ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ለአዲሱ ዓመት የስተላለፉት መልዕክት!

ለመላው አማራ እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ!

ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ

ከሁሉም አስቀድሜ ከእስር ቤትም ከተለያየ ቦታም የነበራችሁ ውድ የአማራ ልጆችና ኢትዮጵያውያን በዓሉን ለማክበር ስለቻልን እግዚያብሔር ይመስገን! በመቀጠልም ተገናኝተን በነፃነት በዓል እንድናከብር ለአስቻሉን ሰማዕታት ክብር ምስጋ ይገባቸዋል።

ወቅቱ የተለያየ ነገር የተቀላቀለበት ነው። ለውጡ መልካም ነገሮች እንዳሉት ሁሉ ያልጠሩም ነገሮች አሉት። በተለይ ለአማራ ሕዝብ ወቅቱ በጥሞና መታየት ያለበት ነው። በሲቪክ ማህበር ስም፣ በፖለቲከኛም ስም የሚመጡ ብዙ ናቸው። እነዚህ አካላት ከአማራው ጥቅምና ጥያቄ አንፃር መታየት አለባቸው። የፖለቲካ ቁማርተኛውን እና እውነተኛውን ተቋም፣ እውነተኛውን አንድነት አካል መለየት አለብን። ከነፈሰው ጋር መንፈስ አያስፈልግም።

አንድነትን እንደግፋለን፣ አንድነትን የምንደግፈው ግነ በምክንያት ነው። አንድነቱንም፣ መደመሩንም የምንደግፈው የአማራውን ጥያቄ እውቅና የሚሰጥ እና የሚመልስ ከሆነ ነው።

ከውጭ የቆዩ፣ በሀገር ውስጥ የተቋቋሙ የአማራ ተቆርቋሪ ድርጅቶች አሉ። አማራ ጥያቄውን ለማቅረብ ብዙ ተቋም አያስፈልገውም። ጠንካራ ተቋም ያስፈልገዋል። ወደፌደራል መንግስቱ፣ ወደ አራት ኪሎ ስንሄድ የምንጠይቀው የአንድ አማራን ጥያቄ ነው። የአንድ አማራን ጥያቄ ለማቅረብ፣ ወደ ፌደራል መንግስቱ፣ ወደ አራት ኪሎም ስንሄድ በአራት ወይም በአምስት አቅጣጫ መጓዝ አይጠበቅብንም። የለብንም። የአንድ አማራን ጥያቄ ለማቅረብ ተቀራርበን ተገናኝተን፣ ተወያይተን፣ መስማማትና መጠንከር ነው የሚገባን። ከመራራቅ ስለ ሕዝባችን ተቀረርበን መስራት አለብን። የአማራ የተበጣጠሰ አደረጃጀት የሚጠቅመው ለሕዝቡ ሳይሆን ለጠላቶች ነው።

አማራ አሁንም መታሰሩ አልቀረለትም። ግድያው አልቀረለትም፣ መፈናቀሉም፣ መበደሉም አልቀረለትም። ዛሬም በወሎ በማንነታቸው እየተገደሉ ነው፣ እየታሰሩ ነው። በወልቃይትና በራያ አማራ በማንነቱ ምክንያት ብዙ በደል እየተፈፀመበት ነው። ይህን ማስቀረት የምንችለው ተቀራርበን፣ በጋራ ስንሰራ ነው። ለአማራው ዘላቂ ሰላምና ጥቅም አብረን፣ ተስማምተን መስራት አለብን።

የአማራውን መደራጀት ሌሎች ብሔሮችም፣ በማንነት ያልተደራጁም ሊቀበሉት ይገባል። እንደራጅ ስንል ራሳችን ለማሰከበር እንጅ ሌሎችን ለመጉዳት አይደለም። ሌሎቹም የአማራን መደራጀት መደገፍ አለባቸው። በማንነት መደራጀት አሁን ባለው ሕገ መንግስት ላይ የተቀመጠና፣ ሌሎች እየተጠቀሙበት መሆኑም መታወቅ አለበት። ሌሎች በማንነት ተደራጅተዋል። እኛ ሌሎች በማንነት ሲደራጁ እንደደገፍን ሁሉ ሌሎቹም የአማራውን መደራጀት ሊያምኑበት ይገባል። ሀገር የጋራ ነች። ሌሎች የራሳቸውን ችግር ለመፍታት እንደተደራጁት፣ አማራም በራሱ ላይ የተደቀነበትን ችግር በመፍታት ለሀገሩም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ መደገፍ አለበት።

ይህን አዲስ አመት እንድናከበር የአማራ ልጆች መስዋዕትነት ከፍለዋል። የኦሮሞ፣ የኢትዮጵያ ልጆች ዋጋ ከፍለዋል። ይህን አዲስ አመት ከእስከዛሬው በተሻለ በነፃነት እንድናከብር መስዋዕትነት የከፈሉት ወንድምና እህቶቻችን ቤተሰቦች ለእኛ ሲሉ የተሰውትን ሰማዕታትን እያሰቡ መቆዘምና ማዘን የለባቸውም። መኩራት ይገባቸዋል። ለዚህ ለውጥ ሲባል የተሰውት ሰማዕታት ቤተሰቦችን ከጎናቸው መሆን ይገባናል። የአማራ ጥያቄዎች እስኪመለሱ ድረስ በሰከነ መልኩ እየተነጋገርን፣ ተባብረን መስራት አለብን!

መጭው ዘመን ለመላው አማራም ሕዝብ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የመተባበርና የስኬት እንዲሆን ምኞቴን እገልፃለሁ።

ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ

(ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እኔ እና ጓደኞቼ ዛሬ መስከረም 1/2011 ዓም ወደቤቱ እንኳን አደረሰህ ለማለት በሄድንበት ወቅት ለሕዝብ እንድናደርስለት ያስተላለፈው መልዕክት ነው)

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.