May 22, 2020

አቶ ሙስጣፊን በቡድን ተደራጅተው ለመግልበጥ የሞከሩና ስርዓት የጣሱ ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ

አቶ ሙስጣፌ መሐመድን ” ተራ የፌስ ቡክ አክቲቪስት” እያሉ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ የሚያጣጥሉዋቸው ጥቂት ክሎች ያሉትን ያህል አብዛኛው ሕዝብ በመገረም የሚተርካቸውና እንደ ክስተት የሚያቸው መሪ ናቸው። እንደ ጄል ኦጋዴ አይነቱን ማሰቃያ ወደ ሙዚየምነት በመቀየራቸውና በስፍራው ሲፈጸም የነበረውን ግፍ ለዓለም ማጋለጣቸውን ተከትሎ ጥቅማቸው የጎደለባቸው ጥርስ ነክሰው ዘመቻ እንደሚያካሂዱባቸው የሚደግፉቸው ደጋግመው ሲናገሩ ቆይተዋል።

A Human Rights Watch drawing of a prisoner in Ethiopia's Jail Ogaden in the country's Somali region.  Human Rights Watch accused officials of treating prisoners poorly and denying them judicial process.

በአሜሪካ ሜኖሶታ የሚኖሩና በዩኒቨርስቲ መመህር የሆኑት አቶ ጎርሴ እሳቸውም በአጋርነት የሚሳተፉበት ቡድን በሙስጣፌ መሪነት በክልሉ የተፈጸመውን ግፍ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን፣ ለዚህም በጀት መገኘቱንና ይህ እንቅስቅሳሴ ያስፈራቸው አካላት እሳቸውን ከሃላፊነት ለማስነሳት በትሥሥር ዘመቻ መጀመራቸውን ከዓመት በፌት ለዛጎል አስታውቀው ነበር።

በቅርቡ አስራ ሁለት የሚጠጋ የጅምላ መቃብሮችን እያሳዩ ” የሶማሌ ክልል ተወላጆች በይፋ ይቅርታ ሊጠየቁ ይገባል” ሲሉ ወንጀሉን የሰሩትን ክፍሎች በመጥቀስ መግለጫ መስጠታቸው የዚሁ የፍትህ ፍለጋው አካል መሆኑንን በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ መስክረዋል።

ለውጡ ይፋ እንደሆነ በክልሉ ተፈትሮ የነበረውን አስፈሪ ቀውስና አሰቃቂ ነውጥ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቆም፣ ተጎጂዎችንም በመካስ ወደ ሰላማዊ ህይወት በመለስ ረገድ የፈጸሙት ተግባር እንደ ትልቅ ስኬት የሚጠቀስላቸው ሙስጣፊ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከሙስና ጋር በተያያዘ ስማቸው በማህበራዊ ሚዲያና በዩቲዩብ ቻናሎች ሲነሳ ከርሟል።

ሂይውማን ራይትስ በኦጋዴን የተፈጸመ ቅሌት ሲል ያቀረበው

ትናንት የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ከመቀመጡ በፊት ” ምንጮች ነገሩን” በሚል እሳቸውን ለማንሳት ሞሽን እንደሚጠየቅ፣ የሙስጣፌ ጉዳይ ያለቀና ያከተመለት እንደሆነ ተደርጎ ቀርቦ ነበር። ስብሰባው ሲጀመር እሳቸውን ከስልጣን ለማስነሳት በተየቁና እንዲያዝላቸው የፈለጉት አጀንዳ በመውደቁ ተበሳጩ ከተባሉት የምክር ቤት አባላት መካከል 12 የሚሆኑት ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱን የክልሉ መንግስት አስታውቋል። ይሁን እንጂ እስካሁን የታሰሩ ስለመኖራቸው አልተገለጸም። ሙስጣፊ በኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ አክራሪ ፖለቲከኞች ጋር በሃሳብ ስለማይግባቡ አይወደዱም።

ቢቢሲ ሁሉንም ወገኖች አናግሬያለሁ ሲል የሚከተለውን ዘግቧል።

ለወራት ሳይካሄድ ቆይቶ የነበረው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድን ከስልጣን እንዲነሱ በጠየቁ አባላት በተነሳ ውዝግብ ምክር ቤቱ የ12 አባላትን ያለመከሰስ መብት አነሳ።

ለረጅም ጊዜ ስብሰባ ሳያካሂድ የቆየው የክልሉ ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት በጠራው ስብሰባ ላይ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመያዝ ውሳኔ ለማሳለፍ የተሰበሰበ ቢሆንም ከተያዘው አጀንዳ ባሻገር በምክትል ፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ላይ በመወያየት የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ በጠየቁ አባላት አማካይነት ውዝግብ ተነስቶ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የምክትል ፕሬዝዳንቱን በሚመለከት በዕለቱ የተያዘ አጀንዳ እንደሌለ ተገልጾ በሌሎቹ ላይ በምክትል አፈጉባኤዋ አማካይነት ውይይት ለማድረግ በሚሞከርበት ጊዜ በአዳራሹ ውስጥ ተቃውሞና ረብሻ መነሳቱን የምክር ቤቱ አባል መሐመድ አሊ ሐላዕ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሂደቱ ላይ ተቃውሟቸውን የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት ከአዳራሹ መውጣታቸውንና በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ውስጥ “ሁከት መፍጠራቸውን” እንዲሁም “ሕገ ወጥ አካሄድን መከተላቸውን” አቶ መሐመድ ገልጸዋል።

ከሁለቱም ወገኖች በኩል በአጀንዳው ላይ ያለቸውን ልዩነት ስላሰሙት የምክር ቤቱ አባላት ብዛትን በተመለከተ የተለያዩ ቁጥሮች ቢሰጥም ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የተወሰነባቸው አባላት ቁጥር ግን 12 ነው።

ያለመከሰስ መብታቸው ከተሰሳው የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አብዱራህማን ኡራቴ “እርምጃው ሕገ ወጥ ነው” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ለመታደም 180 አባላት መገኘታቸውንና በምክትል አፈጉባኤዋ አማካይነት ለዕለቱ የተያዙት የስብሰባ አጀንዳዎችን ወደ ማጽደቅ ሲገባ አለመግባባትና ረብሻ እንደተከሰተ አመልክተዋል።

ከዚህ በኋላም የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ከአጀንዳው ውስጥ የክልሉ መንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ይጨመርበት የሚል ሐሳብ አቅርበዋል። ነገር ግን ይህ አጀንዳ ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተወሰኑ አባላት ስብሰባውን ጥለው መውጣታቸው ተናግረዋል።

የምክር ቤቱን ስብሰባ ረግጠው ከወጡት አባላት አንዱ የሆኑት አቶ አብዱራህማን ኡራቴ ከአዳራሹ ውጪ “ለጋዜጠኞች ስለክስተቱ መግለጫ መስጠት ስንጀምር በፖሊስ ጥቃት ደርሶብናል። የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ላይ ድብደባ ተፈጽሟል። የእኔ ቤትም በፖሊስ ተበርብሯል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እሳቸውን ጨምሮ ስብሰባውን ጥለው የወጡት የምክርቤት አባላት “127” መሆናቸውን የሚናገሩት አብዱራህማን ኡራቴ፤ የአባላቱ ቁጥር በቂ ስለማይሆን ስብሰባው ይቀጥላል ብለው እንዳላሰቡ ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳው በቂ ቁጥር ያላቸው እንደራሴዎች ድምጽ ባልሰጡበት ሁኔታ ከሰዓት በኋላ የ12 የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት መነሳቱን “የሕግ ጥሰት ያለበትና የምክር ቤቱን የአሰራር ደንብ ያልተከተለ ሕገ ወጥ እርምጃ ነው” ይላሉ።

ከዚህ ክስተት በኋላ ከጅግጅጋ ወደ ድሬዳዋ የተመለሱት አቶ አብዱራህማን ኡራቴ እንደሚሉት “በቀጣይ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ለሚመለከተው አካል ድርጊቱን በተመለከተ ክሳችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

ስብሰባውን ረግጠው ከአዳራሹ ወጡ የተባሉት ሰዎች ቁጥር 30 የሚደርስ እንደነበረ ነገር ግን በምክር ቤቱ ውሳኔ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው “ረብሻውን” በመቀስቀስ መርተዋል ከተባሉት 12 አባላት ላይ ብቻ መሆኑን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳው አባላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ባደረገው ሙከራ “ልንታሰር እንችላለን” በሚል ስጋት አብዛኞቹ ከጅግጅጋ ከተማ ወጥተው ወደ ሌሎች ከተሞች መሄዳቸው ተነግሯል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ እስከ መጨረሻው ተሳትፈው የነበሩት እንደራሴ አቶ መሐመድ አሊ ሐላዕ በምክር ቤቱ የ12 አባላት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ሲወስን ድምጽ ሲሰጥ እንደነበሩ በመግለጽ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በቂ የአባላት ቁጥር እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 238 አባላት ያሉት ሲሆን ምክር ቤቱ ውሳኔ ለማሳላፍ የሚያስፈልገው ሁለት ሦስተኛ የአባላት ቁጥር 152 መሆኑን በመግለጽ በትናንቱ ስብሰባ ላይ ግን 184 አባላት መገኘታቸውን ይጠቅሳሉ።

“የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ ሂደቱን ለማወክ ሞክረዋል” የሚሉት እኚህ አባል በዚህም ምክንያት እርምጃ መወሰዱን ይናገራሉ።

እነዚህ አባላት ለዕለቱ ስብሰባ ከቀረበው አጀንዳ ውጪ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ያልመከሩበትን “የራሳቸውን የግል አጀንዳ በማቅረብ ነበር የስብሰባውን ሂደት ለማወክ የሞከሩት” ሲሉም ይከሳሉ አቶ መሐመድ።

ጨምረውም ያቀረቡት አጀንዳም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ከስልጣን እንዲነሱ የሚል እንደሆነ ገልጸው፤ “ይህም ቢሆን ደግሞ የምክር ቤቱ አባላት የሚከተሉትን የአሰራር ሥርዓት መከተል ነበረባቸው። እነሱ ግን ከዚህ ውጪ የሚፈልጉትን ለመፈጸም ሞክረዋል” ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ምክር ቤቱም ያቀረቡትን አጀንዳ ባለመቀበሉ ወደ ረብሻና ሁከት መግባታቸውን በመጥቀስ፤ ከስብሰባው ከወጡ በኋላ ደግሞ ወደ ምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት በመሄድ ሁከት ፈጥረዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።

ከዚህ በኋላም በ12ቱ የምክር ቤት አባላት ላይ ያለመከሰስ መብትን ሲነሳ 158 አባላት ድምጻቸውን እንደሰጡ የተገለጸ ሲሆን “የእነዚህ አባላትም ስም ዝርዝርና ፊርማቸው ያለ ስለሆነ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስፈልገው የምክር ቤት አባላት ቁጥር ተገኝቷል” ሲሉ እርምጃው ሕግን መከተሉን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ ለዕለቱ በተያዙለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ሐሙስ ማምሻውን ስብሰባውን ማጠናቀቁን እስከ መጨረሻው ተሳታፊ የነበሩት አቶ መሐመድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን፤ አንዳንዶች ግን ሊከሰሱ የሚችሉባቸው ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል አመልክተዋል።

Leave a Reply

%d bloggers like this: