ዛሬ ይህ ሆነ፤ እዚህ ላይ ደረስን ፤ ነገስ? የዘር ፖለቲካ ድምር !!እዚህ በመድረሳችን ኩራት የሚሰማችሁ እንኳን ደስ አላችሁ!!

Genocide

በጋምቤላ በአንድ ጀንበር አምስት መቶ የሚደርሱ የአኝዋክ ልጆች ተሰየፉ፣ ተጨፈጨፉ፤ በቢኒሻንጉል በተመሳሳይና በተደጋጋሚ አማራዎች ተገደሉ፣ በበደኖ ገደል ውስጥ ተጣሉ በአርሲ፣ በወተር፣ በቆቦና በደደር እንዲሁም በዋተርና በሞያሌና አካባቢው ላይ ጭፍጨፋ ተካሂዷል። ደቡብ ክልልም የተለያዩ ቦታዎች እልቂት ተፈጽሟል፣ በአወዳይ ይኸው በስዕሉ እንደታየው የሰው ልጆች ተጨፈጨፉ፣ የሚጠየቅ የለም።

somali v oromiya

አሁን አሁን ጭፍጨፋ በአዋጅ ሁሉ ፈቃድ እየተሰጠው ንጹሃን እየተፈጁ ነው። የት ነው ማቆሚያው? እየባሰ እንጂ እየላላ የሚሄድ ነገር አይታይም። የፈለገው ክልል ተነስቶ ያፈናቅላል። የፈለገው ክልል ተነስቶ ድንበሩን ያሰፋል። የፈለገው ክልል ተነስቶ እንደ አገር ከሌላ አገር ጋር ስምምነት ያደርጋል፤ የፈለገ ክልል ተነስቶ ማንነትን በጥይትና በሃይል ያስቀይራል። የፈለገ ክልል ታሪክ እየገለበጠ ወደ ራሱ ይወስዳል። የፈለገ ክልል ያስራል፣ ይፈታል፤ ብዙ ብዙ የተወገዙ ድርጊቶች ይፈጸማሉ … ወዘተ አሁን የሚያሳስበው የነገው ነው። ለምን? ቢባል እየባሰ እንጂ እየለዘበ የሚሄድ ነገር አልታየምና!!

የዘር ፖለቲካ ሃሺሽ ነው። የዘር ፖለቲካ እንደ ሃሺሽ አቅል ያሳጣል። የዘር ፖለቲካ ከሰውነት ያወርዳል። የዘር ፖለቲካ ጠንሳሾቹን፣ አስፈጻሚዎችን፣ተከታዮችን፣ አገልጋዮችን፣ ሁሉንም አውሬ የሚያድርግና እንደ ተስቦ የሚተላለፍ በሽታ ነው። አሁን የደረስንበት መንገድም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

ይህንን ክስረትና ውድቀት ማየት ቢቻልም፣ አዝኖ እርምት ለመውሰድ እንኳን እድል በማይሰጠው በዚህ መጋኛ አስተሳሰብ አገርም ፣ ህዝብም፣ ተተኪው ትውልድም፣ የታጠቀውም፣ ያልታጠቀውም ተያይዞ ወደ ሞት እየጋለበ ነው። ማን ያስቁም? የትኞቹ መሪዎች ከዚህ አዙሪት ነጻ በመውጣት አገሪቱን ይታደጉ?

ተቃዋሚ የሚባሉት የራሳቸው ክሽፈት፣ ሽባበትና፣ ምክንያት የማይቀርብበት የእርስ በእርስ ውዝግባቸው እንዳለ ሆኖ፣ ከፍ ሲሉና ከዘር እሳቤ እርቀው ህዝብ ሲወዳቸው በሃይል ማፍረስ፣ በህግ ማፍረስ፣ ማሰርና ማጥፋት አማራጭ ሆኖ በመወሰዱ አገሪቱ ተተኪ አልባ እንድትሆን አድርጓታል። የዘረኛነት ፖለቲካ ሌሎች በነጻ እንዳያስቡም ጭምር የሚያግድ ጋንግሪን በመሆኑ በሁሉም ደረጃ ክሽፈት ተመዝግቦብናል።

አሁን የሚፈራ መሪ የለንም። የሚከበር የሃይማኖት አባቶች የሉንም። የምንመካባቸው አታጋዮች የሉንም። ነጻ ሆነው መንገድ ለማጽዳት ለሚተጉ እድል የለም፤ እና ምን ይሁን? ዛሬ ጥያቄው ማልቀ ሳይሆን ከዚህ አውሬ አስተሳሰብ እንዴት እንውጣ ነው? እንዴት ? በመፈክር እስከመቼ እንኖራለን? ዘጠኝ ሚሊዮን ርሃብተኞች ይዘን እንዲህ ያለው የዞረበትና መጨበጫ የሌለው የዘር ፖለቲካ ድምር ላይ መድረስ ለሚያኮራቹህ እንኳን ደስ አላችሁ!!

 

 

Advertisements

“ሙሉ ጋዜጠኞች” ነን? እንዴትስ ሙሉ እንሁን?

ዛጎል በይፋ ሃሳቧን መሰንዘር ስትጀምር አንድ ችግር “ጋዜጠኛ” ያደረጋት እህት ” ዲያስፖራውን የሚያስደስት ዘገባ ካላቀረባችሁ አንባቢ አይኖራችሁም” ስትል ምክር ቢጤ ሰነዘረች። መረጃን ማመጣጠን የሚባለው ዋና የ”ጋዜጠኛነት” መለኪያውስ? የሚለውን ጉዳይ አነሳን። ከዚያ በሁዋላ የነበረው እንቶ ፈንቶ ነውና አናነሳውም።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዓለማት ይኖራሉ። ከማይፈለጉት በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው መስማማት ቢቻልም፣ ሁሉም ተመሳሳይ የፖለቲካ አቋምና እምነት አላቸው ብሎ ከቶውንም አይታሰብም። መንግስትን/ ኢህአዴግን ወይም ህወሃትን/ የሚቃወሙት እንኳ ተስማምተው ሲሰሩ አይታዩም። ይልቁኑም በተቃራኒው ሲሻኮቱ ነው ጊዚያቸውን የሚያሳልፉት። ተጋነነ ካልተባለ “የመቃወም ፖለቲካ የጥበብ መጀመሪያ እርስ በእርስ መጣላትና መሰዳደብ ነው” የሚል መተዳደሪያ ያላቸው የሚመስሉ አሉ።
እንግዲህ እንዲህ አይነት ውሉ የጠፋበት ማህበረሰብ ውስጥ ስንኖር አንዱን ወገን ማርካት እንዴት ይቻላል? ጋዜጠኛነት በራሱ ” ማርካትና፣ ማስቀየምን” አንግቦ የሚካሄድ የስራና የሙያ ዘርፍ ነው ወይ? ከዚያም በላይ ዲያስፖራው የተመጣጠነ መረጃ ማግኘት እንደማይፈልግ ማን አጠና? ማንስ ተመራመረ? እንዴትስ እዚህ ድምዳሜ ላይ ተደረሰ? ምክር ቢጤ ለሰነዘረችው ሴት የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ። እሷም ሆነች ሌሎች ሊመስልሱት የማይችሉት ጥያቄ!!
ይህንን ጉዳይ ያነሳነው ወደን አይደለም። የመካሪዋንም ሃሳብ እርቃን ለማሳየት አላሰብንም። ይልቁኑም እንዴት መረጃ በማግኘት የተሟላ ሪፖርት ማቅረብ ይቻላል? የሚለው ጉዳይ ስላሳሰበን ነው። ኢህአዴግ በውጭ አገር ላሉ ሚዲያዎች ዝግ ነው። ለሚቀርባቸውና የራሱ ከሆኑት ውጪ ለሌሎች መርጃ ለመስጠት አያስብም። ይልቁኑም አሸባሪና አተራማሽ እያለ መፈረጅን ነው የሚመርጠው። በዚህ መነሻ የሚፈለጉትም የማይፈልጉትም ሁሉም የተባራሪ መረጃ ሰለባ ሆነዋል። እኛም እየሆን ነው። ለዚህ ችግር ዋና ተጠያቂ ኢህአዴግ ነው። ይህንን ችግር መፍታት ከፈለገ በውጪ አገር የመረጃ ዴስክ መክፈት ወይም አንድ መላ መፈለግ አለበት።
አገር እየመራ ያለው ኢህአዴግ የሚዘለፈውን ያህል ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም በአግባቡ ጠይቆ፣ መርምሮና አረጋግጦ መውቀስም አይቻልም። አንዳንዶቹ ኢሜል እንኳን አይመልሱም። በራቸው ዝግ ነው። ሃስባቸውን ከራሳቸው የዌብ ሳይት አድራሻ ለመውሰድ እንኳን ቢታሰብ ” የሚይስቅ ጉዳይ ያጋጥማል” የተወሰኑት ጥሩ የሚባል የመረጃ የዌብ ገጽ ቢኖራቸውም ለተጨማሪ ጉዳይ የሚገኙ አይደሉም። በዚህ በኩል ተቃዋሚዎችም የኢህአዴግን ያክል ባይሆንም ለመረጃ ዝግ መሆናቸው አሳሳቢ ነው።
ዛጎል በዚህ አጭር ጊዚያት አራት ለሚደርሱ ድርጅቶች መርጃ እንደምትፈልግ ጠቀሳ ጠይቃለች። መልስ ግን አላገኘችም። ለወደፊቱም ቢሆን መረጃ ማግኘት የሚቀል መስሎ አይታይም። ታዲያ እንደ ጋዜጠኛ የሪፖርት ስራ እንዴት እንስራ? ወይስ ተባራሪ ወሬ እንሰብስብ? ወይስ ዳያስፖራው የሚፈልገው ያልተመጣጠነ መረጃ ነው ብለን በመደምደም የውስን ጸሃፊዎችን ሃሳብ እየተቀበልን እናሰራጭ።እዚህ ላይ በተደጋጋሚና ያለማቋረጥ ሃሳባቸውን ለሚያካፍሉ ወገኖች ያለንን አድናቆት ልንገለጽ እንወዳለን። ምክንያቱም “አያገባንም” በሚል አብዛኞች “አድፋጮች” ሆነው ቀርተዋልና።
ከላይ በተገለጹት ምክንያቶችና በሌሎችም ጉዳዮች እንደ ጋዜጠኛ የማያስወቅስ ስራ ለመስራት መቸገራችንን አስረግጠን ለማስገንዘብ እንወዳለን። አሁን ባለው አሰራር ጋዜጠኞች ነን ብልንም አናስብም። አሁን ላለው የመረጃ ክፍተት የተመጣጠነ ሪፖርት በማቅርብ የበኩላችንን ለመወጣት ብናስብም ሰባራ ሆነናል። አዲሱ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቅም ካላቸው ይህንን ሊያስቡበት ይገባል። ራሱ ኢህአዴግም ቢሆን በደፈናው ሚዲያዎችን ከማውገዝ በመቆጠብ ሳያዳላና ሳይመርጥ መረጃ ለሚፈልጉ ሁሉ መረጃ የሚደርስበትን ቀልጣፋና ግልጽ አሰራር ሊተገብር ይገባል። መረጃ የሌለው ጋዜጠኛ ሚዛኑን ለመጠበቅ ስለማይችል ሚዛን በሚጎድላቸው መረጃዎች ራሱን፣ አገርንና ህዝብን ይጎዳል። ሚዲያ ታላቅ ሃይል አለውና በወጉ እንጠቀምበት ዘንድ አስቸኳይ ምላሽ እንሻለን።
በሌላው ጎኑ ተቃዋሚዎች፣ ሲቪክ ድርጅቶች፣ አክቲቪስት ነን የምትሉ፣ ተመራማሪዎች እና ወዘተ… እናንተም ብትሆኑ መረጃ መስጠት ግድ መሆኑን በመረዳት ለሚፈልጋችሁ ሁሉ ደጃችሁ ክፍት ሊሆን እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን። በተመሳሳይ ስም የተደራጃችሁ ቢያንስ ለመረጃ ፈላጊዎች አመቺ ይሆን ዘንድ መረጃ የሚፈስበትን መንገድ አመቻቹ። መረጃ የመስጠት ግዴታ አንዱ የስራችሁ አካል መሆኑን አትዘንጉ። ሌሎች የሚወቀሱበት መንገድ ውስጥ ሆናችሁ ከሌሎች እንደምትሻሉ መስበክ ታማኝ አያደርገምና ግብራችሁ የዴሞክራሲ ወዳድ ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ መረጃ ለመስጠት በርን መበርገድ ይሆናል። ሚስጢር ብሎ ነገር የለምና!!
ዛሬ አብዛኞች በዘርፉ የተሰማሩ ጽሁፎችን እየተቀባበሉ ከማተምና ከማሰራጨት ማለፍ ያለቻሉት በዚሁ በመረጃ ዝግነትና መቀራረብ ላይ በተመሰረት ግንኙነት ነው። ስለዚህ መርጃ ማግኘት መብት ነውና የተዘጉ በሮችን ለማስከፈት ተመሳሳይ ድምጽ እናሰማ። ዲያስፖራውም ሆነ አገር ቤት ያለው ህዝብ ተወደደም ተጠላም የመረጃ ጥማት አለበትና ለተመጣጠነ መረጃ እንትጋ። አለያ ግን አንካሳ ጋዜጠኛ ሆነን የሚፈለገውን ያህል ለማከናወን ይሳነናልና። በዚህ መልኩም መቀጠል አገራዊ ፋይዳም የለውም። ትርፉ ድካምና ድካም ብቻ ይሆናል። እኛም “ጋዜጠኛ” መባላችን ጥያቄ ውስጥ ይወደቃል። ፈተናውንም አናልፍም። ፈተናውን የማያልፍ …
አንዳንድ መረጃዎችን ከተለያዩ ሚዲያዎች በማሰባሰብ መስራት የሚቻልበት አግባብ ሊኖር ይችላል። እያደረግነውም ነው። ግን መረጃዎች ወደ ራስ አስተሳሰብ የመንጋደድ ዝንባሌ አላቸው። የመንግስት ሚዲያዎች በአብዛኛው አሞጋሾች ናቸው። በውጪ ያሉት ደግሞ ከላይ ባልነው ችግር የተነሳ ማመጣተኛ መርጃ ስለማያገኙና ሌሎች ምክንያቶች ታክለውበት ወደ አንድ ጽንፍ የማምራት ጉዳይ ይታያል። እንዚህን መረጃዎች እየቀዱ ማሰራጨት አሁንም ሙሉ ጋዤጠኛ አያደርግም። “ሙሉ ጋዜጠኛ መሆን” ለሚፈለጉና ለሚመኙ ሁለቱም መንገዶች ያስቸገራሉ። እና እንዴት እንቀጥል? እያነከስን? ጽሁፍ በመቀራመት? በግል አስተያየት? እንዴት ? ይህ በአጭር ጊዜ የታዘብነውና ብቻችንን ለንወጣው የማንችለው ችግር ሆኖብናል? እንዴት ” ሙሉ ጋዜጠኛ? እንሁን?