Advertisements

በአዲሱ ዓመት ለለውጥና ለተሻለ የሀገር ግንባታ የዜግነት ድርሻችንን ለማበርከት መዘጋጀት ይኖርብናል- ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ

በአዲሱ ዓመት ለለውጥና ለተሻለ የሀገር ግንባታ የዜግነት ድርሻችንን ለማበርከት መዘጋጀት ይኖርብናል አሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2011 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁም ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው፥ ኢትዮጵያ በረከቷ የበዛ እና ስሟም ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ሰፊ እና አስደናቂ ታሪክ ያላት ሀገር ነች ብለዋል።

እርስ በእርሳቸው የተቆራኙት ህዝቦቿም ያላቸው የጋራ ትውፊት፣ የታሪክ፣ የባህል እና የስነ ልቦና ትስስር የመልካም ገጽታችን ማንፀባረቂያ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሰዋዊ እና ቁሳዊ ሀብት ባለቤት ነች ያሉት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፥ በዚህ ደግሞ ሁሌም እንኮራለን፤ በኩራትም እንናገርለታለንም ብለዋል።

ይህን ሀብት ይዘን ግን ለምን ወደ ታላቅነታችን መመለስ አልቻልንም ብለን መመካከርና መነጋገራችንን እንቀጥላለን፤ ለመፍትሄውም ሌት ተቀን እየሰራን ሁሉም በእኩልነት ተጠቃሚ እንደሚሆኑበትን እርግጠኛ ነኝ ሲሉም ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፥ ልንሸኘው ጥቂት ሰዓታት በቀሩት 2010 ዓ.ም እስከ አጋማሽ ድረስ እንደ ሀገር እና ህዝብ በህልውናችን ላይ አደገኛ ሁኔታ የተፈጠረበት ነበረ ሲሉም አስታውሰዋል።

ይህንኑ ሀገራዊ አለመረጋጋትን ተከትሎም “ኢትዮጵያ አበቃላት” የሚለው የስጋት ዳመና ተገፎ አዲስ የለውጥ ድባብ መከሰቱም የሚታወስ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ።

ባለፉት ዓመታት ምንም እንኳ የሀገሪቱን ገጽታ በተሻለ መንገድ ሊለውጡ የሚችሉ የልማት ስራዎች ለመስራት ጥረት ቢደረግም ከደረጃ እና ከፍጥነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እየሰፉ መሄድ እና የመልካም አስተዳደር አለመስፈን ዜጎችን ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ከተዋል ነው ያሉት።

ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተነሱ ግጭቶች እና አመፆች የበርካታ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉንና የንብረት ውድመት ማስከተሉን አስታስውሰዋል።

ከዚህም ትልቅ ትምህርት ተገምኝቷል ያሉት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፥ የባከነውን ልማት እና ጊዜ በማካካስ ሁላችንም ለልማት ዘብ መቆም አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ አያይዘውም፥ ባለፉት 4 ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው አዲስ የለውጥ መንፈስ ያመጣቸው በርካታ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉም በመግለጫቸው አንስተዋል።

በፖለቲካ ልዩነቶች ተራርቀው የነበሩት የኢትዮጵያ ልጆች አሁን በአንድ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብለው መነጋገር መጀመራቸውም የሚበረታታ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

በዚህ መልኩ ተቀራርቦ መነጋገር መቻልም የሁላችንም የጋራ ቤት ስለሆነችው ኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞን ለማማተር ይጠቅማል ብለዋል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ እንደሚያስፈልግ የፀና እምነት ይዘን የየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደ አጥር እና የልዩነት ግንብ ሳናይ፤ በጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ሳናተኩር በሀገራዊ ትልቅ አጀናዳዎች ላይ መሆን አለበት ብለዋል።

አሁን እርስ በእርስ የምንፈላለገው ለሀገር እድገት እና ልማት መሰረት ለሆኑት ሰላም፣ ፍቅር፣ እና ለጋራ መፃኢ እድልእንጂ አንዱ ሌላውን ለመጫን አይደለም፤ መሆን የለበትም ሲሉም ተናግረዋል።

የአንድን ወገን አመለካከት በሌላው ላይ ገብድ ለመጫን መሞከር እና የአንድን ወገን የበላይነት ለማስፈን መጣጣር ሳይሆን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ሆነን የመቻቻል፣ የመደማመጥ እና የሰለጠነ ባህልን ማዳበር ስንጀምር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን በትክክለኛው ሀዲድ ውስጥ እንደሚገቡ በእርገጥነት መናገር ይቻላል ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፥ ትልልቅ ከሚባሉ ሀገራዊ አጀንዳዎች መካከል ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ልማትን ማረጋገጥ የኢትዮጵያውያንን ህልውና ማስቀጠል እንደመሆኑ፤ በአዲሱ ዓመት ለለውጥ እና ለተሻለ የሀገር ግንባታ የተነቃቃውን ህዝባዊ ፍላጎት በመያዝ ሁሉም የዜግነት ድርሻውን ለማበርከት መዘሃጀት ይኖርበታልም ብለዋል።

መጪው አዲስ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የብልፅግና፣ የደስታ እና የስኬት ዘመን እንዲሆንም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በራሳቸው ስም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

በሙለታ መንገሻ  fbc

Advertisements

Zaggolenews. የዛጎል ዜና

Editor of zaggolenews.com contact editor - zaggolenews2016@gmail.com

You may also like...

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: