May 21, 2020

“40 ሚሊዮን ብር የደሃ ህዝብ ገንዘብ ዛሬ አልበትንም… ዛሬን የምወስነው ነገን አይቼ ነው”

” ለማይፈጸም የምርጫ ስልጠና 40 ሚሊዮን ብር የደሃ ህዝብ ገንዘብ ዛሬ አልበትንም” ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

አመጽ በሌለበት መልኩ ሃሳብዋን በመግለጽዋ ብቻ የታሰረች፣ በልዩ ሁኔታ ብቻዋን እመቃብር ውስጥ የኖረች፣ ሰው ሳይሆን የፍጡር ኮቴና ድምጽ እንዳትሰማ የተከለከለች፣ ከስቃይ በተጨማሪ በሚያስፈራ ጸጥታ ውስጥ እንድትኖር የተደረገች፣ ያለ ሃጢያቷ የተገለለች፣ የማትቀልጠው ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ የማይገባትን እየሆነች ነው።

እስር ቤቱን ባልቀመሱ፣ መራሩን ትግል ሸሽተው ስጋቸውን አክብረው በኖሩ፣ ” የደሙን እዳ እኔ አወራርዳለሁ” በሚል ፉከራ የድሃ ልጅን በማገዱ፣ ከስልጣን ውጪ አንዳችም ነገር የማይታያቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ብርቱካንን ዛሬ በመላ ምት እያወገዙ ናቸው።

ማውገዙ በገሃድ የተጀመረው አሁን ቢሆንም ቀደም ሲል በግል ” አርፈሽ ተቀመጪ” በሚል ዛቻ ሲሰነዝሩ የነበሩ ዛሬ በደቦ ይህንኑ ዘመቻ እያጧጧፉት ነው። ባንዳና ከሃጂዎችም ይህችን የደቦ ዘመቻ ተገን አድርገው ብርቱካን ሚደቅሳን አብረው እየደበደቡ ነው።

“እንዴት የቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሆነች” በሚል የስልጣን ስካር የተጀመረውን ቂም ለመወጣት ጊዜው አሁን ነው በሚል የጅምላ ዘለፋውንና ማውገዙን የተቀላቀሉ እንደሚሉት ” ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም” ሲያክሉ ምርጫው እንዲራዘመ የተደረገውም ከዚህ መነሻ ነው ይላሉ። በጥቅሉ ተአማኒ ሴት አይደሉም ሲሉ ወ/ት ብርቱካንን ሊያሸማቅቁ ይተጋሉ።

ሰሞኑንን ከጀርመን ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወ/ት ብርቱካን ” ለማይፈጸም የምርጫ ስልጠና 40 ሚሊዮን ብር የደሃ ህዝብ ገንዘብ ዛሬ አልበትንም” ሲሉ እንቅጩን ተናግረዋል። ሲያብራሩም ሃምሳ ሺህ የምርጫ ጣቢያ መኖሩን፣ 150 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ይዘጋጃሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በተከታታይ አንዱ ስራ ሲጠቃለለ ሌላው እየተከተለ ነው። እናም በሁለትና ሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አሁን ባለው የወረሺኝ ስጋት እንዴት ስልጠና ማካሄድ ይቻላል? ሲሉ በትዝብት ይጠይቃሉ።

ሚያዚያ 14 ቀን የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው ምዝገባ ሲጀመር በመጋቢት 150 ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች በአግባቡ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል። 150 ሺህ ሰዎች ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ወደ ምስራቅ፣ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ይነቃነቃሉ። ዛሬ ዓለም በምትገኝበት እውነታና አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ይህ እንዴት ይተገበራል ለሚለው መልስ የሚሰጥ ተሳዳቢ የለም። ወይም በገሃድ ወጥቶ ” ያፈለገውን ያህል ህዝብ ይለቅ ስልጣን መያዝ አለበን” ሲሉም አይደመጡም።

ይህችን ትንታግ ሴት ቀድሞውንም ይህንን ያፈጀና የቆሸሸ ተቋም እንድትመራ ይደረጋል ተብሎ አይጠበቀም። ለብርቱካን ቅርበት ያላቸው እንደሚመሰክሩትና የዚህ ሪፖርት አቅራቢ እንደሚያውቀው ወ/ት ብርቱካን በቀላሉ የሚናድ ስብእና የላቸውም።

«አብይ አሕመድ ምርጫው ከመንግሥት ተፅዕኖ ለማውጣት ቃል ሲገቡ ይህንን አደርገዋለሁ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። መንግሥት የምርጫ ቦርዱን ራሱን እንደቻለ ተቋም እንዲቋቋም ፍላጎት አለው” ማለታቸው ሲታሰብና የብርቱካን መሾም ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ለመተግበር ከድምዳሜ ላይ እንደደረሱ የሚያመላክት ነው። እናም ዛሬ የኮሮና ወረርሺኝ ዓለምን እየበላ ባላበት ወቅት ምርጫው እንዲራዘም ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉ በየትኛው መመዘኛ ጥፋተኛ እንደሚያሰኘው ግራ እንደሚያጋባ በርካቶች ይናገራሉ።

ምርጫ ተከታታይ ስብሰባ፣ የአማራጭ ፖሊሲ ክርከር፣ ሰልፍና የተለያዩ ፓርቲዎች ደጋፊዎችን በየጊዜው በመሰብሰብ ሰፊ የውስወሳ ስራ የሚሰሩበት፣ መራጭ ህዝብም ምርጫውን ለማስተካከል አማራጭ ሃሳብ ሊሰማ፣ ሊሞግትና ሊመረምር የሚሻበት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እንዴት ይህንን ዋና ተጋባሩን ሳያከናውን ይካሄዳል? ለሚለው ጥያቄም እነዚሁ ወገኖች ምላሽ የላቸውም። ይልቁኑም ስልጣን ባቋራጭ ለመያዝ ህገመንግስት ተጣሰ በሚል ህገወጥ ጥያቄ እያቀረቡ ነው።

በጤና ባለሙያዎች፣ በኤክስፐርቶች፣ አግባብ ባሉ ተቋሞችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚወጡ መመሪያዎች መነሻነት እንዲራዘም የተወሰነን ምርጫ፣ ይህም ሲሆን ሁሉም ፓርቲዎች በተስማሙበት መድረክ / ቪዲዮው አለ ሲሉ ወ/ት ብርቱካን ይፋ እንዳደረጉት/ አሁን ያለው የሚሰማው ቀረርቶ ወዴት እንደሚወስደን አለማገናዘብ ለሰሚው ግራ ነው።

ውይይቱ ሲደረግ ህወሃትና ብልጽግና ብቻ ሲቃወሙ ሌሎች ፓርቲዎች ኦፌኮን ጨምሮ ተስማምተዋል። ሁለቱ ፓርቲዎች ” ትንሽ እንየው” ሲሉ የወረሽኙን አካሄድ መጠበቅ እንደሚገባ ከማመልከታቸው የዘለለ ተቃውሞ አለመሰንዘራቸውን ወ/ት ብርቱካን ማስረጃ ጠቅሰው ይፋ አድርገዋል። አያይዘውም ህወሃት አስቸኳይ ቀድሞ ጊዜ ማወጁን፣ የፌደራል መንግስትም ትምህርት ቤቶች ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ማራዘሙን፣ ክልሎች የትራንስፖርትን ጨምሮ ማዕቀቦች መጣላቸውን ይፋ እያደረጉ 150 ሺህ የምርጫ አስፈሳሚዎችን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በማዘዋወርና በማሰማራት ምርጫ ለማካሄድ የተሳለጠ ስራ መስራት እንዴት ይቻላል?

Leave a Reply

%d bloggers like this: