Advertisements

“ኦሮሚያ በሶስት ሳምንት ውስጥ ሁሉም ነገር ወደ ቦታው ይመለሳል” ም/ኤታማጆር ሹም ብርሃኑ ጁላ

ከክልሉ ጋር ተስማምተናል፣ ድርጊቱ በተወሰነ ቡድን ፍላጎት የሚከናወን ነው። አሁን በሰሜን የጦርነት ስጋት የለም። ድርጊቱ ተቀባይነት የለውም። ሰራዊቱንም የሚያስቆም አይደለም …

ሕዝቡ መጀመሪያ ነጻ አውጪ መስለዋቸው ባንዲራ ይዞ በሬ አርዶ ጭፍሯል። በሬውን ሲጨርስ ወደ በግ ገቡ። በግ ሲያልቅ ወደ ዶሮ፣ ዶሮ ሲያልቅ ሃያና ሰላሳ ሆነው መደብደብ ማስገደድ ጀመሩ። … በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ስለገቡ እንኳን መከላከያ የአካባቢው ታጣቂ አንድም የተኩስ ምላሽ እንዳይሰጥ መንግስት መመሪያ በመስጠቱ ነበር ዝምታ የተመረጠው።

እንደታሰበው ሳይሆን እየዋለ ሲያድር ጉዳዩ መረን ስለወጣ በክልሉና በመንግስት ትዕዛዝ የመከላከያ ሃይል ገባ። በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አለ። በሶስት ሳምንት ውስጥ ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ሊመለስ ይችላል። ከሕዝብ በመነጠል ሽፍቶቹ እየተመቱ እንደሆነና ሕዝብ ሙሉ ትብብሩን እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወቁት ምክትል ኤታማጆር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ ናቸው።

እሳቸው አይጥቀሱት እንጂ በርካታ ህጻናት እጅ ሰጥተዋል። ስልጠና ሲሰጥባቸው የነበሩ ቦታዎች ተገኝተዋል። በርካታ ተማረከዋል። ሙሉ በሙሉ መንግስትን በሶስት ወር ውስጥ ለማስወገድ በቅዠት የተነደፈው ነድፍና የንድፉ አቀነባባሪዎች ሰንሰለት ተያዟል። በቤተክርስቲያን ውስጥ የተዋቀረው ሰንሰለት መረጃው መያዙን ዛጎል መርጃ አቀባዮቹን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

የመከላከያ ሰራዊትን መለያ ለብሰው ነጹሃንን ከገደሉ በሁዋላ ሰራዊቱ ሲደርስ መላያ ልብሱን በመቀየር የሲቪል ልብስ ለበሰው መከላከያ ገደለ በማለት ሕዝብ ላይ ቁማር እንደሚጫወቱ ያስታወቁት ኤታማዦር ሹሙ፣ አሁን ነገሮች መቀየራቸውን፣ ዝⷝቶም እርምጃ የተወሰደው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ዝም ብሎ ዘው ማለት ስለማይችልና መንግስት ባስቀመጠው አግባብ መሆኑንን ተናግረዋል። ለሁሉም የህግ አግባብ እንዳለ በፓርላማ ተገኝተው ሲያስረዱ መሳሪያ አንግበው አገር ለማተራመስ የሚነሱ ካሉ ሃላፊነቱ የመከላከያ ሰራዊቱ መሆኑንን አመልክተዋል።

ሃላፊው በትግራይ እንቅስቃሴው ስለተስተጓጎለበት የመከላከያ ሃይል ገለጻ ሰጥተዋል። ” ተግባሩ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ነቅፈዋል። እንቅስቃሴው ከመጀመሩ በፊት የክልሉ ባለስልጣናት ሙሉ መረጃ እንዳላቸውና ስምምነት መኖሩን ያወሱት የመከላከያ ሰራዊት ሁለተኛ ሰው፣ የሰራዊቱን እንቅሰቃሴ የማስተጓጎል ተግባር የሚፈጸመው በተወሰነ ቡድን መሆኑንን አመልክተዋል።

‹‹ የመከላከያ ሰራዊቱን ማገት የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ መከላከያን ማንም ሊያግተው አይችልም፡፡ አማርኛው ቢቀየር ጥሩ ነው፡፡ ሰራዊቱን የትግራይ ህዘብ አያገትም፡፡ ነገር ግን ስጋት እየፈጠረ መኖር የለመደ አካል አለ፡፡ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ህዝቡን ሽፋን አድርጎ ትርምስ ለመፍጠር የሚሞክር ሃይል አለ፡፡ ጥቂቶች ናቸው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይጋለጣሉ፡፡ የትግራይ ህዝብም ቢዘገይም ይገባዋል፡፡ እንዲጋለጡና ህዝቡም እንዲያውቃቸው እናደርጋለን፡፡ ይህ እስኪሆን ግን ከህዝቡ ጋር የሚያጣላ ነገር አናደርግም፡፡ ህዝብ ቅር ከሚለው እኛ ቅር ቢለን ይሻለናል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ነገር ከክልሉ እውቅና ውጭ ነው፡፡ ክልሉ ወስኖ የተደረገ ነገር አይደለም፡፡ የክልሉ ፍላጎትም አይደለም››

ከመምህራን ጋር በተደረገ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” ድንገት የከፋ ችግር አገር ላይ ተደቅኖ ቢሆንስ ኖሮ” ሲሉ ነበር ድርጊቱን የኮነኑትና ህግን መተላለፍ እንደሆነ ያስታወቁት። ክልሉም ሆነ የአካባቢው ህዝብ የኢትዮጵያን ሰራዊት እንቅስቃሴ የማወክ መብት እንደሌለው አግባብ ባላቸው የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቢገለጽም ከክልሉ በድጋፍም ይሁን በተቃውሞ የተባለ ነገር አለመኖሩ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ቅር አሰኝቷል።

አንዳን ለክልሉ ቅርብ የሆኑ የማህበራዊ ገጽ ተዋናዮች ” መሳሪያውን አስቀምጡ፣ እናንተ ውጡ ” የሚል አስተያየትና ህዝቡ መንገድ ዘግቶ የሰራዊቱን እንቅስቃሴ መዝጋቱን በማድነቅ ጽፈዋል። አንዳንዶች ደግሞ የኤርትራ ሰራዊት የተከፈተውን በር ዘግቶ ሰራዊት እያነቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ይህ መሆኑ አግባብ አይደለም ሲሉ ከጋት የመነጨ አስተያየት ሰንዝረዋል።

ሁሉም ይህንን ቢሉም በመከላከያ ሃላፊውም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው አስተያየት የጦርነት ስጋት እንደሌለ ነው። ችግር ካላ መንግስትም ሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት እንጂ የአንድ አካባቢን ህብ ብቻ የሚያስጨንቅ እንዳልሆነ ነው ደጋግመው የተናገሩት።

Advertisements


Categories: Head News/መሪ ዜና

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: