1960ዎቹ ተማሪዎች ከዘመሩለት የአርጄንቲና ተወላጅ ቼ ጉቬራ ዓላማ ጋር የሚጋጩ ናቸው፡፡

እዚህ ላይ የ1960ቹ የተማሪዎች የትግል ዓርማ መሬት ለአራሹ ሲሆን ዋናው የቅስቀሳ መፈክር ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፣ እንደ ሆቺሚኒህ እንደ ቼገቬራ፣ በዱር በገደሉ ትግሉን እንድትመራ የሚል ነበር፡፡ ይህ መፈክር ነው ዘር፣ ቀለም፣ ብሔረሰብ፣ ጎሳ፣ ሳይለዩ እንደ ንብ መንጋ አንድ ሆነው ከደርግ ጋር አብረን እየሠራን ከውስጥ ፈንግለን እንጥለዋለን ያሉትን የቀይ ሽብር ተዋንያን መላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄን (መኢሶን) እና የትጥቅ ትግል በዱር በገደል ያሉትን የነጭ ሽብር ተዋንያንን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) ለኹለት ተቃራኒ ጎራ አሰልፎ ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር በሚሉ ስያሜዎች ደም አፋሳሽ ትግል የተደረገው፡፡

ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት ለፖለቲካ ሥልጣን ድምጽ ሲሰጥ ሰውየው ሳይሆን ዳቦው ነው የተመረጠው፡፡ ዘመናዊና ሐቀኛ ፖለቲከኞችም ለራሳቸው ሥልጣን ከማግኘት ይልቅ ሕዝብ ሰውን ሳይሆን ዳቦውን እንዲመርጥ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም በዴሞክራሲ ስም ለመወከል እና ፓርላማ ለመግባት ከመሽቀዳደም በፊት ሕዝቡ ማንን ለምን እንደሚመርጥ ለሰው ብሎ ሳይሆን ለራሱ ለዳቦው ለመብቱ ሲል እንዲመርጥ ማስተማር መጻፍ መናገር ከሕዝብም መስማትና መማር ማስቀደም ያስፈልጋቸው ነበር፡፡

ከስብሰባ አጀንዳና ከጋዜጣ እሰጥ አገባ ሙግት በቀር ሌላ ዘመናዊ የሕዝብና የኢኮኖሚ አስተዳደር ጥበብን ሰምተውም ተናግረውም፣ አንብበውም ጽፈውም የማያውቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከኢሕአዴግ በተሻለ ሁኔታ ይመሩናል ብሎ ሕዝብ አላመነም፤ በብዙ ነገሮች ታዝቧቸዋል፡፡ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ የፖለቲካው ኩሬ ውኃ ውስጥ ገብተው የሚዋኙ ሰዎች ያሰቡት ሳይደርሱ በሁለት መንገድ ይወድቃሉ፡፡ አንድም በቅንጅት፣ በአንድነትና በሰማያዊ ፓርቲዎች እንደታየው በመፈንቅለ አመራር እየተናወጡ፣ ስም ብቻ ተሸክመው ይንገታገታሉ፤ አሊያም ዕድሜያቸውን ቆጥረው የእርጅና ክረምት ገብቶ የሚዋኙበትን ኩሬ ውኃ ሲያቀዘቅዝባቸው፣ የአቅም ማነስ ዝምታ በተባለ የሞቀ ብርድ ልብስ ውስጥ ገብተው ነገረ ዓለሙን በተስፋ መቁረጥ እስከዘላለሙ እስኪሰናበቱ ድረስ ይተኛሉ፡፡ ይህ የተፎካካሪ ፖለቲካ ቡድኖች ድክመት ለኢሕአዴግ ጥንካሬ ሆኖ ከሩብ ምዕተ ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በሕዝብ ተወዳጅ መንግሥት ነኝ እያለ እየዋሸ ለመኖር አስተዋጽኦ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዘ ነው፡፡ ዛሬ ሕዝቡ ኢሕአዴግን እየተንገሸገሸ ጠላሁህ ባለበት ወቅት እንኳ ከሕዝቡ ጎን ቆሞ ሰላማዊ ትግሉን የሚመራ ድምጹን ከፍ አድርጎ የሕዝቡን ስሜት የሚገልጽ ተፎካካሪ ድርጅት ጠፍቶ ሕዝቡ ሁከት ወደ አመጽና ብጥብጥ ውስጥ ገባ፡፡

black lion FB

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: