Advertisements

ተረት ተረት፤ በኢትዮጵያ ያለው የ “ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝም” ነው

በኢትዮጵያ ያለው በሀግም በህግ መንፈስ (letter and spirit of the law) የቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝም ሳይሆን የጎሳ (ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች) ፌደራሊዝም ነው። ልዩነቱ ምንድነው?

የቋንቋ ፌደራሊዝም ማለት የተለያየ የቋንቋ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው የቋንቋ የቡድን መብት ይኖራቸዋል ማለት ነው። ለምሳሌ በኦሮሚያ የክልል ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኖ ማንም ኦርምኛ የሚናገር ሰው በቋንቋ ችሎታው እኩ መብት አላቸው። እንደ እንግዳ ወይንም «መጤ» አይቆጠሩም። የክልሉ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው ብሎ ሲሰየም ሁሉንም የቋንቋ ተናጋሪ ያካትተዋል። ስለዚህ የቋንቋ ፌደራሊዝም በዘር አይለይም። ማንም ቋንቋ እስከቻለ ቡድን ውስጥ አለ ማለት ነው። አግላይ አይደለም።

የጎሳ ፌደራሊዝም ግን ደም እና አጥንት የሚቆጥር ነው። በጎሳ ፌደራሊዝም ኦሮሚያ የኦሮሞ ተናጋሪ ክልል ሳይሆን የኦርሞ በደሙ ኦሮሞ የሆነ ሰው ክልል ነው። ኦሮሞ ያልሆነ ቋንቋውም ባህሉም «ኦሮሞ» ቢሆን የክልሉ ባለቤት አይደለም። ስለዚህ ይህ አሰራር በመሰረቱ አግላይ ነው። በሌላ ቋንቋ ዘረኛ ነው ማለት ይቻላል። አንድ ሰው ምንም ያህል ኦሮምኛ ቢችል በባህልም ሌላም ብዙ የተዋሃዶ ቢሆንም ኦሮሞ አይደለም ስለዚህ በኦሮሞ ክልል በዓድ ወይንም መጤ ነው።

እንደሚታዩት በሁለቱ በቋንቋ እና በጎሳ ፌደራሊዝም ታላቅ መሰረታዊ ልዩነት አለ። አንዱ ክፍት ነው ማንንም መስፈርት እስካሟለ ያቅፋል። ሌላው ግን ዝግ ነው ማንም ምንም ቢያደርግ ሊሳተፍ አይችልም። በመሰረቱ አግላይ ነው። ዘረኛ ነው የዘረኝነትን መንፈስም ተግባርም ይጋብዛል።

ለምሳሌ ጎሳ በመታወቅያ መደረጉ። እንደ የአፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍሪካ! ጎሳ በመታወቅያ የሚደረገው በጎሳ ለመለየት ነው። መረጃ ብቻ ሆኖ አይቀርም መለያ ይሆናል። ማለትም ዘረኝነትን ይጋብዛል። ለዚህ ነው ደቡብ አፍሪካ ይህን ስርዓት የነበረት ዘረኝነትን ለማራመድ ስለሚጠቅም። እና ምን ማለት ነው ኢትዮጵያ ይህን የዘረኝነት ስርዓት በገልበጧ?! የጎሳ ፌደራሊዝም ምን ያህል ዘረኝነትን እንደሚያራምድ እንዳሚያስፋፋ ነው የሚገልጸው። አንዴ የሀገሪቷ ዋና ህግ (ህገ መንግስቷ) ጎሰኝነትን መዋቀራዊ ካደረገች የዘረኝነት ስርዓቶች ይከተላሉ።

በዚህ ምክንያት ነው ዓለም ዙርያ የትም ሀገር የጎሳ ፌደራሊዝም ውየንም የጎሳ መብት (ከሞላ ጎደል) የሌለው። ማንም ሀገር በህገ መንግስቱ «ጎሳ»፤ «ብሄር ብሄረሰብ ህዝብ» አይነቱን ጽንሰ ሀሳብ አይጠቀምም። የቋንቋ ፌደራሊዝም፤ የቋንቋ የቡድን መብቶች፤ የክልል ቡድን መብቶች በህግ ደረጃ ያሰፈኑ ሀገራት በርካታ ናቸው። ግን ማንኛውም ህጉን በጎሳ የመሰረተ የለም።

ለዚህ ይህ የኢትዮጵያ የ1985 ህገ መንግስት ጸንፍ (radical) የያዘ በዓለም ዙርያ መችሄም ታይቶ የማይታወቅ እጅግ ሃላፊነት-ቢስ ሙከራ (experiment) ነው የተባለው። የትም ሀገር ያልተደረገ እና አስፈላጊ ያልሆነ ህገ መንግስት በኢትዮጵያ አይነቱ ደካማ ሀገር መጫኑ ታላቅ ልክስክስነት እና ህጻንነት ነበር። በዚህ ነውረኛ ሙከራ ምክንያት በርካታ ዜጎቻችን ተሰቃይተዋል።

ይህ አይነት የጎሳ ፌደራሊዝም የትም ሀገር የሌለው ምክንያት አለ! ህዝብን በጎሳ መከፋፈል ወይን መብት በጎሳ መመደብ ማለት ኩፍኛ ግጭትን መጋበዝ ማለት ነው። ዓለም ዙርያ የታወቀ ነገር ነው። አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ።

በካናዳ ኬቤክ የምትባል የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክፍለ ሀገር አለች (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/…/using-canada-to-und…)። ኬቤክ ለረዥም ዓመታት ከሌላው ካናዳ እለያየሁ እያለች ትሟገታለች ሁለት ጊዜም የመገንጠል ሬፈረንደም አካሄዳለች። ሁለቱም ጊዜ ህዝቡ ለጥቂት አንገንጠል አለ። የ ኬቤክ ቤርተኞች ግን ተጠንቅቀው የኛ ብሄርተኝነት የቋንቋ ነው እንጂ የጎሳ አይደለም ነው የሚሉት። ጎሳ አላቸው፤ 350 ዓመት በፊት ከፈረንሳይ ወደ ካናዳ የፈለሱት ፈረንሳዮች። ግን እኛ ኬቤክ ስንል ማንነታችን እንደ ቡድን መብት ይከበር ስንል በጎሳ ሳይሆን በቋንቋ ነው ብለው አስምረው ነው የሚናገሩት። በኬቤክ ማንም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ እኩል የኬቤክ ዜጋ ነው ብለው ጠንክረው ይናገራሉ። ልምንድነው ጉዳዩን እንዲህ የሚያሰምሩበት? የቋንቋ ቡድን ክፍት ነው እና «ዘረኛ» መባል አይቻልም። ከሞሮኮ የመጣ ፈረንሳይ ተናጋሪ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ኬቤክ የመጣ ፈረንሳይኛ የተማረ ወዘተ ሁሉም እኩል የኬቤክ ሰው ናቸው። በጎሳ ቢሆን ግን ፈረንጁ የድሮ የኬቤክ ሰው ብቻ ነው የክፍለ ሀገሩ ባለቤት የሚሆነው። ይህ ደግሞ ዘረኝነት ነው። የኬቤክ ብሄርተኞች «ዘረኞች» መባል እጅግ ስለሚፈሩ ያላቸውን መጤዎች ወደነሱ ማምጣትም ስለሚፈልጉ ሁልጊዜ የኛ ብሄርተኝነት የቋንቋ ነው ብለው ተጠንቅቀው ይገልጻሉ።

ሌሎችም በተለምዶ የሚጠቀሱት ሀገሮች እንደ ህንድ፤ ቤልጀም፤ ኤስፓኝ ወዘተ እንዲሁ ነው። የቡድን መብት በቋንቋ ወይንም በክፍለ ሀገር ነው የሚመሰረተው። ጎሳ፤ ብሄር፤ ብሄርተሰብ፤ ህዝብ ወዘተ ተጠንቅቆ ይወገዳል። ዘረኝነትን እና ግጭትን እንደሚጋበዝ የታወቀ ስለሆነ ነው። ዘረኝነትም ቢኖር ቢያንስ ዘረኛ ላለመባል ጥያቄአቸውም በቋንቋ ወይንም በክፍለ ሀገር ሽፋን ያቀርቡታል።

የዓለም ልምድ እንዲህ ሆኖ ኢህአዴግ ይህንን የሙከራ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ መጫኑ የኛ ልሂቃን የጸንፈኝነት ዝንባሌን በደምብ ያሻያል። ትንሽ የቀለም ትምህርት ስንማር ቀንደኛ ጸንፈኛ መሆን የእውቀታችን መለክያ ይመስላችን ይሆን አላውቅም። በተማሪ ንቅናቄው ይህ በደምብ ታይቷል። በህወሓትም እንዲሁ። በኢህአፓም። ዛሬም በተለያዩ ፖለቲከኞች እናየዋለን። የችግር መፍትሄው ቀላላእና ሚዛናዊ ለዘብተኛ ፊት ለፊት እያለ ጸንፈ የያዘ ውስብስብ የሆነ መፍትሄ (ማባባሻ) ይፈለጋል። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ጉዳይ እንዲህ ነበር።

ዛሬ ሀገ መንግስቱ «ብሄር፤ ብሄረሰቦች፤ ህዝቦች» የሚለውን አውጥቶ የቋንቋ ፌደራሊዝም እንዲሆን አስፈላጊ ለውጦች ቢደረግ ብቻ ታላቅ መሻሻያ ይሆናል። ለነ ይህ በቂ ባይሆንም ታላቅ ታላቅ ማሻሻያ ነው የሚሆነው። ህዝባችን እና መሪዎቻችን ይህን ለማድረግ ያብቃን።

ስለዚህ ጉዳይ አንዳርጋቸው ጽጌ ያለውን ከዚህ ቪዲዮ ብትመለከቱ ጥሩ ይመስለኛል፤

Ethimedia

Advertisements


Categories: opinion/ ምልከታ

Tags:

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: