Advertisements

የኢንጂነር ስመኘው ባለቤት “ባዶ” ደብዳቤ”በአርምሞና በጸሎት ግዜዬን እንዳሳልፍ…”

በተለያዩ ሚዲያዎች የተለቀቀው የኢንጂነር ስመኘው ባለቤት ወ/ሮ እሙን ማዘንጊያ ደብዳቤ ” ቀለም ያረፈበት ግን ባዶ ነው” በማለት አንድ ሰው አወያየኝ። ከዛም ደጋግሜ አነበብኩት። በባለቤትዎ አሟሟትና ሞት በጣም ካዘኑት መካከል ነበርኩና ድብዳቤውን ካነበብኩ በሁዋላ ስሜት አጣሁበት። ማለቴ አዲስ ሃሳብ። ፍንጭ። በቃ አንድ ነገር!!

የሰውየው አስተያየት ብዙ ሊያነጋግሩ የሚችሉ ጉዳዮች ቢኖሩትም እርስዎ እንዳሉት ሃዘኑና የአሟሟቱ አይነት ልብን ይሰብራል። ይጎዳል። ከባድም ነው። ከህሊና በቀላሉ የሚወጣም አይደልም። መጽናናትን የሚያምኑት አምላክ የልብዎን ያህል ይስጥዎት እላለሁ። 

ስቀጥል የበርካቶችን ጥያቄዎች አነሳለሁ “ለመሆኑ በልቅሶው ላይ ተገኝተው ነበር ? ካልተገኙም ያልተገኙበትን ምክንያት ፍንጭ እንኳን ሊሰጡ በተገባ ነበር የሚል እምነት አለኝ። በደብዳቤው ላይ ” የስደትን አስከፊ ገጽታ የተረዳሁበት ክስተትና ዜና ነው ” የሚለው ሃረግ ወ/ሮ እሙን ወደ አገር ቤት መግባት ስለማይችሉ ነው ወይስ ምንድነው ስል እንደጠይቅ ያስገድደኛል። መጠየቅ ብቻ አይደለም አገር ቤት መግባት የማይችሉ ይሁን አይሁን ግልጽ አለመሆኑ በጥያቄ ላይ ጥያቄን የሚጭር ጉዳይም ይሆንብኝል። ሌላ የምርመራ ስራ የሚያስፈልገውም ነው። አገር ቤት መግባት የማይችሉ ከሆነ ማለቴ ነው። ዘመኑ የምህረትና የመደመር ሆኖ ሳለ ባለቤትዎን እንዳይሰናበቱ በር የዘጋብዎት ጉዳይ ምን ይሆን? እዚህ ላይ የግል ጉዳይ ከሆነ አያገባኝም። እርስዎም በዝምታዎ ሊገፉበት በተገባ ነበር።

የሶስት ልጆች እናት የሆኑና ባለቤትዎ ፈርሃ እግዚአብሄር እንዳላቸው አጠንክረው ገልጸዋል፣ በሌላ በኩል ስለ ህዳሴው ግድብ ጉዳይ የሚከታተሉት ልክ እንደኛው በቲቪ መግለጫ ሲሰጥ ብቻ ይመስል አንድም ነገር አለመተንፈስዎ ግር የሚል ነው። መቼም ባል ደክሞ ከበረሃ ሲመጣ ” ስራውስ እየሄደ ነው? እምን ደረሰ?…” በማለት ማውራት፣ በስራ የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን የመነጋገር ነገር፣ የስልክ ልውውጦችን የመስማት … ጉዳዮች በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የተለመዱ ጉዳዮች ናቸውና ባለቤትዎን የአገር ጀግና ስላደረጋቸው የህዳሴው ግድብ አንዲትም ሃረግ አለመተንፈስዎ ያስደነግጣል። ትክክልም አይመስልም። ጥያቄም ያጭራል።

ያም ሆኖ ግን እጥር ባለችው ባዶ ደብዳቤ የሚያውቁትን ለመናገር ቀጠሮ መያዝዎን ከግምት ውስጥ በማስገባት ብዙ ለማለት ብቸገርም፣ ባለቤትዎ ራሳቸውን አጥፍተዋል ብለው እንደማያምኑ ለመግለጽ ብቻ በጻፉት መልዕክት ውስጥ መቃወም የፈለጉት የፖሊስን የምርመራ ሪፖርት እንደሆነ ከባዶው ደብዳቤ የሚገኝ ብቸኛ ቁም ነገር መሆኑንን ሳልጠቅስ አላልፍም። እዚህ ላይ ላነሳልዎት የምፈልገው ፖሊስ ያነሳቸው ማስረጃዎች፣ የስልክ ልውውጦች ከእርስዎ ቤተሰብ፣ ከጸሃፊያቸው፣ ከስራ ባልደረቦቻቸው፣ ከቤትዎ ካሉ አንድ ሰራተኛ ጋር መሆኑ ተጠቁሟል። እነዚህን ሰዎች በሙሉ የማግኘትና የማጣራት፣ ከዛም እውነት ካልሆነ የማጋለጥ መብትዎ የተጠበቀ ሆኖ ሳለ፣ በደምሳሳው ብዥታ የሚፈጥርና በየትኛውም መድረክ መከርከሪያ የማይሆን ” ፈጣሪን” በማስረጃነት የመጥቀስ የተለመደው ባህላዊ አካሄድ መሆኑም በዚህ ዘመን ብዙም ሚዛን የሚያነሳ ሆኖ አልተሰማኝም። እንደውም እንደውም ከዚህን ያህል ቆይታ በሁዋላ ” ስለ ፈሪሃ አምላክ” ከማውራት ዝምታን ቢመርጡ በተሻለ ነበር። 

ባለቤትዎ የ”አገር ጀግና” ተብለው ኖረው የጀግና ሽኝት ላደረገላቸው ህዝብ ስለ ግድቡ እውነት አይነገሩትም ነበር። ግድቡ በዝርፊያና በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እያለ ደብቀውት ነበር። ብሄራዊ ንብረቴ ብሎ ከልጆቹ ጉርስ እየከለከለ የገበረለት ፕሮጀክት ምስጥ እየበላው እንደሆነ ቢያውቁም አልተነፈሱም ነበር። ምክንያታቸውን ባናውቀውም መፋረድ እንዳንችል ጉዳዩን ሁሉ ይዘውት ማለፋቸው አንድ የታሪክ ጠባሳ ነው። እውነት ለመናገር በዚህ መልኩ ጉዳዩ መጠናቀቁ እድሜ ልኬን ያመኛል። እርስዎ ባለቤትዎን፣ አገር ብሄራዊ ክራትዋን አጥታለች፣ በጠራራ ጸሃይ ተታላለች፣ ትውልድ ተቀልዶበታል። ፍትህ እንዲሰወርበት ሆኗል።

እርስዎም አሁን ምስጋና ላቀረቡለት ህዝብ እውነት የመናገርና የህዝቡን የተቆርቋሪነት፣ የአክባሪነት፣ እንዲሁም የፍትህ ጠያቂነት በሚመጥን ደረጃ ክብር ሰጥተው የጠራ መረጃ ለማድረስ የደፈሩ አለመሆኑ ተጨማሪ በሽታ ሆኖብኛል። ባለቤትዎ ራሳቸውን እንዳላጠፉ እምነት ካለዎት፣ ሌላውን መንገድ ሊያውቁ፣ ሊጠረጥሩ፣ ወይም ፍንጭ ሊሰጡና ምርመራውን ሊያግዙ በተገባ ነበር።በዚህ በአሁኑ የይቅርታ ዘመን ሰዎች ሁሉ ወደ አገራቸው እንዲገቡ መዝጊያው በተበረገደበት ወቅት መምጣት ካልቻሉ  እዛው ካናዳ ሆነው ቢሆንም።

ይህንን አድርገው ምርመራው ሃሰት ከሆነብዎ ለመከራከር፣ እርስዎ መከራከር ባይችሉም እርዳታ ሊጠይቁ በተገባም ነበር። ያም ሆነ ይህ ከርስዎ የ “ረዥም” ጊዜ ቆይታ አንጻር ፣ድምጽዎ መጥፋቱ ሌላ ጥያቄ ከሆነባቸው አክባሪዎቻችሁ ዜጎች ስሜት አኳያ የሰጡት መረጃ ” ባዶ” እንዲሉ ሆኖብኛል። ይህንን ስል በልጆችዎ፣ በርስዎም ሆነ በቤተሰባችሁ ዙሪያ የደረሰባችሁ ሃዘን ልብ የሚነካ መሆኑን በጠለቀ ስሜት እረዳዋለሁ። ከሁሉም በላይ ለልጆችዎ!! በቀጠሮው ቀን ለመገናኘት ያብቃን!! አምላክ ልቡና

ታዛቢ – አሰፈላጊ ከሆነ በገሃድ ልገኝ እችላለሁ

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ
“ባለቤቴ የራሱን ሕይወት ያጠፋል ለማለት እቸገራለሁ”
የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባለቤት ወ/ሮ እሙን እሙን ጌቴሁን ማዘንጊያ ከካናዳ ቶሮንቶ

የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ፤
ወ/ሮ እሙን ማዘንጊያ እባላለሁ፡፡
የአቶ ስመኘው በቀለ ባለቤትና የልጆቹ፤ የበእምነት ስመኝው፤ አሜን ስመኘውና ጽናት ስመኝው እናት ነኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቴ፤ በቶሮንቶ ካናዳ ነው፡፡

ዛሬ ከፊታችሁ ተገኝቼ ይህንን መግለጫ የምሰጥበት ምክንያት ከሁላችሁም የተሰወረ አይደለም፡፡ የባለቤቴን፤ የአቶ ስመኘው በቀለን ድንገተኛ ምስጢራዊ ሞት ይመለከታል፡፡

ሀሙስ፤ ሀምሌ 19 ቀን፤ 2010 ዓ.ም. ለኔና ለቤተሰቦቼ፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳዛኝ ቀን ነበር፡፡ በመገናኛ ብዙሀን የተለቀቀው፤ ባለቤቴ፤ ስመኝው በቀለ፤ ጠዋት በመስቅል አደባባይ፤ ሞቶ ተገኘ፤ የሚለው ዜና፤ ቅስም ሰባሪና አስደንጋጭ ነበር፡፡

ባለቤቴን እስከማውቀው ድረስ፤ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለው፤ ታታሪ፤ አገሩንና ቤተሰቡን የሚወድ፤ በምንም አይነት መልኩ ልጆቹን፤ አገሩንና ቤተሰቡን ጥሎ፤ የራሱን ሕይወት ያጠፋል ብዬ የማላስበው ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ባለቤቴ ራሱን አጠፋ ለማለት እቸገራለሁ፡፡

በዚህ በስደት በምኖርበት ካናዳ፤ የባለቤቴን ድንገተኛ ሞት በሰማሁ ግዜ፤ ሀዘኔ መሪር ሆኗል፡፡ የስደትን አስከፊ ገጽታ የተረዳሁበት ክስተትና ዜና ነው፡፡

ስለዚህም ላለፉት 4 ሳምንታት በአደባባይ ወጥቼ፤ ሀዘኔን መግለጽ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ማመስገን አልቻልኩም፡፡

በባለቤቴ ሞት መሪርና የማይቆርጥ ሀዘን ቢሰማኛም፤ የባለቤቴን ሞት ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየው ፍቅር፤ ድጋፍና፤ የሀዘን መግለጫ፤ መጽናኛ ሆኖኛል፡፡

ባለቤት ለሀገሩ ካለው ጽኑእ ፍቅር የተነሳ፤ የራሱንና የልጆቹን ህይወት በድሎ ለህዳሴው ግድብ ግንባታም ይሁን ለሌሎች ታላላቅ ግድቦች ግንባታ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ ሞቱን ተከትሎም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየው ፍቅር፤ ባለቤቴ እንዳልሞተና፤ በስራው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር አሳይቶኛል፡፡

በዚህ አሳዛኝና አስቸጋሪ ወቅት፤ ከጎኔ በመሆን ላጽናናችሁኝ፤ የቶሮንቶና አካባቢው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን፤ እንዲሁም በአገርቤት ልጆቼን የተንከባከባችሁልኝ ወገኖቼ፤ ፈጣሪ ብረድራችሁን ይክፈል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት፤ የባለቤቴን አሟሟት አጣርቶ፤ እውነታውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ወደፊት፤ ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ፤ የማውቀውንና የሚሰማኝን በሰፊው እስገልጽ ድረስ፤ ልክ እንደእስካሁኑ ሁሉ; በአርምሞና በጸሎት; ግዜዬን እንዳሳልፍ እንደምትፈቅዱልኝ አምናለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ወ/ሮ እሙን እሙን ጌቴሁን ማዘንጊያ ከካናዳ ቶሮንቶ

Advertisements

Zaggolenews. የዛጎል ዜና

Editor of zaggolenews.com contact editor - zaggolenews2016@gmail.com

You may also like...

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: