Advertisements

የጳጉሜን ስሌት በአመታት ውስጥ

ጳጉሜን ማለት ምን ማለት ነው? 
የአስራ ሶስት ወር ጸጋ የማይለይሽ፣
ለምለሚቱ አገሬ ኢትዮጵያ እንዴት ነሽ!?

ሲሉ ገጣሚያን ያወድሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከአለም አገራት በተለየ መልኩ አመቱን በአስራ ሶስት ወራት ትቆጥራለች ፡፡አሰራሶት ወር የኢትዮጵያ ብቻ ጸጋ ነው፡፡ አውሮፓውያን አመቱን ሲቆጥሩ ግማሹን ወር 31 ቀን፣ ግማሹን ደግሞ 28 ወይም 29 ያደርጉታል፡፡

አብዛኛው የአለም አገራትም የአውሮፓውያንን አቆጣጠር በመውሰድ ወራትን እና ቀናትን ሲቆጥሩ ይታያሉ፡፡ ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን ፣ኢትዮጵያዊ ማንነቱን አይቀይርም!›› እንዳለ መጽሀፍ፤ ኢትዮጵያውያን ግን ከማንም ምንም ሳይወስዱ በራሳቸው ቀለም የራሳቸውን የዘመን አቆጣጠር ይከተላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አስራ ሶሰት ወር ያላት ብቸኛ አገር ያደርጋታል፡፡ ኢትዮጵያ አስራ ሶስቱን ወራት ከወቅቶቹ ጋር በማያያዝ ለወቅቱ ተስማሚ አድርጋ ሰይማለች ፡፡

እንደ አውሮፓውያን ሁሉ በቀደሙ ነገስታት ስም የወራትን ስም አልሰየመችም፡፡ ገበሬው በሚያርስበት፣ በሚያርምበት ፣በሚያጭድበት በሚወቃበት… በመመስረት የወራትን ስያሜ ሰጥታለች፡፡ኢትዮጵያ በአለም ላይ ልዩ ከሚያደርጓት በርካታ ነገሮች አንዱ የአስራ 
ሶሰተኛዋ ወር ወረሃ ጳጉሜን ነች፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከወርሃ ነሐሴ በኋላ ጳጉሜን የምትባል አምስት ቀን አለች፡፡ ‹‹ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፡፡ ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ሆናለች›› ይላሉ አበው፡፡ እዲህም ሆኖ አስራ ሶስተኛ ወር ተብላ ትጠራለች፡፡ጳጉሜን በአራት አመት አንድ ጊዜ 
ስድሰት ቀን ትሆናለች ፡፡

በስድሰት መቶ አመት ደግሞ አንድ ጊዜ ሰባት ቀን ትሆናለች፡፡ ጳጉሜን የሚለው ስያሜዋ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ እንደሆነ በአበው ቃል ይነገራል፡፡ “ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጳጉሜን ተረፈ-ዘመን 
ማለት ነው፡፡ አውሮፓውያን ጳጉሜን የወር ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጥር ሠላሳ ስናደርግ እነርሱ ሠላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ
ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡

የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከግማሽ ብለው ደምረውታል፡፡ አንድ አመት 365 ቀን ከግማሽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአስራሁለት ወራት 30 ቀን እኩል ሲከፈል 360 ይሆን እና 5 ቀን ከግማሽ ይሆናል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ አመት 364 ቀን ሲሆን አንድ ቀን ከግማሽ ከሽርፍራፊ ሰአታት ይገኛሉ ይላሉ፡፡

ይህ ደግሞ ከበጋ ስድሰት ሰአት ፣ከክረምት ስድሰት ሰአት ፣ከበልግ ስድሰት ሰአት እና ከጸደይ ስድስት ሰአት ትርፍ ይገኛል፡፡ አራቱ ሲደመሩ 24 ሰአት (አንድ ቀን)ይሆናሉ ፡፡ከ364 ቀኑ ላይ አንድ ቀን ሲጨመር 365 ቀናት ይሆናል፡፡ አራቱ አመታት ደግሞ ዘመነ ዮሃንስ ስድሰት ሰአት ፣ዘመነ ማርቆስ ስድሰት ሰአት፣ ዘመነ ማቲወስ ስድሰት ሰአት፣ ዘመነ ሉቃስ ስድሰት ሰአት፣ በየአመቱ ትርፍ አላቸው፡፡

እነዚህ ተደምርው ደግሞ አንድ ቀን ስለሚፈጥሩ ስድሰተኛዋን ጳጉሜን ይፈጥራሉ፡፡እነዚህ እየተሸከረከሩ በስድሰት መቶ አመት አንድ ጊዜ ሰባተኛዋን ጳጉሜን ይፈጥራሉ፡፡ ጳጉሜን የቅዱስ ዮሃንስ ሳምንትም ትባላለች፡፡ ቅዱስ ዮሃንስ ሀሰተኛ መምህር ነህ በሚል በአይሁዶች ተይዞ የታሰረው የጳጉሜን የመጀመሪያ ቀን ስለሆነ 
ሳምንቷ የዮሃንስ ሳምንት ትባላለች፡፡

የጳጉሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜን የዓመታት መሸጋገሪያ፣ ጨለማውን የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊው፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊው፣ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነው፡፡ “ጳጉሜን ዕድሜ ትሰጠናለች፤ በኋላም ታድነናለች” ብለው ጾም ይጾሙባታል፡፡ንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ የጾም ሥርዐት ይፈጽሙባት ነበር፡፡

ክርስቲያኖች በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉትም ፈጣሪ የተባረከ ዓመት እንዲሰጣቸው፣ ባለፈው ዓመት የሰሩት ኃጢያት እንዲደመሰስላቸው በማሰብ ነው፡፡‹‹የተቀደሰው ጸበል ከበሽታችን ያድነናል፤ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል›› በሚል ታላቅ እምነት ከህጻን እስከ አዋቂ በጠዋት በመነሳት በጳጉሜን ቀኖች ሁሉ ይጠመቃሉ፡፡

የመረጃ ምንጭ፡- (ባህረ ሃሳብ፡- የአትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እና ሊቃውነት የቤተ ክርስቲያን አባቶች)

ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ አማራ ማስ ሚዲያ

Advertisements


Categories: Art/ጥበብ

Tags:

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: