Advertisements

ከንቲባው የተነጠቋትን ከተማ ከአስራ አንድ ዓመት በሁዋላ አዩ፤ ለሳቸውና ለድርጅታቸው መጪው ጊዜ ቀላል ይሆንላቸው ይሆን?

አዲስ አበባ ስክራ ዋለች። አዲስ አበባ ስታዲየም ካፍ እስከ ገደፉ ጢቅ ብሎ፣ ጎዳናው ሁሉ በሰው ጎርፍ ተሞልቶ፣ ህዝብ ባንዲራውን በገሃድ አውጆ ዋለ። የቦንገር ልጅ በከንቲባነት እንዲመራት የተሰየመላትን ከተማ ዛሬ ረገጠ። እንባ የለም። ሃዘን አይታየም። ደስታ ብቻ።

እዚህ ጋር አንዳርጋቸው ጽጌ በተቃራኒው ይነሳሉ። ስሜታቸው ሲነካ ሰውነታቸው ይርዳል። እንባቸው ይወርዳል። ደማቸው ውስጥ ዘልቆ የገባው የፖለቲካ ብስለታቸው በዚህ ሥሥ ስሜታቸው ውስጥ አልፎ ሲወጣ ነብስና ልብን ይገዛሉ። ከሞት መንጋጋ መንጥቆ ያወጣቸው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሆድም እንዲህ ነው። ችግር ሲያይ ያነባል። ሰው መሆንን ለፖለቲከኞች ማን ነው የከለከላቸው? የኢትዮጵያ ሕዝብስ በእንዲህ ያሉ ሰፋሳፎች ለመመራት አይመጥንም ያለው አምን ነው? በስልክ አስተያየት ከሰጠን የጉዳዩ ባለቤት የተጠቀሰ ነው።

brhanu nega stadium.png

እናም ጅማታሙ አንዳርጋቸው ጽጌና ሳቂታው የነጋ ልጅ ውህደት ፈጥረው አርበኞች ግንቦት ሰባትን እዚህ አድርሰውታል። ገና ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ዶከተር ብርሃኑ እጅግ ደጋግመው የሚሉት ነገር ” አንድ መንፈስ ያስፈልገናል” የሚለውን ነው። ለውጡ ወደ ሰከነ መንፈስ መለውጥ ወይም መሸጋገር ግድ ይለዋል።

የቦንገር ልጅ ስለ ምርጫም አትጨነቁ ባይ ነው። አገር የማስከኑ ጉዳይ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ካለቀ ምርጫው ችግር አያመጣም። ዋናው ጉዳይ አሁን ስክኖ ማሰብና የሚዋሃደው ተዋህዶ፤ ልዩነት ቢኖርም በመቻቻል አገርን ማስቀደምና ለውጡ ያልጣማቸው ክፍሎችን ሴራ ማክሸፍ ቅድሚያ ስራ ነው። እናም በዚሁ ውድ ጉዳይ የዶከተር አብይን አመራር ለመደገፍ ድርጅታቸው ቁርጥ አቋም አለው።

ልክ እንደ አገር ውስጥ ሚኒስትር ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ብርሃኑ ነጋ፣ ያለፈው ስርዓት ላይመለስ መሸነቱን የገለጹት ልክ ኢህአዴግ እንደወደቀ አድርገው መሆኑ ከሞቅታው በሁዋላ ብዙዎችን አስገርሟል። አንዳርጋቸው ጽጌም በተመሳሳይ ባይሆንም በዘመኑ ቋንቋ “… ላይመለስ ወደ ምሽጉ ግብቷል” ምጸት ያለበት መልዕክት አሰምተዋል።

ከነበረው አስደሳች ድባብ ጋር ቀላል የዓመት በዓል ንግግር ተናግሮና መለያየት፣ በተለይም ” ቂም ይዞ የዴሞክራሲ ግንባታ የለም” ሲሉ ጠዋት ተናግረው ብዙም ሳይቆዩ በዲስኩራቸው ያስገቧቸው ጉዳዮች ከመደመር ሂሳቡ ጋር እ እ እ ያሰኛቸው አሉ። ያም ሆኖ ግን ዶክተር ብርሃኑ አንድ ትልቅ ፍንጭ ሰተዋል። ባለሙያዎች እንዳሉት በቅርቡ የፓርቲዎች ግርግር ይጠፋል። ይህ ደግሞ የዋናው ንጉስ አብይ ሃሳብ ነው። እናም ይህ ተመሳሳይ ሃሳብ ወዴት ያመራል? የሚለው ጉዳይ ” ምርጫውን ለህዝብ ቀላል የሚያደርገው የፕሬዚዴንሻል የመርጫ ስርዓት ነዋ” 

በዚሁ እሳቤ ከበዓሉ በሁዋላ ሸሚዛቸውን ጠቅልለው ወደ ዚሁ ጉዳይ የሚገቡት ዶከተር ብርሃኑ ከዚህ ጋር ይያያዝ አይያያዝ ግልጽ ባይሆንም በተቃዋሚ ፓርቲ ስም የቀደመውን የደህንነት መዋቅር ሲያግዙ የነበሩ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ ጠይቀዋል። አሳስበዋል። መክረዋል። 

እጅግ ድንቅ፣ ስልጡን፣ አጭርና፣ ሰው ሰው የሚሸት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ምክንትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ” የፊደል አባቴ” ሲሉ ለዶክተር ብርሃኑ ክብር ሰጥተዋል። እንዲህ ያለውን አይነት ክብር በአደባባይ መስጠት በኢህአዴግ ቋንቋ ያልተለመደ በመሆኑ ከንቲባው ተመስግነዋል። ከንቲባው ” ሃሎ አዲስ አበባ” ካሉ በሁዋላ ” እንኳን ወደ አገራችሁ፣ ወደ ከተማችሁ በሰላም መታችሁ” ሲሉም እንደ አንድ የከተማ መሪ፣ ብሎም ” ኢትዮጵያችንን” በማለት እንደ ዜጋ መልዕክት አስተላልፈዋል። አያይዘውም ” እርዱኝ፣ በሬ ክፍት ነው” ሲሉ መደመርን በፍቅር ጠይቀዋል። 

የሚከተሉት ነጥቦች ከዶክተር ብርሃኑ ንግግር የተለቀሙ ናቸው

‹‹የተጀመረውን ለውጥ ለመደገፍ ነው የመጣነው፡፡››
‹‹በአመለካከት ከምንስማማቸው ጋር እየተዋሃድን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር ይገባል፡፡›› ብርሀኑ ነጋ
‹‹ በኢሀዴግ ውስጥ ሆነው በሀገሪቱ ላይ የተደረገውን ቅጥ ያጣ ምዝበራ የተቃውሙ ግለሰቦች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡›

‹‹ የሰላም ጥሪውን የተቀበልነው አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ወደ ታገልንበት የመጨረሻ አላማ ለማድረስ ነው፡፡
‹‹ለውጡን ሊደናቅፉ የሚችሉ ሁኔታወችን በመለየት ለዘላቂ ሰላምና ለዲሞክራሲ ለመስራት ነው፡፡
‹‹ሀገር ለማረጋጋትና ዲሞክራሲ እንዲጎለብት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረን ለመስራት ነው፡፡››
‹‹ለምክንያታዊ ውይይትና ለክርክር ቅድሚያ ሰጥተን አላማችን ለማራመድ ነው፡፡››
‹‹በመምጣታችን ስጋት የገባቸው አንዳንድ አካላት እንዳሉ ተረድተናል፡፡››
‹‹ እኛ በመምጣታችን የከፋችሁ ካላችሁ ተደላድላችሁ ለመግዛት ስትሞክሩ የሞገትናችሁ አካላት ናችሁ፤ እኛ ከናንተ ጋር የምናወራርደው ምንም ቂም የለንም፡፡››
‹‹ሀገራችን ተጋግዘን ከችግሯ እናውጣት፤ ‹እኛ ካልገዛናት ይህች ሀገር ትበታተናለች!› ከሚል እሳቤ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡››
‹‹ ለስም ብቻ ተቃዋሚ ሆናችሁ ፣የስርዓቱ የደንነት ሀይሎች ሲጠቀሙባችሁ የነበራችሁ ሁሉ ስትጫወቱበት የነበረውን ሂደት እንጠላዋለን!፤ በጋራ ተሳስበን ለሀገራችን መስራት ይኖርብናል፡፡››

አገባባቸውን አስመልክቶ በስራው የነበረው የአማራ ክልል ሚዲያ ከታች ያለውን  ዘግቧል

ማለዳ አዲስ አበባ የገባው የአርበኞች ግንቦት 7 ልኡፀክ በድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የድርጅቱ ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመምራት ነው አዲስ አበባ የገባው። በድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራው አርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች እና አባላቶች አዲስ አበባ ሲገቡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም አርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች እና አባላቶች ደማቅ አቀባበል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። አርበኞች ግንቦት 7 እስከአሁን ለውጡ የሄደበትን ርቀት በማጤን በሀገር ውስጥ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል በማድረግ የተጀምረው የለውጥ ሂደት ወደ እውነተኛ ዘላቂ ለውጥ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ አለ የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ነው ወደ ሀገር የገባው።

የዛሬው የአቀባበል ስነስርዓትም ሀገራዊ አንድነትና መቀራረብ በሚያጎለብት መንገድ እንዲጠናቀቅ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የጠቀሱ ሲሆን ዕለቱ ፍቅር፣ መደጋገፍና መቻቻል የሚጎለብቱበት ጠላትነት፣ መራራቅንና መከፋፈል የሚሟሽሹበት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ከዚህ ቀደም በኤርትራ ያለውን ወታደራዊ ካምፕ መዝጋቱ የሚታወስ ነው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: