Advertisements

ሕዝብ ነጻ ያወጣቸው ” ታጋዮች “ቀረርቶ ወዴት -ወደ ቀድሞ መመልስ?

አሁን አሁን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ በየጎዳናው ላይ ለዛውን በሳተ መልኩ የሚስተዋሉ ድርጊቶች ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች እየሆነ ነው። ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም ትግል ካደረገ በሁዋላ፣ ለውጡን በሰላማዊ መንገድ ማስኬድ ሲገባ ከየአቅጣጫው የሚታየው ጋጋታና አጓጉል ድርጊት ሰላማዊውን ህዝብ እያመሰ ነው።

አንዳንድ መሪዎች ከፕሮፓጋንዳ ያልዘለለ ትግል ሲያደርጉ መቆየታቸው የማይታወቅ ይመስል የድል አርበኛ መስለው ሲያቅራሩ ማየትና መስማት ውሎ አደሮ የሚገለጽ ቢሆንም አሁንም ሰላም ከማናጋት የዘለለ ትርፍ እንደማይኖረው ስጋት አለ። አንዳንዶቹም ቢሆኑ ዓላማቸውን ወደ ህዝብ አምጥተው የሚጫወቱበት መድረክ እያለ ደጋፊዎቻቸው መረን ሲለቁ በኩራት የሚመለከቱ ናቸው። ሲደመሩ አስር ሺህ የማይሞላ ሰራዊት መገንባት ያልቻሉ፣ ዛሬ በህዝብ ትግል ከተማ ገብተው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ እየታየ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር ምን ፍለጋ እንደሆነም ግልጽ አይደለም። የቀድሞውን መቀጥቀጥ፣ መወገር፣ መታሰርና አልፎ ሲሄድም መቀንደብን ከመመጨት በቀር!!

ቄሮን የሚመሩ ሃይሎች ቄሮን ስነ ስርዓት አሲዘው መምራት ካልቻሉ አገር ቤት ግብተው ሲንጫጩበን ቢውሉና ቢያድሩ፣ በየክልሉ እየሄዱ ቢሰብኩ ምን ጥቅም አለው፤ በስመ አማራ ጽንፍ ይዘው ሌላውን በሚያበሳጭ መልኩ ንግግር ማድረግና አጉል ጀግና ሆኖ ትዕዛዝ ማስተላለፍ አሁን ለተጀመረው ለውጥ ምን እንደሚፈይድ ግራ የሚያጋባ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች እንዲሁም አክቲቪስት የሚባሉት ሰዎች መቼ እንደሚሰክኑ መገመትም አልተቻለም። ሁሉም ጀግና ልሁን ባይ ሆነና ነገሩ ሁሉ ተራ ጭፈራ መስሎ ቁጭ አለ።

በኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ፕሮግራም ዶክተር ጸጋዬ አራርስን ጨምረው የሚያስተላልፉት የእናፈርሳለን፣ የእናጠፋለን፣ የእንገለብጣለን ቅስቀሳ መነሻው ግልጽ አይደለም። ማንን እነደሚያስፈራሩ ገሃድ አያደርጉትም። ጸጋዬ የትኛውን የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚውክል ባይታወቅም በኦሮሞ ህዝብ ስም ምን እንደሚጠይቅ፣ ጥያቄው የት ደርሶ እንደሚቆም፣ ለመረዳት ያዳግታል። ጥያቄም ሆነ ፍላጎት ካለ በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር የክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት በር ክፍት ሆኖ ሳለ ” አሳደህ በለው” ዘመቻ ” እዚህም ጋር እሳት አለ” እንዲሉ መሆኑ አልገባውም። ይህ በግል ብቻ ሳይሆን በድርጅት ደረጃም አጉል ” ውሮ ወሸባዬ” የሚዘፈንላቸው ጋርም ተመሳሳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት “ሕዝብ ነጻ ያወጣቸው” ሃይሎች ደርሰው አሸንፈውና መንግስት ገልብጠው የገቡ ይመስል ያለ አንዳች ሃፍረት ” ዘራፍ” ሲሉ ይህ በስሜት የሚነጉደው ደጋፊ ምን ሊል እንደሚችል መገመት አያዳግትም። አሁን ተወደደም ተጠላም ይህ በመንጋ አገርን እየረበሸ ያለ አካሄድ ድርጅቶች ሃላፊነት ወስደው እንዲያስቆሙ፣ አለያም መሪ የሌለው የብጥብጥ መንጋ ከሆነ አስፈላጊው  ስርዓትን የማስከበር እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ነጻነት ማለት ሌላውን ማስፈራርት፣ መግደል፣ መፈንከት እና ንብረት ማውደም አይደልምና።

ሰሞኑንን የባንዲራ ጉዳይ የፈጠረው ቀውስ አግባብነት የሌለውና በህግ ገደብ ሊበጅለት የሚገባው ነው። የፌደራል የክልል እና የድርጅት ባንዲራ የሚታዩበት ህጋዊ አግባብ ሊከበርም ይገባል። ይህንን አስመልክቶ በመንግስት ደረጃ ፍጹም የሆነ ቸልተኛነት እንዳለ ቢተችም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ አስተያየት ሰጥተዋል። 

“ስለ ምልክት ሳይሆን ስለሀገር ከልብ እናስብ! ሀገር ካለች ባንዲራ መስቀል እና ሀዉልት መገንባት አይከብድም! ሀገር ከሌለ ግን ባንዲራ ብቻዉን ትርጉም የለዉም! አሁን ሊቢያ ወይም የመን ላይ ባንዲራ መያዝ ወይም ሐዉልት መትከል ምን ያደርጋል? ችግራችን በባንዲራ ወይም በሐዉልት አይፈታም። የግጭት ነጋዴዎችን ሴራ እናክሽፍ። ጆሮ ያለዉ ይስማ ” ሲሉ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆነው አቶ ታዬ ደንደአ አስጠንቅቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት ቅድሚያ የሚሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች እያሉ በባንዲራ መጋጨት ፍጹም ድንቁርና ነው። አንድ አገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እያቀናች ባለበት ሁኔታ ነገሮችን ወደ መድረክ አምጥቶ መወያየት ሲቻል በረባ ባልረባው መጋደል፣ መፈናከት፣ ንብረት ማውደም ፍጹም የሚዘገንን የ፪፩ኛው ክፍለ ዘመን የወደቀ አመለካከት ነው። ይህ በተራ ሆያሆዬ የሚነዳው መንጋ ወይ እንመራዋለን በሚሉት ድርጅቶች፣ ባለቤት ከሌላቸውም በህግ አግባብ መላ ማለት የውቅቱ ጥያቄ ነው።

ቢቢሲ የሚከተለውን ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዐብይ አህመድ ዛሬ ረፋዱ ላይ ለተወሰኑ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በሰንደቅ አላማ ምክንያት አለመግባባትና ግጭት መፈጠር እንደሌለበት አሳስበዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ የሃገሪቱ ስፍራዎች ዜጎች ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ አደባባይ ሲወጡ የወደዱትን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ በአደባባይ መታየት የተለመደ ሆኗል።

ከወራት በፊት ለእስረ ይዳርጉ የነበሩ ሰንደቅ አላማዎች ዛሬ ሰዎች እንደፈቀዳቸው ይዘው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

ትናንት ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የፊታችን ቅዳሜ ወደ ሃገር የሚመለሱትን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮችን ለመቀበል በማሰብ የኦነግ ባንዲራን በመንገዶች ጠርዥ ላይ በቀለም በሚቀቡ ወጣቶች እና እነሱን በተቃወሙ ነዋሪዎች መካከል ግጭት ተከስቶ ነበር።

ስንደቅ ዓላማን በተመለከተ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ”ባንዲራ የሃገር ወይም የፓርቲ የሃሳብ መግለጫ እና ማሳያ አርማ ነው። የትኛውም ቡድን ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው። ይህም መብት ባንዲራን ይጨምራል” ብለዋል።

• “የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የህዝቡን ውይይት መጠየቁ አይቀሬ ነው” – አቶ ንጉሡ ጥላሁን

• የቀድሞው የሶማሌ ክልል ሰንደቅ አላማ እንዲመለሰ ተደረገ

”ያለን ተሞክሮ አንዱ አንዱን አሸንፎ ስልጣን ይዞ ገዢ መሆን እንጂ መሪ መሆን አይደለም። እንደ ማሕብረሰብ አሸንፈን አናውቅም። አሸንፈን የምናውቀው ወራሪዎችን ብቻ ነው። አሁን እኛ እያልን ያለነው፤ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ይሁን ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አውድ ይፈጠር ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ጨምረውም፤ አሜሪካ 13 ጊዜ ባንዲራዋን መቀየሯን በማስታወስ ”የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ከሆነ ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መልኩ መክሮ፣ ዘክሮ እና ደምጽ ሰጥቶ ባንዲራው ሊቀየር ይችላል። ለዚህ ግን ትዕግስት የሌለው ተሸናፊ ነው” ብለዋል።

”በቀን ሁለት ጊዜ በልቶ የማያድር ዜጋ ባለባት ሃገር የህዝብን ጥቅም እንዴት እናስጠብቅ ብሎ ከማሰብ ይልቅ፤ ጉልበቱን ለማሳየት ይሚፍጨረጨር ኃይል ካለ ማንም የማያሸንፍበት እልቂት ውስጥ እንገባለን። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሸንፍ የሚፈልግ ኃይል ሰጥቶ መቀበልን ማወቅ ይኖርበታል” ሲሉም ተደምጠዋል።

‘ሆርን ኦፍ አፍሪካ’

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ ረፋዱ ላይ በሰጡት መግለጫ መግለጫ ላይም መተባበርና በአንድነት መቆም በኢትዮጵያዊያን መካከል ብቻ መሆን ያለበት ነገር ሳይሆን የአካባቢውን ሃገራት በማቀፍ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

”ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ አንድ ላይ ብንሰባሰብ በምሥራቅ አፍሪካ ኃያል ሃገር መፍጠር እንችላለን። ለሁላችን የሚበቃ መሬት፣ ውሃ እና ነዳጅ ያለው ሃገር እንፈጥራለን። ተበታትነን ግን ተሰልፈን ቻይናን ስንለምን እንኖራለን። ህዝቡም ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሃሳቡን በመደገፍ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ።” በማለት በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሃገራት ተሰባስበው አንድ ኃያል ሃገር እንዲመሰረት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው አልፈዋል።

Advertisements

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: