Advertisements

‹‹በጣና ድርድር የለም፤የዉሸት ዘመን ማብቃት አለበት፤ጣና ችግር ዉስጥ ነዉ፡፡›› ዶ/ር አያሌዉ ወንዴ


‹‹በጣና ድርድር የለም፤የዉሸት ዘመን ማብቃት አለበት፤ጣና ችግር ዉስጥ ነዉ፡፡›› ዶር. አያሌዉ ወንዴ

ጣና አሁንም ሀኪም ፍለጋ ላይ ነው!

ጣናን የወረረዉ እንቦጭ አረም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና አረሙን ለማስወገድ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዶር. አያሌዉ ወንዴ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዉሃ ሳይንስ መምህር እና የሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም እና ባዮ ዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማህበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በመንግስት እና በሌሎች አካላት የሚቀርቡ የተሳሳቱ ሪፖርቶች ህዝቡን “እንቦጭ አረም እየጠፋ ነዉ” ወደሚል መዘናጋት ዉስጥ እያስገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “በጣና ድርድር የለም፤የዉሸት ዘመን ማብቃት አለበት፤ጣና ችግር ዉስጥ ነዉ” በማለትም አሳስበዋል፡፡ አረሙን በህብረተሰቡ ጉልበት፣ በመዋጮ በተገዙ ማሽኖች እና በሌሎች የምርምር ዉጤቶች ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የተጠበቀዉን ዉጤት ማግኘት አልተቻለም ብለዋል ዶክተር አያሌው፡፡

ይልቁንም አረሙ ከጎርጎራ-ጣና ቂርቆስ ድረስ ባሉ የሀይቁ ዳርቻዎች ተስፋፍቶ ይገኛል ነዉ ያሉት፡፡ ይህም በብዝሃ ህይወት፣ በአሳ ማስገር፣ በእንስሳት መኖ፣ በቱሪዝም እና በእርሻ ስራ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ነው ያስረዱት፡፡ የህብረተሰቡን ጊዜ እና ጉልበት በማባከን በምርታማነት ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
እንደ ዶር. አያሌዉ ገለጻ ለችግሩ እስካሁን የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግስት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጡ በመቆየታቸዉ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀርጾለት የማስወገድ ስራዉ በአግባቡ አልተከናወነም፡፡ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ እና በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የአመራሮች ተነሳሽነት ወሳኝ ነው፤ እስካሁን ባለው ጥረት ግን ትኩረታቸው ዝቅተኛ ነበር ብለዋል ዶር. አያሌዉ፡፡

የቆዩ የዕጽዋት ዝርያዎችን አረሙ በተወገደባቸዉ ስፍራዎች መትከል፣ ከልክ ያለፈ ግጦሽን ማስቀረት፣ አረም የማስወገድ ዘመቻውን በተከታታይነት በበጋ እና በክረምት ማከናወን እና ወደ ሀይቁ የሚለቀቁ ኬሚካሎችን መቀነስ እምቦጭን ለመቀነስ ዋና ዋናዎቹ መፍትሄዎች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡

ጉዳዩን የሚቆጣጠር የቱሪዘም፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች አካላትን ያሳተፈ ገለልተኛ እና ራሱን የቻለ ተቋም መመስረት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ 
ሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም እና ባዮ ዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን ማህበር ተፈጥሮ በቆየዉ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና በድርብርብ ቢሮክራሲዎች ምክንያት የተፈለገዉን ያህል መስራት አልቻለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን እንቦጭን ለማጥፋት ማሽን በመግዛት የራሱን ድርሻ ማበርከቱንም ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም ለጣና ደህንነት በጋራ ለመስራት ማቀዳቸዉን ዶር. አያሌዉ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ቢኒያም መስፍን – አብመድ

Advertisements

Zaggolenews. የዛጎል ዜና

Editor of zaggolenews.com contact editor - zaggolenews2016@gmail.com

You may also like...

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: