Advertisements

በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ያለው አለመግባባት በውይይት ተፈታ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር አገልግሎቱን በሚፈጽመው በማኅበረ ቅዱሳንና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት በውይይት መፈታቱ ተገለጸ፡፡

  • ዱስነታቸው፣ ከሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ጋራም ተወያዩ፤
  • ውይይቱን ያመቻቸው ለአባቶች ዕርቀ ሰላም የተንቀሳቀሰው ኮሚቴ ነው፤
  • ሒደቱ የሚጠናቀቅበት የራት ምሽት፣ በመንበረ ፓትርያርኩ ይካሔዳል፤
  • ለለውጥ ያላደለው የአ/አበባ ሀ/ስብከትስ፣መሰል ጥረት እየጠበቀ ይኾን?

ለሲኖዶሳዊው የአባቶች ዕርቀ ሰላም የተንቀሳቀሰው ኹለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ዓለም አቀፍ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ አባላት፣ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩንና የማኅበሩን የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት በተናጠል ያነጋገሩ ሲኾን፤ ትላንት ኀሙስ፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት፣ የማግባባት ሒደቱ የሚቋጭበት የጋራ የራት መርሐ ግብር በቅዱስነታቸው ጽ/ቤት እንደሚከናወን ታውቋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ 6ኛው ፓትርያርክ ኾነው ከመሠየማቸው በፊት በሊቀ ጳጳስነት በመሯቸው የሰሜን አሜሪካ እና የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አህጉረ ስብከት እንዲሁም ከተሾሙም በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ ለኾነ ጊዜ ከማኅበሩ አካላትና አባላት ጋራ መልካም የአባትና ልጅ ግንኙነት የነበራቸው ቢኾንም፣ በተለይም ከመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. መጨረሻ በኋላ ግንኙነቱ ሻክሮ ቆይቷል፡፡

ይህም ኾኖ የማኅበሩ አመራር፣ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርቦ በመወያየት መመሪያና ቡራኬ ለመቀበል በተደጋጋሚ ደጅ ቢጠናም ጥረቱ አልተሳካም፡፡ አለመግባባቱ ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ በብፁዓን አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በባለሥልጣናት አነጋጋሪነት አለመግባባቱን ለመፍታት መሞከሩን የጠቀሰው የማኅበሩ ጽ/ቤት፣ “ችግሩ በቀጥታ ተገናኝቶ ለመወያየት አለመቻል” እንደኾነና ይህም ያልተሳካው፣ “የተለየ ዓላማ ያላቸው ሰዎች በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ” እንደኾነ ገልጿል፡፡ ክፍተቶቹ፣ በማንኛውም ጊዜ መነጋገር ሲጀመር በቀላሉ ሊፈቱ እንደሚችሉ ማስታወቁን አውስቷል፡፡

በዕርቀ ሰላም ከተመለሰው ሲኖዶሳዊ አንድነት ጋራ ተያይዞ ውጤቱ ኹለንተናዊ መኾን እንዳለበት ያመነው ኮሚቴው፣ በኹለት ዙር ከቅዱስነታቸው ጋራ ባደረገው ውይይት የአለመግባባቱን መንሥኤ በመፈተሽ በማኅበሩ አገልግሎትና አሠራር ላይ ላነሧቸው ጥያቄዎች በቂ ምላሽና ማብራሪያ እንዲያገኙ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

በዋናነት ከፋይናንስና ንብረት አያያዝ አንጻር ያነሡት እንደሚገኝበትና “እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ ያለው የውጭ ኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የ2008 እና 2009 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ተደርጓል፤ ኤስድሮስን በተመለከተ የአክስዮን አሠራሩ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው፤ የማኅበረ ቅዱሳን ንብረት የቤተ ክርስቲያን እንደኾነና በአገልግሎት ላይ እስካለ ድረስ ብቻ እንደሚጠቀምበት በመተዳደርያ ደንቡ በሰፈረው መሠረት መተማመን ተደርሷል፤” ብለዋል የውይይቱ ምንጮች፡፡

መገናኘት ከሌለ በተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዙ የማይቀር ነው፤ ያሉት ምንጮቹ፣ አለመግባባቱ፣ ማኅበሩ በዋናው ማእከል ደረጃ ያቀዳቸውን የተለያዩ መርሐ ግብሮቹን በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አዳራሽ እንዳያካሒድ፣ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ እንዳይሳተፍ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቭዥን እንዳያገለግልና ቅዱስነታቸው በሚሰጧቸው መግለጫዎች ላይም ዘጋቢዎቹ እንዳይገኙ ዕንቅፋት ፈጥሮበት እንደቆየ አስረድተዋል፡፡ አሁን አለመግባባቱ በውይይት መፈታቱ፣ እነኚህን ዕንቅፋቶች ከማስወገድ ባሻገር፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች ከማኅበሩ አገልግሎት ጋራ በተገናኘ በየጊዜው ለሚነሡ ጭቅጭቆች እልባት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፤ ማኅበሩ፣ በኢኦተቤ ቴቪም የአየር ሰዓት እንዲሰጠው ጥያቄ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታ፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴው፣ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ከቅዱስነታቸው ጋራ በማገናኘት እንዲወያዩ አድርጓል፡፡በ“ዳንኤል ክብረት እይታዎች” የጡመራ መድረኩና በግል ፕሬሶች ዓምደኝነቱ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አመራር ላይ የሰነዘራቸው ሒሳዊ ጽሑፎች የአለመግባባቱ መንሥኤ የነበሩ ሲኾን፤ የማኅበሩን የ2008 ዓ.ም. ዐውደ ርእይ መታገድ መነሻ ያደረገውን ጽሑፍ ያተመውን ሰንደቅ ጋዜጣን ለክሥ አድርሶት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሒሳዊ ጽሑፎቹ ሳቢያ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በነገረ ቤተ ክርስቲያን ተመራማሪው ጦማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መካከል የሻከረው ግንኙነት በመግባባት ቢመለስም፣ ትችቱ የአመራሩን ድክመት መነሻ ያደረገ እንጅ ግላዊ አልነበረምና ዛሬም የመፍትሔ ያለህ የሚሉት ተቋማዊ ችግሮች የሚፈቱበት የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ስትራተጅያዊ ጥናቶች ተግባራዊነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ሩቅ ሳንሔድ፣ በፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት አዲስ አበባ፣ ከዋና ክፍል ሓላፊዎች ምደባ ጋራ ተያይዞ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ ተቃውሞ ይጠቀሳል፡፡ የቀድሞዎቹ 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች በሙስና ተግባራት፣ በአስተዳደር በደልና በአሠራር ጥሰት መወገዳቸው በተገለጸ ማግሥት፣በጥፋቱ የተነሣ መዝባሪ ግለሰብ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ተደርጎ ለሦስተኛ ጊዜ መመለሱና አጠቃላይ ምደባው ከጎጠኝነትና ጥቅመኝነት አሠራር የጸዳ አለመኾኑ፣ የለውጡን እውንነት ተስፋ አስቆራጭ አድርጎታል፡፡

ይህንንም ስጋት፣ ሰሞኑን ሊደረግ በታሰበው ከ30 በላይ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ዝውውር የታየው፣ የጎጠኝነት አድልዎና አስከፊ ጉቦኝነት አረጋግጧል፡፡ ደረጃን ያለመጠበቅ ጨምሮ እንደ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም፣ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል እና ብሥራተ ገብርኤል ባሉት ታላላቅ አድባራት ላይ ተፈጻሚ ከኾነም፣ ምእመናንን ለከፍተኛ ተቃውሞ የሚያነሣሣ የአርኣያነት፣ የተጠያቂነትና የግልጽነት ጉድለቶች እንዳሉበት ተጠቁሟል፤ ገና ለቋሚ ሲኖዶስ ሳይቀርብ እንጎዳበታለን የሚሉ አስተዳዳሪዎችን እያወዛገበና “ዘር ተኮር ጥቃት ተፈጽሞበታል” በሚሉ ብፁዓን አባቶች መካከልም ኃይለ ቃል እያለዋወጠ ይገኛል፡፡

ዕድሜያቸው ለጡረታ የደረሱትን በማሰናበት ያላግባብ ከሓላፊነታቸው ለተነሡና እንዲመለሱ ለተወሰነላቸው አስተዳዳሪዎች ቦታ ለማግኘት የታቀደበት ዝውውር ነው፤ ቢባልም፣የሀገረ ስብከቱን አስተዳደር ጉባኤ ሥልጣን ያላከበረ፣ የኹሉ አባትነታቸውን የዘነጉ ጳጳሳት ቀጥተኛና የእጅ አዙር ወገንተኛ ጫና ያረፈበት ይልቁንም በተስፈኛ/ተተኪ ደላሎች የተመራ የድብብቆሽ አካሔድ የተወጠነ ዝውውር እንደኾነ ታምኖበታል፡፡

በዕርቀ ሰላም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጠናከሩ በእጅጉ አስፈላጊ የኾነውን ያህል፣ ለተቋማዊ አመራሯ ኹለንተናዊ ችግሮች በተለይም በማሳያነት ለሚነሣው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የማያባራ ቀውስ መፍትሔ እንደኾነ የታመነበት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ስትራተጅያዊ ጥናት ተግባራዊነት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ ካልኾነ፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴውን ጣልቃ ገብነት እየጠበቀ ይኾን?

ሐራ ዘተዋሕዶ

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: