እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም ያሸጋገረን – ጌታቸው ኃይሌ

እንኳን ከዘመነ ማርቆስ (2010 ዓ. ም.) ወደ ዘመነ ሉቃስ (2011ዓ.ም.) በሰላም ያሸጋገረን። አዲሱን ዘመን ኢትዮጵያውያን በረኀብ የሚሞቱበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማቆም የምንጀምርበት ጊዜ ያድርግልን።

የዘንድሮውን ዘመነ ማርቆስ የምናስታውሰው ከወያኔ የጭቆናና ጌትነት ነፃ የወጣንበት ዓመት እያልን ነው። ወያኔዎችና በወያኔ አገዛዝ ተጠቃሚዎችም፥ ከጌትነት መውረዳቸው ለጊዜው ቅር ቢላቸውም፥ የኋላ ኋላ ወንድማማችነት/እትማማችነት እንደሚበልጥ እየተረዱት ይሄዳሉ። ምክንያቱም፥ ጌትነት የቀማኛነት በሽታ ያሲዛል። ወያኔዎችና በወያኔ አገዛዝ ተጠቃሚዎችም በጌትነታቸው ዘመን ይህ በሽታና በሌሎች ላይ መንቀባረር እንደለከፋቸው ውስጥ-ውስጡንም ውጭ-ውጭውንም ይወራባቸዋል። እውነት ከሆነ፥ ሌባ ከመሆንና ከመባል ወጥቶ ንጹሕ ከመሆን የበለጠ ደስታ የለም። ተደስተንላችኋል፥ ደስ ይበላችሁ። ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የምትክሷት ለውጡን ከማንም ቀድማችሁ በሙሉ ልብ ስትደግፉና ስትረዱ ነው።

ያለፈው ታሪካችን ነው። የሚመጣው ወራሲዎቻችንን የሚያኮራ ግዳጃችንን የምንፈጽምበት ነው።

እኛና ምዕራባውያን የዘመን አቈጣጠር መንሥኤያችን አንድ ሆኖ ሳለ (ሁለታችንም ከልደተ ክርስቶስ እንነሣለን) ልዩነቶች ለምን እንደተፈጠሩ የታወቀ ቢሆንም፥ መግለጫው በየዓመቱ እመስከረም መባቻ ላይ ይሰጣል። የኛ Julian Calendar፥ የነሱ Gregorian Calendar ይባላሉ። በኛ ዓመተ ምሕረት (ዓ. ም.) እና በነሱ ዓመተ እግዚእ (ዓ. እ. = AD) መካክል ሁለት ልዩነት አሉ። ግን ሁለት መሆናቸውን ባለመገንዘብ የአንዱን ልዩነት ከሌላው ጋር እናምታታዋለን። አንደኛው ልዩነት የ7/8 ዓመት ልዩነት ነው። ስለዚህ፥ ዛሬ በኛ 2011 ዓ. ም. በነሱ 2018 ዓ. እ. ነው። ይህ ልዩነት የተፈጠረው ዘመን ቈጠራ ሲጀመር ምዕራባያን 7/8 ዓመት  ቀደም  ብለው  ወይም እኛ 7/8 ዓመት ዘግየት ብለን ስለጀመርን ነው። ሆኖም፥ ይኼ ልዩነት በJulian Calendar እና በGregorian Calendar መካከል ያለውን ልዩነት የሚያመለክት አይደለም፤ አንሳሳት። በJulian Calendar እና በGregorian Calendar መካከል ያለውን ልዩነት የሚያመለክተው ሁለተኛው ልዩነት ነው። እሱውም፥ ወር ስንጀምር በ10/11 ቀን መለያየታችንን ነው። እስከ1582 ዓ. እ. (AD) ድረስ ሁላችንም ወር የምንጀምረው በአንድ ቀን ነበረ። በ1582 ዓ. እ. (AD) ሊቃውንቱ በዘመናት ተቈርጠው የቀሩ ደቂቃዎችንና ዳግሚቶችን (minutes and seconds) ቢሰበስቧቸው 10 ቀን ወጣቸው። በዚያን ዘመን የገዛው የሮሙ ፖፕ ግሪጎሪ 10 ቀን የወጣቸውን የተቈረጡን ደቂቃዎችና ዳግሚቶች አምጥቶ ደመራቸው።

የተቈረጡበት ምክንያት በብዙ ቦታ በሰፊው ተተችቷል። ለማስታወስ ያህል፥ እንዲህ ነው፤ አንድ ሙሉ ዓመት 365 ዕለት፥ ከ5 ሰዓት፥ ከ48 ደቂቃ፥ ከ46 ዳግሚት (seconds) ነው። ተመራማሪው ለአያያዥ የሚሻለው 48ን ደቂቃና 46 ዳግሚት ገድፎ ፥ ዓመቱን 365 ዕለት፥ ከ5 ሰዓት ብቻ ማድረግ መሆኑን ወሰነ።

ይህ ውሳኔ በየዓመቱ መስከረም ሳይጠባ ቀደም ብሎ፥ መስከረም ጠባ ማለትን አስከተለ። የፖፕ ግሪጎሪ ሊቃውንት እስከነሱ ዘመን ድረስ በየዓመቱ የተገደፉትን ደቂቃዎችና ዳግሚቶች ወደኋላ ሄደው ቢሰበስቧቸው 10 ቀን እንደወጣቸው ነገሩት። እሱም እነኚህን የተሰበሰቡትን ቀናት ደምራ ወሩን እንድትጀምር ቤተ ክርስቲያናቸውን አዘዘ፤ ታዘዘች። እኛ ባለንበት ረጋን። ለምሳሌ፥ ዘንድሮ እኛ መስከረምን የጀመርነው፥ እነሱ ሰፕቴምበርን 10 ቀን ቀድመውን ከጀመሩ በኋላ፥ በ11ኛው ቀን ነው።

በየዋሆቹ ዘመን የዘመን ቈጠራ ችግር አልነበረም። ሲነጋ ጎበዞቹ አደን አደና ወይም ፍሬ ለቀማ ጫካ ውስጥ ውለው ሲመሽ ያገኙትን ይዘው ወደየ ዋሻቸው ይመለሱ ነበር። የዘመን ቈጠራ አስፈላጊነት የታየው የሥልጣኔ (በተለይም የእርሻ) ባህል መዳበር ሲጀምር ነው። እርሻ የአየርን ሁኔታ ተከትሎ የሚሄድ ሥልጣኔ ነው። መቸ ነው ክረምት የሚገባው፥ ዝናም የሚዘንመው? መቸ ነው የሚዘራው፥ የሚታጨደው፥ የሚሰበሰበው?

ደግነቱ፥ የአየሩ ጠባይ የሚለዋወጠው ከሞላ ጐደል በተወሰነ ጊዜ ነው። ገበሬዎቹ ማወቅ ያለባቸው እነዚያ የመለዋወጫ ጊዜዎች መቸ እንደሆኑ ነው። ሊቃውንቱ እንደደረሱበት፥ የአየር ልውውጦች ደርሰው የሚፈጸሙት በ365 ዕለት፥ ከ5 ሰዓት፥ ከ48 ደቂቃ፥ ከ46 ዳግሚት (seconds) ጊዜ ውስጥ ነው። ይኸንን ጊዜ “ሙሉ ዓመት” አሉት። ሙሉ ዓመት ተመላልሶ ስለሚመጣ፥ “ዓውደ ዓመት” (የዓመት ዙር) አሉት። መስከረም 1 ቀንን “ርእሰ ዓውደ ዓመት” (የሙሉ ዓመት ቁንጮ) አሉት።

አንድ ሙሉ ዓመት የሚባለው አንድ የ365 ዕለት፥ ከ5 ሰዓት፥ ከ48 ደቂቃ፥ ከ46 ዳግሚት (seconds) ዙር አልፎ የሚቀጥለው 365 ዕለት፥ ከ5 ሰዓት፥ ከ48 ደቂቃ፥ ከ46 ዳግሚት (seconds) ሲጀምር ነው። እውነታው እንዲህ ከሆነ፥ አዲሱን ዓመት የምንጀምረው እኩለ ሌሊት ላይ መሆኑ ለምቾት ነው እንጂ ትክክል ሆኖ አይደለም። ትክክሉ 46ኛዋ ዳግሚት (seconds)  ሞልታ ሌላው ዓውደ ዓመት  ሲጀምር ነው።

የዳበረው የሥልጣኔ ባህል ግብርና ብቻ አልነበረም። ከዓመት ባነሰ ጊዜ የሚፈጸሙ ብዙ ጕዳዮች አሉ። ለምሳሌ፥ ሰዎች ለመቃጠር ሲፈልጉ፥ “ነገ፥ ከነገ ወዲያ”፥ ያለፈውን ነገር ለማንሣት፥ ታሪክ ለመመዝገብም ሆነ ለልጆች ለማስተላለፍ  ሲፈልጉ፥ “ትናንት፥ ከትናን ወዲያ” የሚባሉት አነጋገሮች አይበቁም። ብዙ ዕለታትን መጠቈም አስፈለገ። ምርምሩ ቀጠለ። መጀመሪያ ዕለቱን ፀሓይ ወሰነችላቸው። ፀሓይ የምትታይበትን ጊዜ “ቀን”፥ የማትታይበትን ጊዜ “ሌሊት”፥ ሁለቱን በአንድነት “ዕለት” አሏቸው። ዕለት እየተመላለሰ ስለሚመጣ፥ “ዓውደ ዕለት” አሉት።

የሳምንትን ዓውድ ያለ አንዳች የተፈጥሮ ማስረጃ ሰባት ዕለት አድርገው ፈጥረው፥ ለያንዳንዱ ዕለት የመሰላቸውን ስም ሰጡት። እኛ፥ በግዕዝ “እሑድ”(አንደኛ)፥ “ሰኑይ” (ሁለተኛ)፥ “ሠሉስ” (ሦስተኛ)፥ “ረቡዕ” (አራተኛ)፥ “ሐሙስ” (አምስተኛ)፥ “ዓርብ” (ምሽት)፥ “ሰንበት” (ዕረፍት፥ቅዳሜን) ቀን አልናቸው። “ሰኑይ”፥ “ዓርብ”፥ “ሰንበት” የሚባሉትን ቃላት ለሦስቱ ቀኖች መጠሪያ ማድረጋችንና ሳምንቱን ሰባት ቀን ማድረጋችን ባሕረ ሐሳባችን ከዕብራውያን ባሕረ ሐሳብ ጋር ግንኙነት እንዳለው

ይመሰክራሉ። ምክንያቱም፥ “ሰኑይ” ዕብራይስጥ እንጂ ግዕዝ አይደለም፤“ዓርብ” ለዕብራውያን የሳምንቱ ምሽት (ማለቂያ)፥ “ሰንበት” ዕረፍታቸው ነው። “ሰባት” ዓለም ከነገሠሡ ተፈጥሮ እንዳለቀና ፈጣሪ ከፈጠራው እንዳረፈ የሚመሰክረው፥ የኛም የሆነው፥ የነሱ መጽሐፍ ነው። ግን እነዚህን የዕብራይስጥ ስሞች የወሰድነው ብሉይ ኪዳኑን ወደግዕዝ የተረጐንም ጊዜ አይደለም። እሱን የተረጐምነው ወደግሪክ ከተተረጐመው መጽሐፍ ነው።

ወርን ለመለካት ሁለት መንገድ ነበራቸው። የሴቶች አበባ በየስንት ቀኑ ነው የሚመጣው? ጨረቃ (ወርኅ) በየስንት ቀኑ ነው የምትወለደው? እነዚህንና ምናልባትም ሌሎች ነገሮች ከእሳቤ አስገብተው ነበር። ጨረቃ የምትወለደው አንድ ጊዜ በ29፥ ሌላ ጊዜ በ30 ቀን ቢሆንም፥ የጨረቃን መመላለስ የተሻለ መለኪያ ሆኖ አገኙት። ወር በጨረቃ መጠራቱ ስለዚህ ነው። ወር/ወርኅ ማለት ጨረቃ ማለት ነው።

2010 ዓመተ ምሕረት ከወያኔ የጭቈና አገዛዝ ነፃ የወጣንበትና አፈ ልጓማችንን የተፈታንበት ያህል፥

2011ዓመተ ምሕረት በክልል ከመከፋፈል የምንድንበት ዘመን ይሁንልን። “ኢትዮጵያ ያላት አንድ ድምበር ብቻ ነው፤ ያውም ከጎረ ቤት አገሮች ጋር ብቻ ነው። በውስጥ ያለው ያስተዳደር ወሰን ነው” ብንባልም የአስተዳደሩ ወሰን የጎረቤት ድምበርን ያህል ሠርቶብናል።

የታደሱት የፖለቲካ መሪዎቻችን በሀገሪቷ ላይ የማይናወጥ መሠረት የያዘ ፍትሕ ርትዕ ያነግሡ ዘንድ ተሐድሷቸውን ያጽናልን። ሙሉ ጤናቸውን ይጠብቅልን። ለለውጡ አስተዋፅኦ ያደረጉ ጸሐፊዎችና ጋዜጠኞች፥ በአካል ፊት ለፊት የተጋደሉ ጀግኖች ሁሉ ባለውለታችንና ሁሌም ጀግኖቻችን ናቸው።

የንጹሕ ምርጫ ውጤት ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝብ እንደሚያሳዝን ተረድተን፥ የምንመኘው ዲሞክራሲ ሲነግሥ፥ “ለዘላለም ንገሥ” የምንልበት ሰፊ ሆድ ይስጠን።

አሜሪካን ሁል ጊዜም በዓለም ፊት የምትከበርበት ሥራ እንድትሠራ ያድርጋት። የዓለምን ሰላም ዘላቂ ያድርግልን።

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.