ጃዋር የፖለቲካ ሥልጣን ቢኖረው በዮ ለአንዳፍታ አሰብኩና -ያሬድ ሃለማሪያም

ጃዋር በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው ቃለ-ምልልሶች ውስጥ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የሚሰነዝራቸው አንዳንድ አስተሳሰቦቹ በውስጡ እያቆጠቆጠ ያለ የአንባገነናዊነት ስሜት መኖኑን በግላጭ የሚያሳዩ ናቸው። ባለፉት ጥቂት አመታት በኦሮሞ ሕዝብ የመብት ጥያቄ እና ትግል ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ጃዋር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉን ወጣቶች በሺዎች ማይልስ ላይ ሆኖ ማነቃነቅ እና መምራት መቻሉ፤ እንዲሁም ትግሉ ጫፍ እንዲደርስ ያደረገው ታላቅ ተጋድሎ የሚካድ አይደለም። ሌላው ጃዋር ጎልቶ የሚታወቀው እጅግ አወዛጋቢ የሆኑ ነገሮችን በድፍረት በማንሳት የወዳጆቹን ብቻ ሳይሆን የነቃፊዎቹንም ቀልብ የመሳብ ችሎታው ነው።

ይሁንና በብዙ ንግግሮቹ ውስጥ ከትንተና ችሎታው ጀርባ በግልጽ የሚታይ የአንባገነናዊ ስሜት አለ። የዛሬውን ከLTV ጋር ያደረገውን ውይይት ሰማውና ይሄ ሰው ስልጣን ሳይኖረው እንዲህ ከሆነ ስልጣን ቢያገኝ ምን ሊያደረገን ይሆን ብዮ ለአንድ አፍታ ማሰብ ጀመርኩ። ሕዝብን በተለይም ወጣቶችን መምራትና ማንቀሳቀስ መቻሉ የሰጠው ድፍረት ሳይሆን አይቀርም እራሱን የሁሉ ነገር አድራጊና ፈጣሪ፤ እንዲሁም ያሻውን የማድረግ አቅምና ሥልጣን ያለው ሰው አድርጎ እንደሚቆጥር ብዙዎቹ መልሶቹ በግልጽ ይናገራሉ። በንግግሩ ውስጥ ትቢት፣ ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን፣ ከእውቀትም የዘለለ ጥራዝ ነጠቅነት፣ ቄሮን የመሰለ ትልቅ የለውጥ ኃይል እሱ እንደፈለገው ሊያሽከረክረው የሚችል እና በአንድ ጭንቅላት ብቻ የሚመራ ቡድን አድርጎ ማስቀመጥ እና ለነጻነት የሚታገል አንባገነን ሆኖ ነው ያገኘሁት።

አንዳንድ ንግግሮቹ እሱ ከፈለገ የኦሮሞን ሕዝብ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ሊነዳ እንደሚችል የሚያስብ ያስመስለዋል። ቀደም ሲል በሰጣቸው ሌሎች ቃለ-ምልልሶቹም ‘እኛ ብንፈልግ ኖሮ ኦሮሚያን እንገነጥላት ነበር’ የሚለው አነጋገሩ ብቻ ሰፊውን የኦሮሞን ሕዝብ እንዳሻኝ ማድረግ እችላለሁ የሚል እብሪት የተሞላበት አነጋገር ነው። በአገሪቱ ውስጥም ሁለት መንግስት አለ በማለት ቄሮን እንደ አንድ መንግስት አድርጎ ለማስቀመጥ መሞከሩም ሌላ ስህተት ብቻ ሳይሆን ሲመራቸው ለቆዩትም ወጣቶች በራሳቸው እንዲታበዩ እና ድርጅታቸውን ከመንግሥት እኩል አድርገው እንዲቆጥሩም የሚያበረታታ ነው። ለእነ አብይ አስተዳደርም ሆነ ክልሉን ለሚመሩት ለእነ አቶ ለማ ያለው ቦታ እና ግምትም አጃይብ የሚያስብል ነው። እራሱን ሽቅብ አውጥቶ ያለሱ ምሪት እና ድጋፍ አገሪቱ እና ፖለቲካው የትም ሊደርስ እንደማይችል እና ባፍጢሙ ሊደፋ እንደሚችል አድርጎም የሚያስብ መሆኑን ነው ንግግሮቹ የሚያሳብቁት።

ጃዋር ያለውን ትልቅ አቅም እና እውቀት በጥንቃቄ እና በስክነት ከተጠቀመበት ብዙ የሚደነቁ ነገሮችን ሊሰራ እና አገርንም ሊጠቅም ይችላል። በውስጡ እያቆጠቆጠች ያለችውን አንባገነናዊ ስሜት ግን ከወዲሁ በእንጭጩ ሊቀጫት ካልቻለ እያደር ግንድ ትሆናለች።

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.