ኦህዴድ “ስግብግብ” ህወሃት በተስፋ ባቡር …

ያስቃል። ያዝናናል። ከሃያ ሰባት ዓመት በሁዋላ ኦህዴድ ለመሪነት ቢበቃ ” ገብጋባ ” ተባለ። ለልጣን የቋመጠ ሆነና ተፈረጀ። እናም ኦህዴድ ሲመራ አገር እንደምትበተን ይነገር ጀመር። ሃያ ሰባት ዓመት በጠቅላይ ጨዋታ ስልጣን ላይ ጉብ ያሉ ” ገብጋባ፣ ስግብግብ” እያሉ ኦህዴድን ሲፈርጁት መስማት የዘመኑ ድንቅ ድርሰት ሆነ። ከፈራጆቹ በስተቀር!! ፈረንጆቹ ማለቴ አይደለም። ሃያ ሰባት ዓመት አይበቃም ማለት ወይስ … ማን ነው ገብጋባ፣ ሥስታም? ሆዳም? ከርሳም? የስልጣን ሱሰኛ….

Continue Reading

Advertisements

የትግራይ ሪፐብሊክ አዋጅ!! ” እናት” ኢትዮጵያ ምን ይዋጥሽ?

አገሩ በሙሉ በባንዲራ አሸብርቋል። ከበሮ ይደለቃል። ለቁጥር የምታክቱ ሃውልቶች የሚፈስባቸው ብርሃን ያጥበረብራል። መኪኖች ጥሩምባ እየነፉ ይከንፋሉ። ሁሉም ዘንድ ” ደርብ” ይጨፈራል። ሁሉም መንደር ስካር ሆኗል። ቀይ፣ ቢጫና፣ በውል የማይለይ ቀለም የለበሱ ሕጻናት በሰልፍ ይተማሉ። “በታላቁ” መሪ ሃውልት አናት ላይ የሚንቀለቀል እሳት ይነዳል። የሃውልቱ ቁመት ትልቅ በመሆኑ ለሁሉም ይታያል። ከሃውልቱ ግርጌ ” እድሜ ላንተ” የሚል ክታብ ብልጭ ድርግም ይላል። የሱዳን ባንዲራ መንገዱን ሞልቶታል። ጀለቢያ የለበሱ የሱዳን ሰዎችም ያወካሉ። 

Continue Reading

“የሚገልህ ሆዳም ወንድምህ ነው” አለችን – ሃሬ ጉድ!!

ባልደረባዬም ሙሊት ነው። ሴትየዋ እንደ ጋሪ ነች። መናገር እንጂ ማሰብ አትችልም። ፋናና ኢቲቪን የምታዳምጥም አትመስልም። ቀባጠረች። ግድያው ላይ እና የስር ቤቱ ሮሮ ላይ ሙግት ገቡ። ቡና ስኒ ተሰበረ። ተዘላለፉ። በብሄር ተኮር ስድብ ተናረቱ። ይህን ጊዜ ያበደው ጥሎ ወደ ሚኖርበት ከተማ አመራ።

Continue Reading

ኧረ – ሼም ነው !! – አይ ” በጥል – ቁ ” መታደስ

ገዚዎች ራሳቸውን ክፉ ስድብ ሲሰደቡ። በጠቂቱ ሸተናል፣ ገምተናል፣ በስብሰናል፣ኪራይ ስብሳቢ ነን፣ ሙሰኞች ነን፣ ነቅዘናል፣ እንደ ስርዓት ሟምተናል፣ መተማመን አልቻልንም፣ ጸረ ዴሞክራሲ ነን፣ ሕዝብ ፊት መቆም አልቻልንም እናፍራለን፣ ተሸርሽረናል፣ ተገዝግዘናል፣ ሞተናል፣ ሕዝብ ጠልቶናል፣ ሕዝብ አንቅሮ ተፍቶናል፣ በእኛ ምክንያት አገሪቱ አደጋ ላይ ወድቃለች፣ ልትፈራርስ ነው፣ ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፣ ደላሎችና ኮንትሮባንዲስቶች ሆነናል……… ይቀጥልና …. ተሃድሶ፣ ጥልቅ ተሃድሶ፣ የጠለቀ ለውጥ፣ ስር ነቀል ለውጥ… ይቀጥልና ለጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ፣ ሂስ፣ ግለ ሂስ… ይቀጥልና አሮጌ አመራር ከች!!
ሕዝብ እንዲህ ይል ነበር። አሁንም እያለ ነው። በጥቂቱ፤ በቃን፣ መረረን፣ ፍትህ አጣን፣ ሙሰኞች ይወገዱ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ናፈቀን፣ ነቅዛቹሃል፣ በስብሳቹሃል፣ ሸታቹሃል፣ ፍትህን ከልክላችሁሃል፣ አትሰሩን፣ አትግደሉን፣ አትግረፉን፣ ውረዱ፣ በመረጥነው እንተዳደር፣ አትበታትኑን፣ አትከፋፍሉን፣ አገራችንን አታክስሙ፣ አትነገዱብን፣ …. ቀጥሎ አመጽ ገነፈለ፣ ሕዝብ ተነሳ፣…. ቀጥሎ ሕዝብ ተገደለ፣ ታሰረ፣ ተገረፈ፣ ቀጥሎ… ቀጥሎማ አሁንም ሕዝብ እንደቶቆጣ ነው። የቻለም ሽፍቷል ይባላል።
ሰላም ይብዛላችሁ። በያላችሁበት ክብር ለናንተ ይሁን።አሁን ባለው ሁኔታ ሰማእታት እነማን ናቸው? ያበደው ጠየቀ። አዎ መልሱ አጭር ነው። ሲሞቱም ሲገሉም፣ ሲያስገድሉም ” ሰማእታት” እነሱ ብቻ ናቸው። ግን አሁን ሰው ሰማእት ተባለ አልተባለ… ሰው ከበሰበሰ በሁዋላ … ያበደው ቀላመደ። ….
አሁን ያበደው ሁለቱንም ወገኖች አሰባቸው። ሕዝብና ገዢዎቹ ቋንቋቸው አንድ ሆነበት። ራሳቸውን ከሚሰድቡት በላይ ማን ሰድቧቸው ያውቃል? ችግሩ ሌሎች የራሳሸውን ቃል እንኳን ተጠቅመው ሲናገሯቸው ነው።
ራሳቸውን ይሰድባሉ። ራሳቸውን ያጠለሻሉ። ራሳቸውን ያዋርዳሉ። ራሳቸውን ” ብስብስ” ይላሉ። ሌሎች ” ብስብስ” ሊሏቸው ሲሰባሰቡ አፈሙዝ ይወድራሉ። ግን ራሳቸው ለራሳቸው ባወጡት ስም፣ አይ እቺ አገር ቦሰና ሲከፋት የምትለው ነው።
ቦሰና ሲነሳባት ክፉ ናት። ደጎል እንኳን ገሸሽ ይላል። ቦሰና “አሁን በደብረጽዮን እና በሌሎቹ መካከል ምን ልዩነት አለ?” አለች። “ሁሉም ሲበሰብሱ ደብረጽዮን ሽቶ ይነፉ ነበር?” ጠየቀች። አስከትላ ” አሁንስ ማይሙን እንኳ ማታለል አቃታቸው” እንደ ልማዷ ጢቅ አደረገች።
ሰዎቹ አያረጁም? አይሰለቻቸውም? ማረፍ አይፈልጉም? እንደ ሰው አርፈው ማለፍ አይመኙም? ለመጪው ትውልድ አስረከበው ቀሪ ዘመናቸውን በአደባባይ ቡና እየጠጡ፣ ካሻቸውም እያስቀደሱ አይኖሩም? ሰው ነብስ ካወቀበት ጊዜ ጀመሮ በቁማር አድጎ እንዴት እንደቆመረ ይገነዛል? ቤተስብስ አይመክርም? በቃ አባባ አይልም? አይበደው ደነዘዘው። ሰው እንዴት ነጻነት ይጠላል? ስብሃት ነጋ፣ አባይ ጸሃዬ፣ ስዩም መስፍን፣ አርከበ እቁባይ፣ ራስዋ አዜብ፣ አባይ ወልዱ፣ የአቶ ባሌማ ልጅ…. ሁሉም በተፈጠሮ ሂደት እንኳን አትሸነፉም? የጤናችሁ ሁኔታ አያሳስባችሁም….. ሱስ ማለት ይህ ነው!! በሽታ ማለት ይህ ነው። በሙጋቤ እየሳቁ ፣ ብዙ ሙጋቤዎችን አቅፎ መኖር!!
ያበደው ተስፈነጠረ። በቁጣ ተርጎመጎመ። ችግር በመጣ ቁጥር የገዢዎች መሃላ አጥወለወለው። ሁሌ ቀለም መቀያየር፣ መታደስ፣….. ባትታደሱስ? እንደ ሸተታሽሁ ብትኖሩስ፣ ሕዝብ ምን አገባው። የትኛው ፍቅሩ? የት መረጣችሁ? የት ነው ውል የገባችሁት?… በታመማችሁ፣ በተቧደናችሁ፣ ግራ በተጋባችሁ ጊዜ ሁሉ ” ቆይ ልንታደስ ነው” የምትሉት? ሕዝብ ምን አገባው። ያለ እናንተ ሌላ ትውልድ የለም? ያለ እናንተ አገር ሌላ ዜጋ የላትም? ነው ወይስ ነገሩ ምንድን ነው? ያበደው ጠየቀ!! ለውጥ ለሚፈልጉ ሁሉ አባይ ተነስተው ደብረጽዮን ቢመጡ ባይመጡ ምኑ ነው? ሙክታር ተባረው ለማ ቢተኩ ባይተኩ….
በፌደራሉ ቋንቋ እናውራው ፣ በመለስ አባባል እንተንትነው። ህወሃት ታደሰ አልታደሰ ለነቀምቴ፣ ለነጆ፣ ልባሌ፣ ለአርሲ፣ ለሃረር፣ ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለሸዋ፣ ለአዲስ አበባ፣ ለቤኒሻንጉል፣ ለጋምቤላው…. ሕዝብ ዜና ነው? ምኑ ነው? ልክ “የአክሱም ሃውልት ለሌላው ምኑ ነው?”
ቦሰናም በዚህ ሃሳብ ትስማማለች። ደጎልም በዚህ ጉዳይ ጭራውን አይቆላም። አንገቱን ቀና አድርጎ ነው ድጋፍ የሚሰጠው። ጉድ እኮ ነው…. ለሁለት የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ፣ በሰላ የሂስ ጅራፍ ተገረፉ…. እና ምን ይሁን? የናንተ መሰዳደብ የሕዝብን ጥያቄ ይመልሳል?
ያበደው ጮኸ። አገር ነፍራለች፣ አገሪቱ ልክ አይደልችም፣ የቀለም ቅብ ፖለቲካ አይሰራም። እባካችሁን ስሙ፣ ሁሉም ቦታ አደገኛ ቀጣና እየሆነ ነው፣ ሁሉም ያልፋል፣ ለመጪው ትውልድ ስትሉ፣ ለፈጣሪ ስትሉ፣ ለህጻናት ስትሉ …. አሁን የተነሳውን ሰደድ እሳት እናጥፋ፣ ቆራጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ ወስኑ፣ ሁሉንም አካቱ፣ ሁሉንም ሰብስቡ፣ ሕዝብ እንዲወስን አድርጉ፣ ስሜት ጎሿል። ጥይት መልስ ሊሆን አልቻለም። ከጠመንጃ ጋር የሚጋፈጡ ….. ደም በፈሰሰ ቁጥር ….. ሰላም ሁኑ !!ጉድ ነው። አጃኢብ ነው። የጥልቅ ተሃድሶ መንፈስ!!

ለ “ገዳዮች” – ውሮ ወሸባዬ

…. ውሮ ወሸባዬ…. ጀግኖች… እናትን ከልጅ ነጥላችሁ የምታርዱ፤ እናንተ ” ምጡቃኖች” የዚህ ሂሳብ ቆማሪዎች እልል በሉ፤ አግሱ፣ ደም ጠጡ፣ የተቆረጠ አንገት አቅፋችሁ ደንሱ፤ እናንተ የእርግማን ሽንቶች፣ እናንት ደም የማትጠግቡ የሃጢያት ሁሉ ኩይሳዎች፣ በሰው ነብስ ላይ የምታመነዘሩ ውርጃዎች፣ አዛውንትን የምትሰይፉ ክፉዎች፣ ታዛዦች፣ አዛዦች፣ …… የለጋ ህጻናት እምባ ይፍረድባቸሁ… የተጋታችሁት የንጹሃን ደም በፍርዳቹህ ላይ ይንተክተክ….. አዎ … ማንም ሆነ ማን የራሱ ጉዳይ… ያበደው ተስፈነጠረ ..

…አብረን አልበላንም፣ ገንፎ በማንኪያ ሳናጥብ እልተጎራረስንም፣ በደም ተነክሬ …አንቺና ባለቤትሽ… ” እራሷን መቆጣጠር አቃታት። አነባች። ሌላዋ ተቀብላ ስም እየጠራች ” እድሜያችንን አብረን ኖርን? አሁን ወደየት እንሄዳለን። ዛሬ ምን ተፈጠረ? ምን ተገኘ? ይህ ቀን ያልፍል… አነባች። ሁሉም እየተቀባበሉ አነቡ። ለሚሰማ !! አንዱ በዘሩ የተነሳ የተወነጀለ መምህር የቀረበበትን ውንጀላ መስማት ደክሞት፣ የሚሰማውን ማመን አቅቶት አነባ ። ሌሎች በክራት መንፈስ ተጀነኑ። እየሰሙ እንዳልሰሙ ሆኑ። ይህ ሁሉ ሲሆን ቦሰና ነበረች። ይህ የሆነው ኦሮሚያ ውስጥ ነው።

ኢተያ ፈርታ ነበር። ኢተያ ሳትጨልም ጨልማ ነበር። ኢተያ ከተማ ውስጥ የነበሩ የአማራዎች ፈርተው ነበር። በስጋት የሆኑትን በሙሉ ለያበደው በውቅቱ አጫውተውታል። በኢተያ የምርጫ ጣቢያ ጁነዲን ሳዶና አባ ዱላ ተገንድሰው ነበር። እነሱ ዳግም እንዲመረጡ “በታዘዘው” መሰረት የነብረው ቅስቀሳ አደገኛ ነበር። ቅስቀሳውን የመሩት አቶ ጁነዲን ነበሩ። ዛሬ ምን የሰማቸው እንደሆነ ያበደው መረጃ የለውም። ግን እውነት ነው። 

“ክርስቲያን እንዴት መረጣችሁ?” በሚል ቅስቀሳው ውስጥ ለውስጥ ተበተነ። ብርድልብስ በነፍስ ወከፍ ታደለ። ቅስቀሳው መልኩ ሌላ ነበርና ” አማሮች” – ክርስቲያኖች ስጋት ገብቷቸው ….. ያበደው ነኝ። ሰላም ጤና ይብዛላችሁ። ለ ” ገዳዮች” እንኳን ደስ አላችሁ። ደም አልጠግብም ለምትሉ ጭራቆች… ያበደው ሰላምታውን ሳይጀምር አናቱ ጋለ። ምራቁ ወፈረ። ሰው እንዴት ሰውን ያርዳል? ጠየቀ። መልሱን ማግኘት አለመቻሉ አዞረው። ዞረበት። ሰው እያረዱ እንቅልፍ የሚተኙትን አሰበ። እረዱ የሚሉትን አሰበ። መልስ የለም። ማስረጃም ሊቀርብበት አይችልም……. ጮኸ…. ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። ወገን ወገኑን በላ። ገና ይበላል። አሁንም ያልደነገጡ አሉ። የሚታበዩና የሚጋቱት ደም የሚያስጎመጃቸው የደም ጥመኞች አሉ …..

ውሮ ወሸባዬ…. ጀግኖች… እናትን ከልጅ ነጥላችሁ የምታርዱ፤ እናንተ ” ምጡቃኖች” የዚህ ሂሳብ ቆማሪዎች እልል በሉ፤ አግሱ፣ ደም ጠጡ፣ የተቆረጠ አንገት አቅፋችሁ ደንሱ፤ እናንተ የእርግማን ሽንቶች፣ እናንት ደም የማትጠግቡ የሃጢያት ሁሉ ኩይሳዎች፣ በሰው ነብስ ላይ የምታመነዘሩ ውርጃዎች፣ አዛውንትን የምትሰይፉ ክፉዎች፣ ታዛዦች፣ አዛዦች፣ …… የለጋ ህጻናት እምባ ይፍረድባቸሁ… የተጋታችሁት የንጹሃን ደም በፍርዳቹህ ላይ ይንተክተክ….. አዎ … ማንም ሆነ ማን የራሱ ጉዳይ… ያበደው ተስፈነጠረ።

አዎ በየዋሃን፣ በንጹሃን ላይ ሰይፍ የመዘዛችሁ፣ ያስመዘዛችሁ፣ ጨፍሩ፤ ስለታችሁ ደርሷልና ደንሱ፤ ሃሳባችሁ ጫፍ ደርሷልና አውካኩ፤ ምሳችሁ ሞልቷልና አጓሩ፤ ግብሩ ገብቷልና የወንድሞቻችሁን ደም የሰፈራችሁበትን ዋንጫ አናታችሁ ላይ እየደፋችሁ በሙታን መንፈስ ስከሩ… መርጋት፣ ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ የወደፊቱን ማየት… አልተቻለም። ሁሉም በየፊናው ታውሯል። ጥቂቶች ቢያስጠነቀቁም ሰሚ የለም። ያበደው አይኑን ጨፈነ፤ አሰበ….. አሰበ…. በየጫካው የተከነቸሩትን፣ ፈርተው የተሸሸጉትን ጎበኘ… መፍትሄ የለም።

አማራጭ የሚባሉት ይህንን ሁሉ ጉድ እያዩ ወደ ልባቸው ሊመለሱ አልቻሉም። አሁንም ይነታረካሉ። የደም ዋንጫ ሞልቶ እየፈሰሰም ልባቸውን መሰብሰብ አልቻሉም። አብሮ መስራት እንኳን ባይቻል መሰዳደብ አላቆሙም። እነሱ ገዳይ ባይሆኑም፣ ለአራጆቹ ገጀራ አቀባዮች መሆናቸውን ዘንግተዋል። ልቡናቸው በወንበር ፍቅር ስለተዘጋ ማርጀትና መሞት እንዳለ እንኳን አያስቡም። አቶ መለስ ተሸውደው ይህንን የመሰለ ፍሬያቸውን ሳያዩ ሞቱ። ዋንጫውን ሳያነሱ አመለጡ…. ባለሳምንት!!

በአራቱም መዓዘናት በሞት ቡፌ ደምቀናል። ጥይት፣ ገጀራ፣ ዱላ፣ ቢላ፣ መርዝ… ሌላም አለ። ወገን ይረግፋል። ጠኔና ረሃብም ያረግፋሉ። ለመርገፍ የተዘጋጁ ብዙ ናቸው። እየኖሩ የማይኖሩም አሉ። ላለመርገፍ የሚውተረተሩም አሉ። መርገፍ አጠገባቸው ድርሽ እንደማይል ያመኑም አሉ። ኢትዮጵያ እንዲህ ሆና አረፈችው።

ቦሰና ተስፋ በሚቆርጡት ላይ ትበሳጫለች። “አሁንም ተስፋ አለን” ትላለች። ጸሎት የሚያስፈለጋቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ትናገራለች። አዎ !! እንደ ቦሰና ያሉ የዋሃን ባይኖሩ ሃያ ስድስት ዓመት የከነፈው የዘር ጣጣ ባጠፋን ነበር። አዎ ባቡሩ ይከንፋል። ሾፌሮቹ መንዳት እንጂ ማቆም አያውቁም። አቁመው ስለማውርደና ወርዶ ስለማረፍ ማሰቢያቸው ወድቋል። መክነፍ ብቻ… መክነፍ… መድረሻው የት ይሆን? ያበደው መሃረቡን አወጣ። አይኑን አባበሰ። ደጎልን አየው። ደጎል ተሽኮረመመ፤ ደጎል ይገባዋል። “ሰበር ዜና” ተብሎ ጉዳችን በሚጠብቀን አካል ሲነገረን ደጎል ዘሎ ከቤት ወጥቶ ነበር።

ዘመን ሲሸት እንዲህ ነው። ዘመን ሲከረፋ እንዲህ ነው። ማዘዝ፣ መአስቆም፣ ማቀብ፣ መገሰጽ አልተቻለም። የፈረሱ ነገሮች በዝተዋል። መፍትሄው ግራ ነው። ሁሉምበያለበት ይጮሃል። ሁሉም በያለበት ይሳደባል። ወገን እየታጨደ ነው። ወገን ብሄር የለውም። ወገን ወገን ነው። ወገን ወገን ናት። ወገን ቆም እንበል። የሞላላችሁም ሆነ የጎደለባችሁ ቆም በሉ። አሻግራችሁ ተመከቱ፤ የመውጣትና የመውረድ በሽታ የሚያሰቃያችሁም ረጋ በሎ፤ ስለ መጪው ትውልድ፣ ስለ እናቶች፣ ስለ አዛውንቶች፣ ስለ ….. ያበደው ለመነ… አሁን ያበደው ማረፍ ፈለገ። ውሮ ወሸባዬን ጋበዘ ለ” ገዳዮች” ውሮ ወሸባዬን ዘፈነላቸው። ውሮ ወሸባዬ !!

 

አዲስ አበባም ነፍጠኛ ? አዲስ አበባ ትፍረስ? ቡፋዎች !!

yabedew-2ለኢትዮጵያ ሰላም ከሰጠ አዲስ አበባ ስሟ ብቻ ሳይሆን ህንጻዎቹእም ይፍረሱ። አሃ – ለካ ህንጻው ባለቤት አለው። ባለቤት የሌላት አዲስ አበባ ናት። አዲስ አበባ!! … አዲስ አበባዬ ፣ አዱ ገነት… አዱዬ የሁሉም ጎጆ!!… ያበደው አዘነ… ከምር አለቀሰ… ደህና ስንብቺ ብሎ ሊሰናበታት ሞከረ። አዲስ አበባን ሊሰናበት ቃላት ፈለገ … አልቻለም… አንባው አነቀው። ሳግ ጉሮሮው ውስጥ ተቀረቀረ። አዲስ አበባን ገሎ መገነዝና ወደ መቃብር ማውረድ ቀላል እንዳልሆነ ታሰበው። በትልቁ፣ በረጅም፣ በጥልቅ ….. ተነፈሰ!! ጥልቅ፣ ጥልቁ፣ …. ቡፋ!!

ዳግም ለቅሶ፣ ዳግም የሃዘን አዋጅ፣ የሃዘን ማቅ፣ በየመንደሩ፣ በየክልሉ፣ በየጉድባው… በፊነፊኔ ታላቅ ድንኳን ይጣል፤ በየብሄረስብ ቋንቋ ይለቀስ፣ አማራ ሙሾ ያውረድ፣ ደቡብ እያለቀሰ ይጨፍር፣ ቤተ መንግስት ይበርገድ፣ እህል ካለ ንፍሮ ይቀቀል…. ለዚህ ዓላማ “ሆነ ብለው” የተሰዉ ሁሉ አጥንታቸው ይለቀምና በክብር ይከማች፤ መፈክር ይዘጋጅ … ” ይህንን አዋጅ ሳትሰሙ ላለፋችሁ ሃዘናችን ትልቅ ነው” የሚል መፈክር አገሪቱን ያጥለቅልቅ። ከሁሉም በላይ ” ባለ ራዕዩ መሪያችን ኮራንብህ” የሚል ጥቡቆ ህዝብ ሁሉ ይልበስ። የሙታን መንፈስ የሚያናገሩ ይፈለጉና የባለ ራዕዮችን መልዕክት ሰምተው ያሰሙ….. ኮተት ሃሳብ ሲል ያበደው ሙዚቃውን አቆመ።

” አንድ ላይ ሆነን ተለያይተናል” ዘፈኑ ነበር። አዎ !! የኋላው ከሌለ የፊቱ አይኖርም። አሁን ያለው የአዲስ አበባ የተለያዩ መጠሪያዎች ይቀየራሉ ሲሉን ኖረው አሁን አበሰሩን። አዋጅ ታወጀ።  የድሮዎቹ ገዢዎች ብቻ ሳይሆኑ ራስዋ አዲስ አበባና መንደሮቿም ጨቋኞች ሆኑ። አዲስ አበባ ነፍጠኛ ሆነች።  እንግዲህ አዲስ አበቤ አማራጭህ ገዢህን እያመሰገንክ አዲሱን ስም ማጥናት ብቻ ነው። ታክሲ ስትሳፈር ሌላ ሰፈር እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ። መቼም የእኛ ነገር እና የአገራችን ጉዳይ የሚተነበይ አልሆነም። ያደቆነ ሳያቄስ እንዲሉ!! መለስ አዲስ አበባ ወይባ፣ ፊንፊኔ ሆና፣ ቅርሶቿ ሁሉ የባዕድ እንደሆኑ ተቆጥሮ እንዲመክኑ ሲደረጉ ሳያዩ አለፉ። ያበደው ያዘነው በዚህ ነው። ባለ ራዕዩ ራዕያቸው ሲፈጸም ሳያዩ … ይህኔ ነው ደረት መምታት። ለአዲስ አበባ ሳይሆን ህልማቸውን ሳያዩ ” ለተሰውት” ገናናው መለስ ዳግም ሃዘን እንቀመጥ ሲል ያበደው የጠየቀው ለዚህ ነው። የምትቃወሙ ካላችሁ …. አሳዩን!! አማራ ክልል የዝግጅቱ አስተባባሪና ስፖንሰር እንዲሆን ያበደው ሃሳብ ያቀርባል። ግን ደግሞ ችግር አለ። ለካ አማራ መደራጀት የለበትም የሚ አሉ!!

ያበደው የለም ነበር። ያልነበረው በራሱ ፍላጎት ከተወሰኑ ጉዳዮች ራሱን በማቀቡ ነው። ራስን ማቀብ ለጊዜውም ቢሆን ያው አለመኖር ነው። አንዳንዴ እየኖሩ ካለመኖር፤ ጭራሹኑ አለመኖር ይሻላል። ግን ድፍረት የለም። ሳይኖሩ መኖር የተሻለ ነው የምትሉ ግፉበት። ጠኔ መንደር ኦጋዴን ሂዱና ምርጫችሁን አስተካክሉ። ኦጋዴን፣ ሶማሌ ክልል ግቡና ውጡ… ያንን ጉደ ተሸክመን ሌላ ነገር ብሶብናል።  አዲስ አበባ፣ ይቅርታ ጨቋኟ አዲስ አበባ፣ ነፍጠኛዋ አዲስ አበባ ….. አሁን አሁን ባትኖር ይሻላታል። ለነገሩ አሁን ከጫፍ ነች። ልትሽቀነጠር፣ ልትሰዋ፣ እዛው መለስ ያሉበት የ ” ባለራዕዮች ሰፈረ” ልትሄድ!! ደረት ሳይመታላት በማጉረምረም ልትቀበር!! ያበደው ዘለለ። “እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲል አዋጁን ያወጁትን በሙሉ …. አላቸው። የያበደው ምርቃት የገባችሁ አክሉበት።

ማጉረምረም ከባድ ነው። ዝምታና ማጉረምረም መጨረሻቸው ክፉ ነው። ጉምጉምታ እንደ ደራሽ ጎርፍ ነው። ሲፈነዳ ያገኘውን ሁሉ ይጠርጋል። መደገፊያ ፍለጋ እንኳን ጊዜ አይሰጥም። ድህነት፣ ረሃብ፣ ችጋር፣ መገፋት፣ መናቅ፣ መጠላት፣ ከብሄርተኛነት መርዝ ጋር ተደፍድፈው እየተጉመተመቱ ነው። ድፍድፍ ይፈላል። ፈልቶ ይገነፍላል። ያበደው አሰበ። ይህ ድፍድፍ እንዴት ሊመክን ይችላል? እንዴት? እንዴት……..

ቦሰና  ” ነ ደደቤ” ብላለች። ደከመኝ ማለቷ ነው። አዎ! ይደክማል። በነጋ ቁጥር በጥፋትና የነበረን በማፍረስ መኖር። የነበረ እንዴት እንደሚጠፋ በማውጠንጠን መኖር። ታሪክ አልባ ለመሆን መማማል። የባህር በር ለማስረከብ መቆመር። ከተማና ቅርስ ለማጥፋት መትጋት። ለዚህ ሁሉ በጅት መከስከስ። ያበደው እንባውን አቀረረ። ያበደው ሲያዝን ወሻውን ያየዋል። ደጎልም አዝኗል። የሚያዝነው ለራሱ አይደልም። የሚያዝነው እሱን “ውሻ” ለሚሉት ሰዎች ነው።

ደጎል ቲቪ ሲከፈት ተስፈንጥሮ ይወጣል። ሁሉንም አይነት ሚዲያ ጠልቷል። ቦሰናም እንደሱ ነች። “ከዛም ከዚም መርዝ ይረጫል” ትላለች። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመንደርና በቀበሌ ስሞች ውዝግብ ላይ ነን። በዚህ ባለቀ ዘመን 8 ሚሊዮን ችጋር ያቃጠለው ህዝብ ያላት አገር ዳቦን ረሰታ ለቀበሌና ለመንደር ሰያሜ ትኩረት ሰጥታ፣ በጀት መድባ፣ የአየር ሰዓት ሰጥታ… ትኳትናለች። ቦሰና ” አይ አዲስ አበባ ስንቱን ተሸከምሽ?” ስትል ሃዘኗን ትገልጻለች። አዲስ አበባ የደጎች ከተማ በአደገኛ ተምች ተመታች።

አልበቅልም ብሏል። የበቀለውን ተምች ይበላዋል። ከተምች የተረፈውን ተስማምተን እንዳንበላ የዘር ተምች እያመሰን ነው። የዘር ተምች!! ዘረኝነት የሰው ልጅን ወደ አውሬነት የቀይራል። ሰው አውሬ ሲሆን አበቃ!! አሁን በፍጥነት ወደ አውሬነት እየሮጥን ነው። አውሬ ለመሆን እየከነፍን ነው። በየጥጉ የሚርከፈከፈው ዘይት አውሬ ለመሆን የሚፈረገውን ሩጫ ክንፍ እያበጀለት ነው። ሰከን ብሎ ማሰብ የጠፋ ይመስላል። ባይጠፋም መንምኗል።

ኦሮሞ ጥያቄ አለው። የኦሮሞ ጥያቄ ልክ እንደሌሎች ህዝቦች ጥያቄ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ኦሮሞን ” እንወክላለን ” እንደሚሉት ሌሎችን የመጉዳት አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ለጥላቻ ቦታ የለውም። የኢትዮጵያን ህዝብ ሙሉ በሙሉ የዴሞክራሲ ባለቤት ማድረግ እንጂ ዘር ላይ ተክሎ በማቧደንና ማባላት ልክ አይመጣም። ቦሰና ” በማይም አንደበቴ” እየላች የምትናገረው ነው።

ለኢትዮጵያ ሰላም ከሰጠ አዲስ አበባ ስሟ ብቻ ሳይሆን ህንጻዎቹእም ይፍረሱ። አሃ – ለካ ህንጻው ባለቤት አለው። ባለቤት የሌላት አዲስ አበባ ናት። አዲስ አበባ!! … አዲስ አበባዬ ፣ አዱ ገነት… አዱዬ የሁሉም ጎጆ!!… ያበደው አዘነ… ከምር አለቀሰ… ደህና ስንብቺ ብሎ ሊሰናበታት ሞከረ። አዲስ አበባን ሊሰናበት ቃላት ፈለገ … አልቻለም… አንባው አነቀው። ሳግ ጉሮሮው ውስጥ ተቀረቀረ። አዲስ አበባን ገሎ መገነዝና ወደ መቃብር ማውረድ ቀላል እንዳልሆነ ታሰበው። በትልቁ፣ በረጅም፣ በጥልቅ ….. ተነፈሰ!! ጥልቅ፣ ጥልቁ፣ …. ቡፋ!!

ተስፋ አለ። አዲስ አበባ አትሞትም። አዲስ አበባ ትኖራለች። አዲስ አበባ ማተብ ናት። አዲስ አበባ የሁሉም ቤት ናት። ኦሮሞ መራት ትግሬ አዲስ አበባ የራሷ  ኬሚስቲሪ / ወህድ ነገር / አላት። በጠበቀ ነገር ተገምዳለች። አዲስ አበባ ልጆቿ ወደ አስመራ ሲሄዱ አልቅሳለች። በየመንደሩ አልቀሳ ሽኝታለች እንጂ ከበሮ አልደበደበችም። ዛሬም እነሱኑ አቅፋለች። ይህ ውበቷ ነግም ይኖራል። ይህ ረቂቅ ግን ግልጽ ሚስጥሯ መሰሪነት ዝም ብሎ የሚነደው አይደለም። ማርክሲስቶች አንብንበው የቀመሩት ስርዓት አይመጥናትም። እያስተማረች ዛሬ ደርሳለች። አዎ!! አዲስ አበባ በማያስተውሉ ብትነዳም እሷ ታስተውላለች። ያበደው አንድ ሃይል ነዘረው!! ያበደው ዘለለ… ደጎልም ዘለለ…  አብረው ተነሱ። ያገኙትን የዘር ድንኳን እየመነገሉ ጣሉ። ” አንድ ነን አንለያይም ፤ ለጠላት አንታለልም … ” የሚለውን መዝሙር እያዘሙ አገምሳ፣ ዶቢ፣ሁሩፋ ቦምቢ፣ቢሪቢርሳ ጉስሮ፣ ጨፌ አራራ፣ መልካ ዳቡስ ….. ወረዱ ሁሉም እንደ ድሮው ነው…. ለውጥ የለም!! ሁሉም በቦታቸው ናቸው… ሰላም ሁኑ !! አሁን ያበደው አይጠፋም።

Addisababa oromifa names

‘ብክለት’ – ተኮር ጉዳዮች – በድህነትን አትነገዱ!!

“…እንደ ጥናቱ ድምዳሜ ሁለት አበይት ጉዳዮች ተገኝተዋል። አሁን ሕዝባችን የሚበላውና የሚሸምተው ልክ እንደ አገሪቱ ኢኮኖሚ ስላደገ የሚጣለው ቆሻሻ ብዛት አድጓል። ጭብጨባ…. ሕዝባችን በቀን ሶስቴ ይበቃሃል ቢባልም ባለመስማቱና ከዚያ በላይ በመመገቡ የቆሻሻሻው መጠን በዝቷል።  ስለዚህ ይህ የእድገታቸን ማሳያ ዋናው ምልክት በመሆኑ በበጎ ጎኑ የታየ ሆኗል። ጭብጨባ… በሌላ በኩል የተገኘው ግኝት ሕዝባችን የሚመገበውና የሚጥለው በመበርከቱ ቆሻሻው አካባቢ በመኖር ተረፈ ምግቡን ለመጣል የሚያወጣውን ጉልበት ለመቆጠብ መወሰኑ ነው። ስለዚህ ካሁን በሁዋላ የሲሚንቶ ችግርን ስላንበረከክነው ቆሻሻውን ሲጥሉ ሲሚንቶ እየቀላቀሉ በማሰወገድ  ናዳውንና የአካባቢውን ብክለት  እንዲከላከሉ ቢደረግ ….” የቆሼ አጣሪ ኮሚቴ

ብክለት – ያው መበከል ነው። የተበከለ ሁሉ ንጹህ አይደለም። መበከል ሲያድግ መመረዝን ያመጣል። የተመረዘ መዳኛ የለውም። መዳን የማይችል ብክለቱን ለሌላው፤ ለቤተሰቡ ጭምር ያራባል። ከዛ ሁሉም ይበከላሉ። እናም ይመረዛሉ… የተመረዙ እየበዙ ሲሄዱ ንጹሃንም የተበከሉ ስለሚመስሉ ለመለየት ያስቸግራል። ይህ ሁሉም ጋር ነው። ቄሱም፣ ዲያቆኑም፣ ደብተራውም፣ ተወዛዋዡም፣ ፓስተሩም፣ ሽማግሌዎችም፣ ነቢይ የሚባሉትም… ሃጂውም፣ ሼካውም፣ ወልዩም….. መሪውም፣ ጀሌውም፣ ገዢውም፣ ተቃዋሚውም… ከራስ እንስከ እግር…. ጉድ እኮ ነው!! ከሁሉም ወገን ንጹሃን አሉ፤ ግን ለዛሬ እነሱን ልለፋቸው። ግን ቀናዎች ራሳችሁን መግለጽና ” አያገባናል” በማለት …..

ያበደው ከቆሼ ሰለባዎች ጋር ተሰውሮ ከርሟል። እንደምን ሰነበታችሁ? ቆሻሻ ሆይ የእለት ጉርስ፣ የመኖሪያ ሚስጢር፣ መሸሸጊያ ያደረጉህን በላሃቸው። ያላቸው የሌላቸው ላይ ቆሻሻ ከምረው፣ ከምረው፣ ከምረው….. ግን ለመሆኑ መከመር ጥበብ የለውም? ” ዝም ብለህ ከምር” የሚሉ መሃነዲሶች አዲስ አበባን እንዴት እያነጿት ይሆን? እውነት እንነጋገር ከተባለ ክምር እንደሚናድ የማይረዳ መሃንዲስ ቢገመገም፣ ቢታደስ፣ እስከ ጥልቁ ቢመረመር ምን ዋጋ አለው? ጥልቅ ነገር የምንመኘው እኮ ሜዳ ላይ ያለውን ስናየው ነው።

ቆይ ወገኖቼ፣ ቆሼ ሰፈር አጥር የለውም። በነገራችን ላይ አጥር እንኳን ቢኖረው አደጋው አይደርስም ወይም ይቀል ነበር። ቆሼ ሰፈር አላፊ አግዳሚ አፍንጫውን ጠቅጥቆ የሚመላለስበት ነው። እድሜውም ቀላል አይደለም። “ነዋሪዎች” አቤት ባይሉም ሲሚንቶና አሸዋ የሌለውን ቁልል፣ “ክምር” የሚሉት ክፍሎች፣ ክምር ለዚያውም የቆሻሻ እንደሚናድ እንዴት አያውቁም? አጣሪ ኮሚቴው ምን ይል ይሆን? ልክ እንደ ኦሮሚያ ማጣራት ” መንግስት ከልክ ያለፈ ሃይል አልተጠቀመም” እንዳለው? ባዶ እጁን የሚጮህ ህዝብ ላይ ጥይት ከማዝነብ ውጪ ምን ሊመጣ…. ያበደው ቀባጠረ። አሁንም ቆሼ…… ሲጣራ ” … ባለፉት 25 ዓመታት የተከመረው ሳይሆን የድሮው ነው” ሊባል? ወይስ ” አሁን ዜጎች የሚጥሉት ተረፈ ምርት ኢኮኖሚው እንዳደገው ሁሉ በመጨመሩ አደጋው የእድገቱ አመላካች ነው” ሊሉ?  የማዘጋጃ ቤት መሃንዲሶች ስለ ሬሾ አያውቁም እንዴ? ቦሰናም አሽሟጣለች። የተቆፈረ አፈር እንኳ ሲጋዝ የሚከመርበት የቁመት መጠን አለው። አጥር አፍራሽ መሃንዲሶች ካልሆኑ በስተቀር … እስኪ ለሁሉም ነብስ ይማር።

ቦሰና ቆቅ ናት። ነገሯ ይከብዳል። ስለ አየር መበከል፣ ስለተፈጥሮ መዛባትና የዓለም ሙቀት መጨመር መሪዎቻችን ሲናገሩ ትስቃለች። ” እኛ ተበክለናል” ትላለች። ” እንደውም ተመርዘናል” ስትል ግምገማዋን ታሰፋዋለች። ያበደው ስለመበከል አሰበ። የእምነት ቤቶች ስብከቱን ድህነት ተኮር አድርገውታል። ስብከታቸው ሁሉ ” ማድጋሽ ይሞላል፤ ትዳርሽ ይቃናል፣ ህዘንሽ ከዚች ሰዓት ጀምሮ ተወግዷል፤ ቀንበርሽ ተሰብሯል…” የሚል ነው። ከስብከቱ በሁዋላ ሁሉም ቤታቸው ሲመለሱ ሁሉም እነደነበረው ነው። ያሳዝናል። ትልቁን አምላክ ያሳንሱትና ….. ይህ መበከል ነው።

ሃብታም የበሽታ ጎሬ ስለሆነ  በህመሙ ይሰብኩታል። በፈውስ ያማልሉታል። በልጆቹ ይገቡበታል። ሰው እንዲያስብ፣ እንዲመራመርን የጌታውን ቃል በማጥናት ተረድቶ ” ከእለት ደራሽ የተራ ተሰፋ ስብከት እንዳይወጣ” በጉድለቱ እየሰበኩት ታላቁን የጌታውን ስጦታ እንዳይቀበል ይጎትቱታል። አንዱ ፓስተር በፈገግታ ” እኔ ሰው እያዳንኩ ገንዘብ ብሰበስብ ምን አለበት፣ ቅሪላ/ ኳስ የሚያለፉ ገንዘብ ይዝቁ አይደል ” እንዳለው፤ አዎ!! ብክለት ቀስ እያለ ያድጋል። ቀስ እያለ መርዝ ይሆናል። መርዙ በፍጥነት እየተራባ ዛሬ ሁሉም ግቢውን እያጠረ … በፈውስ ስም ብር ይለቅማል!! አንዱ ከሌላው እየተገነጠለ አባላትን ለማስኮበለል ሰራዊት ያሰማራል። የገባቸውን ግራ ያጋቡዋቸዋል። ያልገባቸውን ከወዲያ ወዲህ ያወዛውዟቸዋል። ” እምነት በስራ ካልተገለጠ እየሉ እየሰበኩ ….” ጎበዝ ቦሰና እንዳለችው ተበክለናል። ንጽሃና ጎሎናል። ከእውነት ጋር ተጣልተናል። 60 ለማይሞላ እድሜ እግዜሩ ቤት ሆነን ለከርስ እንባላለን።

መንግስትም እንዲሁ ነው። ስብከቱ ልክ እንደ ሃይማኖት ቤቱ ድህነት ተኮር ነው። ” በቀን ሶስቴ ትበላላችሁ” ብለው ነው የጀመሩት።”ዋና ጠላታችን ድህነት ነው ድባቅ እነከተዋለን” ብለው አስቃዡን። አሁን ጥሩ ደሃ መሆን ሲያቅት ” ስራ እንሰጥሃለን፣ በቢሊዮን ብሮች በጀት ይዘንልሃል”  ማለት ተጀመረ። ደሃን በድህነቱ ማማለል። ክቡር የሆነውን ሰው በሆዱ ማታለል። አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ባናቱ እየተነሱ ቃል መግባት። በእቅድ የሌለን ነገር ማወጅ። ሲያቅት ” ከረፋን፣ በሰብስን፣ ገማን፣ ተሃድሶ፣ ግምገማ፣ ….. ” በማለት አባላትን ማባረር። ተመልሶ ጭቃ!! ከዚህ በላይ መመረዝ የለም።

ያበደው ይህንን የሚለው ለወቀሳ አይደልም። በበዙ መልኩ ተበክለናል። ቀናነት ተስኖናል። ቀናዎችን በማግለል ቦታ አሳጥተናቸዋል። ፍሬ ያላቸውን ወገኖች ገፍተን ረብ የሌለው ጉዳይ ላይ እንገብራለን። ከእድሜ፣ ከስህተት፣ ከተሞከሮ መማር አቅቶናል። ከቆሸሸ አስተሳሰብ ጋር ተጋብተን እየኖርን ” ቆሼ ሰፈር ቆሻሻ ለተደረመሰባቸው እናለቀሳለን”

ያበደው ዝም አለ። ራሱንም፣ አካባቢውንም ቃኘ። ጠኔ እየገረፈን ነው። ችጋር ምንም የማያውቁ ህጻናትን እየበላቸው ነው። እናት የሚቃትት ልጇን አቅፋ የነጠፈውን “ጡት” አፉ በመወተፍ …  ወደሞት የሚሮጡ ወገኖች ገጠውና ገርጥተው እያየን ነው። ዓለም ይህንን ጉዳችንን እያየ… በየድረ ገጹ እየተለመነልን ነው። ያም ሆኖ አልሆነም። ይኸው ግማሽ ምዕተ ዓመት በእርጥባን ላይ ነን።  ድህነቱ ቤቱን በላያችን ላይ ሰርቶብናል። የሚቀንስ ነገር የለም። እየባሰብን ነው…… አንድም የምንኮራበት ነገር የለም። ከመራብ በላይ አስነዋሪ ነገር የለም። የእኛ ረሃብ በዛ። የህሊናና የልቡና ረሃባቸን ጠነከረ። ትል በሚኖርበት ብስባሽ ውስጥ ኖረን ከሞትን በሁዋላ አሁንም አፋችንን እንከፍታለን። ያበደው ተንቆራጠጠ። የሚደርገው ጠፋው።

አገሪቱ ቢዘረዘር የማያልቅ ጣጣ ውስጥ ወደቃ እያቃሰተች ነው። የማይተዋወቁ ተፋቅረው ሲኖሩ እኛ ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክመን በጎሳ እንባለለን። በቋንቋ እንወዛገባለን። በዘር ተቧድነን እንሞሻለቃለን። ጠኔ የሚጨፈጭፈን አንሶ … ያበደው እንባው አይኑንን ሞላው። ሆድ ባሰው። መቼ እንደ ሰለጠነ ሰው …. አሁን የሚያስፈለገው ……..

ያበደው ዘለለ። ተቆናጥሮ ተነሳ። ምራቁን ጢቅ አደረገ። እንደ ልማዱ ” አዋጅ አዋጅ” ለማለት ቃጣው ። ሃይሉን ሰበሰበና አዋጁን እያውጀ …. ወደድንም ጠላንም ተበክለናል። በቅዠት የ60 ዎቹ ትውልዶች የነደፉት ስትራቴጂ ድምሩ ክሽፈት ነው። ያ- ትውልድ እያላችሁ አትመጻደቁ። ያ – ትውልድ ቋንቋው ደም ነው። ከዚህ ኡደት የሚያወጡን መሪዎች ያስፈልጉናል። የደም ፖለቲካ ይቁም። ዳቦ ዳቦ ዳቦ ዳቦ ዳቦ…. እንዴት እንደምንበላ እንምከር። ድህነት ተኮር ስብከት ይቁም። ድህነት ላይ የተንጠለጠሉ ስብከቶች በቃን።  በድህነት ስም ንግድ የቂም። ህይወታችንንም፣ ቤትችንንም፣ ኑሯችንንም የምንመራው ራሳቸን ነንና ድህነትን የስልጣን፣ የገቢና የኑሮ ስልታችሁ ያደረጋችሁ ተው!! እናንተ “አያገባንም” ብላችሁ የተቀመጣችሁ፣ ስትሞክሩ ሰሚ ያጣችሁ፣ እያወቃችሁ ዝም ያላችሁ፣ ተነሱ!! የተጥቀላላችሁበትን ሽል ስበሩ… እናንተ የምድሪቱ መደሃኔት ትሆኑ ዘንድ በድህነት ስብከት ላይ ተነሱ…..

ያበደው አመመው። ረጋ ማለት አለበት። አፍቃሪዋን የማታውቅ፣ ሲያፈቅራት ስትግደረደር የነበረች፣ ታግሶ ታግሶ ከተለያት በሁዋላ ልትቆጣጠር የምትሞክር ሴት ታሪክ ትዝ አለው። እሷን እያሰበ ከገባበት ሃዘን ለመውጣት ታገለ። ቦሰና ይህችን ባለ ታሪክ ” የዞሮባት” ስትል ታዝንላታለች። የተለያት ጓደኛዋ ግን መታከም አለባት ባይ ነው። ዋይ ዋይ ተለያየን ዋጋ የለውም። አፍቃሪንም ለማወቅ አቅም ያስፈለጋል። አለበልዚያ በነጋ ቁጥር እንደ ፌስ ቡክ ትግትግ / ቻት ህይወት በቅዠት ይጠቃለላል። አለያም ሎተሪ ይደርስና…. አሁን ያበደው ቦሰና ጎን ነው። ደጎል ደብሮታል። መናፈስ ይፈልጋል። እዚህ ደጎል ከሰው በላይ መብት አለው። ሰላም ሁኑ!!

ባለፈው የወደፊቱን አመንዣጊ ትውልድ

ዛጎል ዜና ፡- ልቀቅ፣ ልቀቁን፣ ውጣልን፣ ውጡልን፣ ሂድልን፣ ሂዱልን፣ ጥፋ፣ ጥፉልን፣ ውደም፣ ውደሙ፣ ሙት፣ ሙቱ እለቅ፣ እለቁልን ….. ከንባታ ከጎንደር ወጣ፣ ጉራጌ ከኤርትራ ፈለሰ፣ ኦሮሞ ከኬንያ መጣ፣ ሃደሬ … የድሮው የሚጎትተን ህዝቦች፣ የወደፊታችንን በቀድሞው ጉዳይ የምናመነዥግ… በስደት የማናውቃቸውን ተጠግተን እየለመንን እየኖርን፣ የራሳችን ወገን ላይ ስደት የምናውጅ… አድሮ ማንሰለጥን… ታሪካችን የወደፊት እድላችንን አንቆ እንዲገለው የምንማማል …..
እኛ ጊዜው በትክክል በማይታወቅ የሩቅ፣ በጣም የራቀ፣ በልጆች ቋንቋ እ እ እ እ ሩ ቅ ቅ ቅ ቅ ቅ ዘመን ወደሁዋላ ሄደን እንባላለን። ዛሬ ”አሜሪካዊ” የሚባሉት ቅድመ አያቶቻቸው አውሮፓ ናቸው። ዘር ቆጥረው ሲቧጨቁ ግን አንሰማም። 200 ዓመት ባላስቆጠረ የቅርብ ታሪክ ይኖራሉ። ጸብ የለም። እኛ ከክርስቶስ ልደት በፊት ተፈጸመ ወይም በተመጣጣኝ ጊዜ “ሆነ” በተባለ ታሪክ እንባላለን። “ለወደፊታችን ምን ይጠቅመናል” ብለን ማስብ የምንጀምረው መቼ ነው። 10 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ርሃብ እየደፋቸው፤ እኛ ገና በደምና በስጋ ጉዳይ ዘር ቆጠራ …. ማፈሪያዎች ነን። የኢትዮጵያ ችግር በዘር መባላት ይፈታል? ያበደው እንባው አይኑን አጠበው። ሳያስበው አለቀሰ። ገዢ፣ ተገዢ፣ አጎብዳጅ… ሁሉም ከሽፈዋል።
ኢህአዴግ በህግ አገሪቱን እስከመበታተን የሚያደርስ ውሳኔ ያጸደቀ እለት ሁሉም ነገር አብቅቷል። መለስ ዜናዊ ያንተ ቱርፋት ይህ ነው። ዛሬ ተከበናል። ጠላቶቻችን አፍንጫችን ስር ገብተው ጦር እያደራጁ ነው። ጅቡቲ፣ አሰብ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌ… ተከበናል። መለስ አገሪቱን ባህር አልባ አድርጎ በክብር ተቀበረ። “የገደለሽ ኮራ….” አፍረትህ ብዙ ነው። ያበደው ክጥንት ጀምሮ ለመለስ ክብር የለውም። አጠገቡ ካሉት ባለደረቦቹ ጋር መቅረጫውን እያስቆሙት ተወያይቷል። ብዙዎቹ ያሙት ነበር።
በባለቤትነት ጉዳይ የታመምን፤ አንድ ጥይት ሲተኮስ እኛ፣ እኔ፣ ተኮስኩ፤ ግብግብ፣ ሕዝብ ሲያምጽና ሲቆጣ የኮፒ ራይት ግብግብ፣ በአዝማችነት ስም ለመጠራት ከተተኮሰው ጥይት በላይ የቃላት ጦርነት፣ አንድ አስተያየት ሲሰጥ ጦርነት። ልዩነት የሚባለውን ነገር ለማሳየት ስድብ፣ ውግዘት፣ ርግማን፣ ሰው አስተያየት የመስጠት መብቱን በስድብ መለጎም፤ ጊዜው የነጻነት ነው። ሰው ወደ ግልጽነትና ነጻነት መጓዝ አለበት። በነጋ ቁጥር ነጻና ግልጽ ወደ መሆን መራመድ፣ መቅረብ ግድ ነው። ዘመኑን መሆን ያስፈለጋል ። እዚህም እዚያም አፈና አይሰራም። ዛሬ በነጻነት የማይደረግ ነገር አደሮ ዋጋ ያስከፍላል። ሃይማኖቱም ቤት እንዲሁ ነው። ኢየሱስ እየተሰበከ አደረጃጀት አለ። ያበደው ምራቁ ወፈረ። ማለት የሚፈለገውን ከማለት ሲሸበሸብ አፉ ውስጥ ምራቁ ያብጣል።
ያበደው በዝምታ ሰነበተ። ሲምታታበት በቄጤማና በሃሪቲ እንደተለከፈ ባለ ቆሌ አይንከወከውም። በዘርና በጎሳ ጥላቻ የውቃቢ መንፈስ እንደተጠመቁ እዛም እዛም አይረግጥም። የቦሰናን ምክር ተግባራዊ ያደርጋል። ቦሰና ” የማሪያም ምሩቅ ናት” ራስዋን ” አዋቂ” ከሚሉት ባትደምርም፣ ያበደው ግን ይመካባታል። “ኤጭ” ካለች ነገር አለ። ታወርደዋለች። መገልፈጥ አትወድም። ሰሞኑን እሷም ታማለች። “ምን ቢደረግ ይሻላል” እያለች ማቃሰት ላይ ነች። ” ተወረናል” ትላለች። ሁሉም ነገር ደስ አይልም ባይ ነች።
ያበደው አንድ ሙዚየም ውስጥ እየጠየቀ ጎበኘ። ከዛ ወጣ። ቁጭ አለ። አሰበ። ሰዎቹ ታሪካቸውን ባግባቡ አስቀምጠወታል። ታሪክ ያው ብርዝ ነው። ጽድት ያለ ታሪክ ብሎ ነገር የለም። እዚህ ነጮቹ ሲናገሩ በየጊዜው የሚሻሻል አዲስ ግኝት ካለ ይታከላል። በምንም ምክንያት ግን ታሪክ የወደፊታቸውን እንዲመራ፣ እንዲጫን፣ እንዲጎዳ…. አይፈቅዱም። ለታሪካቸው ክብር አላቸው። ነገር ግን ታሪካቸው በወደፊት ጉዳያቸው ላይ ጥላውን እንዲጥል ….. እኛስ? ያበደው ጠየቀ።
እኛም ገና ጥርብ ነን። በታሪክ ስንጋጭ ይኸው 21ኛው ክፍለ ዘመን ደረስን። በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ገና የጋራ ባንዲራ የለንም። የደቆሰንና የገደልን በሽታ መለየት ቀርቶ፤ ህመሙ የት ጋር እንደሚሰማን ለመረዳት አልታደልንም። ይቅርታ መታደል ብሎ ነገር የለም። አልቻልንም። አቅቶናል።በእድል ታሪኩን ያከበረ የለም። በእድል ድህነትን ያሸነፈ የለም። በእድል በምግብ ራሱን የቻለ የለም። በእድል ፋብሪካ የገነባ የለም። በእድል የምድር ሃብትን የዛቀ የለም። ያበደው ሳቀ። አላሙዲን ሰይፉ ከሚባለው / መቼም ራሱን ጋዜጠኛ አይልምና/ ኢትዮጵያ ችግሯ ተቀርፎ ለማየት ምኞት ሲያልሙ ሰማን። ይዘው ከሚመኙ ለምን የዛሬ 20 ዓመት እሰራዋለሁ ያሉትን አይሰሩም። ለእኛ ሲሉ ሳይሆን ለቢዝነሳቸው… እኛ አገር ለዘፋኝ ሁለት ሚሊዮን ተሰጠ ሲባል ማበድ እንወዳለን። አዝማሪ ማስጮህ አላቸው የሚባሉት ሰዎች ጥበብ ነው አሉ….
ቢጣራ ከክርስቶስ ለደትም በፊት ሊሆን በሚችል ታሪክ መቧቀስ ምን ያደርጋል? እሱንስ ለማወቅ መጎርጎሩ የት ያደረሳል? ቢታወቅስ ምን ይጠቅማል? ወደፊታችንን ከሚያጭደው በቀር ምን ሊፈይድ? የዘር ነገር መቆሚያ የለውም። በተጫጨድ ነው። ከዛ ጥቁር ታሪክ በነበረው ላይ ይታከላል። መጪው ትውልድ ይህንኑ ይወርሳል። መርገምት አውራሽ ከምሆን፣ “ቅድመ አያትህ እንዲህ አድርጎኝ ነበር ” ከማለት ሃስብ እንወጣ!! ሳናስበው የወደፊቱን እያጨደን እዚህ ደረስን። እስከመቼ ነው ወደፊታችንን እያመነዠግን የምንኖረው? ኢህአዴግም ቢሆን ይብቃህ። የሄድክበት መንገድ/ የመለስ ቅዠትና ተራ ፍልስፍና/ ይብቃ። የተዘራው የዘር መርዝ ይለቀም ዘንድ ቁርጠኛ ሁን። ሃዘኑ በሁዋል የሁሉም ነው። አዎ!! በፖለቲካ ዓለም በድንገት የሚሆን ነገር የለም። ከሱዳን ጋር በፍቅር ከማበድ ከምትመራው ህዝብ ጋር ታረቅ። ጊዜ የለም። ነገሮች መስመር ሳይለቁ ሁሉም አገሩን ያድን። ያበደው ጥሪው አንድ ነው። አገር መጀመሪያ!!
ለልጆቻችን የምናወራውና የምናወርሰው ችግር ነው። ቂም ነው። ጥላቻን ነው። አንዳንድ ህጽናት መሸከም እስከማይችሉ ድረስ በተመጣጥኝ ምግብ ፈንታ ክፋት እየጋትናቸው ነው። ያበደው እዚህ አውሮፓ ብዙ ታዝቧል። ገና ያልገባቸውና ከአሳዳሪዎቻቸው ያልተማሩ ይበዛሉ። ዛሬም ያልረጠቡ አሳዎች አሉ። በአስተሳሰብ ሳቪጀሪ ዘመን ያሉ፣ በግብር ከፈረንጅ ጋር የሚኖሩ… እባካችሁ እንመለስ። ሰክን እንበል።
የአገር ቤቱን እንተወው። እዚህ ” ስደት” እሚባለው ዓለም እንዴት ነው ኑሮ። በዘር ፣ በቀለም፣ በባህል፣ በአመለካከት፣ በወግ፣ በልምድ፣ በተፈጥሮ፣ በአመጋገብ… የማንተዋወቅ አስጥገተውን እንኖራለን። ቦሰና እንዲህ ትላለች ” እባካችሁ እናስተውል” አዎ መጽሃፉም ” የማያስተውል ህዝብ ይገለበጣል” ይላል። በውስጥም በውጭም ” ሰከን” በርጋታ መፍትሄ ይፈለግ። እንደቀድሞው በማምታታት አይሆንም። ኦሮሞ ከፊት አድርጎ ከጀርባ እየገፉ፣ ደቡብን ዙፋን ላይ አስቀምጦ፤ ዙፋኑ ስር ሆኖ መግዛት ከአሁን በሁዋላ ብዙም አያስኬድም። አሁንጊዜው የደጎል ነው። ደጎል መብቱ ካልተጠበቀ ይቆጣል። ይረብሻል። አንዳንዴም እቃ ይሰብራል። እናም ያበደው ወደ ደጎል ይበራል። ሰላም እንሁን!! ሰላም!!

የ “ኢህአዲግ ዋንጫ” ተሳታፊዎች ድልድል ይፋ ሆነ!!

የ ”ኢህአዲግ ዋናጫ” አንድ ውድድር ነው። በዚህ ውድድር የተሳታፊዎች ገደብ የሚጣለው አንዳንዴ ነው። ሲደምን ህገ ደንብ ይነሳል። ቅድመ ሁኔታ ይሰረዛል። ደመናው ሲገፍ ህግ ባይኖርም ” አለ” ተብሎ እግድ ይጣላል። ይህ ውድድር ታሪካዊ አሻራና መነሻ ይኑረው አይኑረው አዘጋጆቹ ራሳቸው አያውቁትም። ዋናው ፌዴሬሽኑ ግን አዲስ አበባ ቢሮ እንጂ ወኪል የለውም። የውድድሩ የጊዜ ሰሌዳም ውሱን አይደለም። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው የሚዘጋጀው። የውድድር ኤክስፐርቶች እንደሚሉት ውድድሩን መዝግቦ ዓለም አቀፍ እውቅና ለመስጠት የሚችል የታመነ አካልና ቋሚ ህገ ደንብ  እስካሁን የለም።
የተጀመረው የዛሬ 26 ዓመት ግድም ነበር። የዚያን ጊዜ የተሳታፊዎች ቁጥር አይታወቅም ነበር። እጣ ለማውጣት ሲሰበሰቡ ወንበር አንሶ ነበር። የምድብ ድልድል ሲወጣ አግዳሚ ላይ እንዲቀመጡ የተደረጉ ነበሩ። አጨዋወታቸው ፈጣንና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑ መረጃ የወጣባቸው ወዲያው በመታገዳቸው ፉክክሩ ” እንቅልፋም ነበር ” ተብሎ ነበር። ያበደው የሚናገረው ” ነበር”ን  ነው። “ነበር ” ለትምህርት ቢሆን ጥሩ ነበር። “ነበር” ን በ “ነበር” እያጀቡ መንጎድ!! ያበደው ሳቀ!!
በጥቅማ ጥቅም አንድ ቡድን የበላይነት የነበርበት ፉክክር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ አቶ ኢሳያስ የክቡር እንግዳ ነበሩ። ግን ከክብር እንግዳነት አልፈው ተጨዋቾችን አሳትፈው እንደ ነበር ጌዜ ቆጥረው እራሳቸው አምነዋል። ውድድሩ ይግባኝ ሰሚ ስለሌለው ጥፋት እንደ ጥፋት አይቆጠርም። እንደውም ‘እውነት’ ተብሎ ነው የሚወሰደው። አሁንም ያበደው ሳቀ!! ሌሎች ተፎካካሪዎችን ደግሞ በስልት አዳክመዋል የሚሏቸው ነበሩ። አቶ ኢሳያስ ‘ውድድር’ ባይወዱም ይህንን ውድድር ግን ከጥንሱ እስከ ፍጻሜው ተከታትለውታል። በውድድሩ ወቅትና ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የምክር አገልግሎት ሰጥተው እንደነበር ትዝታ አላቸው።
በውድድሩ የራስን መለያ መልበስ አይቻልም ነበር። መለያ የሚመርጠው አዘጋጁ ነው። በግድ የራሳቸውን መለያ መረጡ የተባሉት ከውስጥ የአዘጋጁ ምርጫ የሆነውን መለያ ይለብሱ ነበር። ተመልካቾች ግን የላይኛውን ሳይሆን የውስጠኛውን መለያ ለማየት አልተቸገሩም ነበር። እናም ሁሌም ውድድሩ በአዘጋጆቹ የበላይነት ቢጠናቀቅም ይፌዝበታል እንጂ እንደ ድል አይታሰብም ነበር። ውጤቱ አስቀድሞ ስለሚታወቅ!!
ዳኞችን የሚመድበው አዘጋጁ ብቻ ነበር። ዳኞቹ ስለሚዳኙበት “ህግ” ተፎካካሪዎች አያውቁም። መስፈርቱና መመዘኛው አልተቀመጠምና ለመከራከርና አቤት ለማለት አያስችልም። ዳኞቹ የፊሽካ አነፋፍና የካርድ አመዛዝ የሰለጠኑት ” ከባለ ራእዩ” እንደነበር ተፎካካሪዎች ያውቃሉ። አራጋቢዎች፣ ታዛቢ ዳኞችና እንግዶች የሚመደቡት ከአዘጋጁ ነው። አዘጋጁ ካበጃቸው ተፎካካሪዎች በቀር ዋናዎች ቡድኖች ሁሉን አውቀው፣ እንደማይረቱ ቢረዱም ከውድድሩ አይቀሩም ነበር። አውቀው  ገብተው አማረው ይወጣሉ። አዘጋጆቹ የራሳቸው የውስጥ ውድድር ሲኖርባቸው ለዋናው ተሳታፊዎች ክብር ይሰጣሉ። አጀብ ትላለች ቦሰና። ደጎል ይህን ውድድር ተከታትሎ አይውቅም። ደጎል ባያያውም ተመለካች አልባ ሆኖ አያውቅም። እንደዚህ ሆኖ የሚካሄደው ውድድር በህዝብ አስገዳጅነት ዛሬ አዲስ ስም ተሰጠው። ድርድር!! ወገኖቼ ለካ እርቅም አለ። ቦሰና ቀልቧን የሳበው እርቅ የሚለው ነው።
ሰላም!! እንዴት ከረማችሁ?እንደ ኢህአዴግ ፖለቲካ የወበቃችሁ፣ እንደ እምዬ ኢትዮጵያ ድብርት በቤታችሁና በፍቅራቹህ መካከል የገባባችሁም ተደራደሩ። ለመታረቅ ውጤት ላይ ሳይሆን፣ ምክንያት ላይ አተኩሩ። ውጤት የምክንያት ባርያ ነውና ስለውጤቱ ማሰብ አስቀድሞ ነው። ውጤት ከተበላሸ በሁዋላ ምክንያት እንጂ ውጤት የመስማሚያ መንገድን አያጸዳም። ውጤት ያስተምራል። ቦሰና አባብሉን ባትወደውም ልክ ተናገሮ አናጋሪ እንደሚባለው!!
ቦሰና አስተዋይ ናት። ጸሎቷ አጭር ነው። ሁሉን ከሚያውቀው አምላክ ጋር በረባ ባልረባው አትነታረክም። ” ከተናግሮ አናጋሪ ሰውረኝ” ብላ ከንቱ ጸሎት አታደርግም። “ሰው” ሳይነካ ሌላውን እንደማይነካ ስለምትረዳ፣ አምላኳን በቅንጥብጣቢ ጥያቄዎች አታሰለችም። “የልምድ ጸሎቶች ድሮ ይሰሩ ነበር” ትላለች። ምሳሌ አላት። ” አሁን ሰው አምላኩን እርዱኝ እረዳችኋለሁ ብሏል” ትልና አፏን ታጣምማለች። ” አሁን እሱ በምን የሆን የሚረዳው? ምን አጥቶ?” ትጠይቃለች።  ድሮ ታላላቆች ሁሉም ነገር በየዋህነት ያደርጉ  ስለነበር። እሱም ይረዳቸው ነበር።  አሁን ግን የዋሆች የሚጸልዩት ጸሎት … የቦሰና አካሄድ የተለየ ነው። ያበደው ወደ ጉዳዩ ተመለሰ።

ቦሰና ” እሱ ይቅር ይበልሽ” ሲሏትም አትወድም። እሱ ከላይ ወርዶ ጥንት ይቅር እንዳላት ታምናለች። ሰው ራሱ ይቅር እንዳይል ደረሶ ” አማላጅ” ይሆናል። የወደደ እሱ ብግልጥ እንዳለውና አድርጎ እንዳሳየው ” ይቅር ማድረግ እንጂ ይቅር ይበልህ ብሎ የአሰታራቂነት ሚና…” ቦሰና ትፈላሰፋለች። ይቅርታ ከፖለቲካው ሰፈር መሰማቱ ልቧን እንደነካው ግን አትደብቅም። ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል። ይቅርታ ካልሆነ የኢትዮጵያን የክፋት ቂጢኝ የሚነቅል መድሃኒት የለም። ያበደው ከቦሰና ጋር ይስማማል። ቂም ያፈረሳል። ቂም ቋጥረው የተነሱ አልጠቀሙንም። በጊዜ መሰናበታቸው አንዳንዴም ለበጎ እንዳይሆነ… ለመታረቅና ሰላም ለማውረድ ወንጌልን መሸምደድ፣ ኦሪት ላይ መላከክ አያስፈልግም። ሰው መሆን ብቻ ይበቃል። ያበደው ” ሰው” ሲል ሁሌም ደጎል እንዳይሰማ በመጠንቀቅ ነው። ደጎል ውሻው!!

የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልቅ ” የኢህአዲግ ዋንጫ” ቀድሞ ቢጀመርም አልተጠናቀቀም። አሁን በሚወጡ መረጃዎች አራት ምድቦች ይፋ ሆነዋል። አየለ ጫሚሶ ተነጥቆ የተሰጣታቸው/ የቅንጅት/ ቡድን በስሩ ያካተታቸውን 11 ተጠባባቂ ቅጥቅጥ ክለቦችን በረዳትነት ይመራሉ። ኢዴፓ የቡድን አባት የሆነበት ሌላው ምድብ እነ ሰማያዊን፣ መኢአድን አካቷል። ህብረት አሰላለፉን ሚስጢር አድርጎ እየተጠበቀ ነው። ኢህአዲግ አሰላለፉን እንደ ተጋጣሚዎች የመቀያየር ልዩ መብት ስላለው አስቀድሞ የሚታወቅ አቋም የለውም። ኢህአዴግ ይቅርታ ህወሃት ግን በምርጫ ቦርድና በአንቀጽ 39 ቀልድ አያውቅም።
የውድድሩ አዘጋጆች ለያበደው በላኩት መረጃ አቶ ልደቱ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እንደሚሆኑ ከወዲሁ አስታውቀዋል። በመረጃው ላይ የውድድሩ የጊዜ ሰሌዳ አልተገለጸም። አቶ አየለ ጫሚሶ ለሞራል ማስጠበቂያ 11 ቀጥቅጥ ክለቦቻቸውን አሰባስበው የገመድ ጉተታ ውድድር እንደሚያደርጉ የጠቆመው መረጃው የዚህን ዋንጫ አየለ ጫሚሶ ከቀዳማይ እመቤት እጅ እንዲወስዱ ይደረጋል። ከዚህ ውድድር በሁዋላ አሸናፊዎች ” በታዛቢዎች ፊት በድምጽ ይለያሉ።
ጊዜው ባይገለጽም የመዝናኛ ትዕይንት የሚያሳዩ ተወዳዳሪዎች አሉ። ያበደው ፈገግ ብሎ ያነበበው መረጃ በዚህ የመዝናኛ ትርኢት ላይ የሚቀርቡ ዝግጅቶችን ነው። አስመስሎ መሳቅ፣ ፊትን በተለያዩ ቀለማት በመቀያየር በሥሥ ልብሶች ሰርከስ ማሳየት ፣ ሌላ ሰው ወይም አውሬ መስሎ መታየት፣ ጅብ መምስል፣ ተኩላ መምሰል፣ አሳማ መምሰል፣ ተዘጋጅተው የቀረቡ ጭምብሎችን በመልበስ የተጠኑ መነባንቦችን ማቅረብ፣ የምግብ ማግበስበስ ውድድር፣  የብሄር ብሄረሰቦችን ጭፈራ ማሳየት…. ” እስከመገንጠል ” የሚለውን አንቀጽ ሆን ብሎ መቃወም…
አዎ!! እንዲህ እያሉ ለድርድር ቀንድና ጭራ የሚቀጥሉ አሉ። እንዚህ “ጸረ ልማታዊ አስተሳሰብ” ያላቸውን አታዳምጡ። ሃሃሃሃሃሃ……አሁን ያበደው ነቃ። ድርድር ግድ ነው። አሁን ጊዜው የአሽሙር አይደለም። አገራችንን እናስብ። ችግሯና ጠላቶቿ ብዙ ኢትዮጵያ!! ያበደው አምላክን ዘወትር ለኢትዮጵያ ብቻ የሚያስብ አድርገው የሚመለከቱትን ይታዘባል። አምላክ ዩጋንዳን፣ ኬናያን፣ አሜሪካን፣ እንግሊዝን፣ ናይጀሪያን፣ ብራዚልን… ሁሉን ረስቶ ኢትዮጵያን ብቻ ሲጠብቅ ውሎ፣ ሲጠብቅ የሚያድር የሚመስላቸው…. አሁን ጊዜ የማሰቢያ ነው። ያበደው ድምጹን ከፍ አድርጎ መጮህ ቃጣው!!
ተደራዳሪዎች ዋስትና ይፈልጋሉ። እንደራደር ያሉ ደግሞ ይበልጥ ዋስትና ይሻሉ። በቂምና በጥላቻ የሚሆን ነገር የለም። መጪውን ትውልድ ማሰብ፣ አገርን ማስቀደም ግድ ነው። ተከባብሮ ወደ ሚጠቀመው መንገድ ማምራት የወቅቱ ጥያቄ ነው። ደጎል ምክር አለው። ማስጠንቀቂያም!!
ደጎል ” እኛ ውሾች ብዙ ዘር አለን። እባቶቻችንን እንኳን ጠንቀቀን ባለማወቃችን ጥርጣሬ ጤና አይነሳንም።  ዘረኞች አይደለንም። ከየትኛውም ዓለም ስንገናኝ ስለ ዘር አናወራም። ጠረናችንን እንቀያየራለን። ሰዎች ይህን ስናደርግ ሰላምታ እንደምንቀያየርና ግንኙነት እንደምናደርግ አይገባቸውም። በርግጥ አንዳንድ ተናካሽ ውሾች አሉ። መናከስ ተፈጥሯችን አይደለም። አሳዳጊ የሚያስተምረን ችግር ነው። አሳዳጊዎች መርዝ እየጋቱ እናንተን እንደሚያባሉዋችሁ ሁሉ ተናካሽ እንድንሆን ጉድጓድ ቆፍረው ጉድጓድ ውስጥ የሚያሳድጉን አሉ።…. መታመን ልዩ ባህሪያችን ነው። ኮተት የለንም። ለሆዳችን ብለን ወዳጃችንን አሳልፈን አንሰጥም። ፍቅር መቀበልና መስጠት እናውቃለን። በቤታችን ቀልድ አናውቅም…” ደጎል አይጨርስም። ደጎል ማብራሪያው ብዙ ነው። ” ግን ሰው ለምን ውሻን ስድብ አድርጎ ቃሉን ይጠቀምበታል” ይላል። አዎ!! አለአግባብ መለጠፍ እንወዳለን። መልካም የኢህአዴግ ዋንጫ ውድድር። ይቅርታ ድርድር !! እርቅ!! አንዱ አምላክ ስለ መጪው ትውልድ ሲል እርቅ እንዲመጣ ይርዳን!! ሌላው መንገድ ….. ተግባብተናል… ሰላም ሰለም… አሁን ወደ ቦሰና!! ቸር ያሰማን!!

ቅድሚያ አሜሪካ- ቅድሚያ ” ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራዋይ፣ሲዳማ…” አይ እኛና ኢትዮጵያ

ጫ”ካሁን በሁዋላ አትረሱም፣ አንድ ልብ፣ አንድ መንፈስ፣ አንድ ቤት..”ቃላቶቹ፣ ቃላቶቹ የሚወጡበት ስሜት፣ አገላለጹ፣ አወራረዱ፣ የቃላቶቹና የሃረጎቹ ሃይልልዩነታችን!! “አሜሪካን ዳግም ሃያል፣ ታላቅ፣ ታዋቂ፣ ገናና እናደርጋታለን”ጩኽት!! መጀነን!! መቼ? እስከዛሬስ? “ እንደገና ሃያልነት” ስሙልኝ ወገኖቼ እኒህ ሰዎች አሁንም ገናናነት ያንሳቸዋል። ይርባቸዋል። ይጠማቸዋል። አሜሪካኖች!! ” ካሁን በሁዋላ ቅድሚያ ለአሜሪካይሉናል። እንዴት ነበር እስከዛሬ የኖሩት? ለሌሎች ኖረው ያውቃሉ እንዴ? ትራምፕ ኢራቅ ገብታችሁ ዘይት ሳትዝቁ .. ገና ይቆጫቸዋል

እኛ ገናናነታችን ውርደት ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን እየኖርን ገና ስለ ባንዲራ አልተግባባንም። መሪዎቻችን የሚመርጡልን ቃላት ራሱ ያረጀ ነው። ነፍጠኛ፣ ጠባብ፣ መታደስ፣ ጸረህዝብ፣ ጸረ ልማት፣ጥገኛ፣ ጎጥ፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ መንደር፣ ቀበሌ፣ጌቶቻችን የዓለም ማማ ላይ ሆነው “ አንድ ከሆን የሚያቆመን የለም” ሲሉ፣ እኛ የወረዳ የማንነት ጥያቄ ውስት ተወሽቀን እናነባለን። ሰው የፈለገውን መሆን ተከለክሎ ይታጨዳል፤ በቀላሉ የሚመለስ ጉዳይ አገር ደም እንዲያቃባ ይደረጋል፤ የመገንጠል ጥያቄ፣ የመለያየት ጥያቄ፣…. እነሱ “ ቅድሚያ አሜሪካሲሉ፤ እኛ ቅድሚያ ኦሮሚያ”… “ ቅድሚያ ጎንደሬ፣ አማራ፣ ትግራዋይ…” እነሱ አሁን ካሉበት በላይ በታላቅነትለመስከር ሲማማሉ፤ እኛ ስለመጠፋፋት፣ እርስ በእርስ ስለመባላት፣ አንዱ ወገን ስለማባረር፣ ስለ ትምክህትያበደው አጥወለወለው!!

እንዴት ከረማችሁ? ሰሞኑንን ጉድ ነው የሚሰማው። መቼም ጉድ አያልቅም። ጉድ ቢያልቅ ኖሮ ራሳቸን ጉድ እንሆን ነበር። ጉድን ምስጋና ይግባውና ይኸው ከቀን ወደ ቀን፣ ከሳምንት ወደ ሳምንት፣ ከወር ወር፣ ከዓመት ወደ አመት ያንጓልለናል። ጉድ!! ቦሰና ትራምፕን “ ውርዝልያ” ነው የምትለው። ውርዝልያ በወሲብ ውስጥ ያለው አጋንንት ነው። ወይም ጅኒ ነው። ወይም ሼጣን ነው። ወይም ወሲብ ውስጥ የተቀረቀረ መንፈስ ሙሉበት።

ትራምፕ የተመቻቸውም ያልተመቻቸውም ብዙ ናቸው። በነገሱ ማግስት የተቃውሞ ሱናሚ ተነስቶባቸዋል። ከንግሳቸው ቀን በላይ በወግዘታቸው ላይ ህዝብ ፈሷል። የልባቸውን ባናውቅም “ ምርጫው ላይ የት ነበሩ?” ሲሉ ተዛብተዋል። የዚህ ሁሉ ሱናሚ የሳቸው ውጤት እንደሆነም ተናገረዋል። እሳቸው ገና ሙቀት ላይ ናቸው። ሲያልቅ አምሮላቸዋል። በ70 ዓመታቸው ነግሰዋል። ያበደው መቶ አለቃ ግርማ ታወሱት። እንደ አቂሚቲ፣ ስልጣኑ ጫፍና ታች ቢሆንም!!

አቶ መለስ በስተርጅና ሲሞሽሯቸው በደስታ መቆም አቅቷቸው ነበር። በደስታ ርደው ነበር። ሲያልቅ አምሮላቸው ደስታ ዳዴ አስብሏቸዋል። የደስታው ብዝት ምን እንዳረጋቸው ያበደው መረጃ ባይኖረውም ሳኡዲ አረቢያ ለጥገና መመላለሳቸውን ሰምቷል። ሳኡዲ አረቢያ ሆስፒታል ተጨማሪ ጊዜ ጠይቀው አሁን ድረስ አሉ። ትራምፕም አብደው ነበር። ደስታቸው ፊታቸው ላይ ሲንተከተክ ሊደብቅ አይችልም ነበር። አንዳንዴም ይንጣቸው ነበር። ቢሊየነሩ ሰው የምስራቅ አውሮጳ ሚሽታቸውን ከንፈር በይምክንያቱ እየለመጠጡ ፎከሩዓለምን ጨበጡ። ኦባማን ከሚቼል ጋር ሸኙ። ነጩን “ቤተ መቅደስ” ወረሱ። ኦባማ ተራ የቀበሌ ነዋሪ ሆኑ። ለውጥ፣ልህግ መኖር፣ የሰለጠነ ህዝብ። እኛ ገና ዴሞክራሲን ተማሩእንባላለን። መማር እንዴት ነው? ህዝብ ድምጽ ሲነሳ በግድ ስልጣን ላይ በቀመጥ? 25 ዓመት … ከሞኖፖሊ ትውልድ ምን ይማር?

ያበደው ሳቀ። አዎ የምንማረው እስር ቤት ወደ ማሰለጠኛ መቀየሩን፣ ታስረው ተፈቱ መባል ቀርቶ “ ሰልጥነው ወጡ” ማለትን፣ ድረብ አሃዝ እድገት፣ ዜናን ገልብጦ መረዳትን፣ ጥልቅ ተሃድሶን፣ ቁርጠኛነት፣ ህዝባዊ አገለጋይነትንበነገራችን ላይ ቦሰና “ በጥልቅ ለመታደስ ወስናለች” ላባጆ ገብታ ዘይት ማስቀየር አስባለች። አላስተኛ ያላትን የወግብ ወለምታ ላንዴና ለመጨረጫ ጊዜ ለማስወግድ ምላለች። ከታደሰች በሁዋላ ንግግሯ እንደሚቀየር ዝታለች። ተረትና እምነትን ትለያለች። ድንቁርና ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ስለደረሰችበት ከደንቆሮዎች ጋር ህብረት ታቆማለች። ከተግባር ይለቅ የሽንገላ ፍቅር ለሚመኙ መንገዱን ጨርቅ ያድርገላችሁ የምትል ትሆናለች። ከማይገባቸው ደረቅ አሶች ጋር ጊዜ አታባክንም። እንዲህ አይነት ጓደኞቿን ወዶ ለሚያገባ አጥብቃ ትጸልያለች። አለያም ተመሳሳይ ጭንቅላት እንዲኖራቸው ለፈጣሪዋ ታሳስባለች። አንጎል አይቀየረም እንጂ አንጎል ሊቀየርላቸው የሚገቡ አሉ ባይ ናት። መታደስ ውስጥ አንጎል የመቀየር ፓኬጅ እንዲካተት …

ይሄ ገንገበት የጋምቢያ መሪ “ ተሸነፌያለሁ” አለና ወዲያው ሃሳቡን ቀየረ። አናፍጠው እንደሚያወረዱት ሲያውቅ ዘርፎ ጠፋ። ጋምቢያን ሚሊዮን ዓመት ለመምራት አምላክ ሹክ ብሎኛል.. ያለ እለት ቡቱቶ አመለካከት እንዳለው ግልጽ ቢሆንም፣ በሰላም እንደሚወርድ ካረጋገጠ በሁዋል ለምን ሃሳቡን ቀየረ? ነብስ ይማርና አቶ በድሩ አደም በ1997 የቅንጅት ሰልፍ…. አቤት ሰልፍ፣ አቤት የሰው ጎርፍ፣ አቤት አቤትእንዲህ ይባል ነበር “ የበግ ቆዳ ያለው፣ የንብ ቆዳ ያለው፣ የንብ ዱንግላ…” ያ የህዝብ ሱናሚ ከዛ ሁሉ ምንም ሳያተርፍ በዜሮ ከጨዋጣው ወጣ። ሞተ!! መሪዎቹ አሁን ድረስ ከዛ የነተበ ክስረታቸው ሳይማሩ አሉ። እገሌ ከእገሌ ሳይባሉ ሁሉም!!

አቶ በድሩ ሲያስፎክሩ ወደ መጡበት እንመልሳቸዋለንአሉ። መለስ ይህንን ፉከራ ተጠቀሙበት። ከጎናቸው ስልጣን እናካፍል የሚሉትን ረቱበት። የሚወክላቸውን ህዝብ “ ራስህን ጠብቅ” ብለው አነሳሱበት። እናም ያጋምቢያው የቀድሞ መሪ ገና መሸነፋቸው እውን ሲሆን “ ለፍርድ ይቀርባል፣ ይታሰራል፣ በገደላቸው ሰዎች ይጠየቃል…” እያሉ ሲዝቱባቸው በረገጉ። አልውርድምአሉ። አስቸኳይ ጊዜ አወጁ። ተንፈራገጡ፤ አልሆን አለና እንደበረገጉ ሳየትኙ ከርመው ኮበለሉ።

ገና አዲስ ናቸው ጊዜ ያስፈልጋቸዋለ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ በተለይ ትራምፕን ሴቶች አብዝተው ይጠሉዋቸዋል። አብዝተው ይቃወሙዋቸዋል። በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ይፋ የሆነባቸው መረጃ ስድ እንደሆኑና ለሴቶች ያላቸውን ክብር በማጋለጡ… ” ሴት ከወደድኩ ዘልዬ … እጨብጠዋለሁአሜሪካ ወግ ደረሳት፤ የሚመጥናትን ሰው አገኘች። በትክክል ተሰፈረች። በብሩ ሲሞላቀቅ የኖረይመራታል። አሜሪካን ትራምፕ “ ይበልጥ ገናና፣ ሃያል፣ አንደኛ፣ ይበልጥ አንደኛከሁሉም በላይ አንደኛ ሊያደርጉጉድ ያሰማን። እኛ መቼም እንኳን ዓለምን ራሳቸንንም ማስገረም ተስኖናል። አንድ ያድርገን። አሁን የደጎል ሰዓት ነው። ቦሰናም በተሃድሶ ሱባኤ ላይ ነች። በር ዘገታ መጸለይ አብዝታለች። ያበደው ጣልቃ አይገባም። ደጎል ጋር መጫወት ደስታ አለው። ትራምፕን በቴሌቪዥን ሲያይ ይጮሃል። በጸጉራቸው ሰለሚቀና ነው መሰል ቲቪው ላይ መሽናት ሁሉ ይፈለጋል!!  ደህና ሁኑ ሰላም!! ከህብረት ይልቅ ህንፍሽፍሽነት ለሚበልጥባችሁም ሰላም!!

አዲስ አበባ አታብድም፤ ግን ምላጭ ውጣለች

…ያበደው ” እመኑኝ” ይላል። አዲስ አበባን የሚመቻት በልኳ የሚሰፋ ፖለቲካና ፍልስፍና ከልተበጀ  አትነቃነቅም። ሁሉን ስላቀፈች ለሁሉም ቤት እንዳትሆን ለሚጎትቷት መልስ የላትም። የሁሉ እናት ሆና በረከቱን ስላየች ጎንደሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ኦጋዴን፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግሬ… በሚሉ ሃይሎች ለመበለት አትፈቅድም። ግን ለውጥ ትፈልጋለች። መለወጥ ያምራታል። ሁሉንም ታውቃለች። አትሸወድም። ንቃቷ ከሁሉም በላይ ነው። ችግር ቢያንተከትካትም ” ብልኬ” ባይ ነች። ልኳ የሁሉም ቤት ሆኖ የመኖር እምነቷ ነው። እምነት !! በቦስና ቋንቋ  ማተቧ አብሮነት ነው!!…

አዲስ አበባን ጅል የሚያደርጉ አሉ። ግን አዲስ አበባ አዋቂ ነች። የነቃች ነች። ዝም ብላ አታብድም። የማያዋጣት ጨዋታ ውስጥ አትገባም። በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ሳትንቦጫረቅ ሩብ ምዕት ኖራለች። ያም ሆኖ ህመም ቢኖርባትም ዋስትና ትፈልጋለች። ለውጥ ፈላጊ ብትሆንም እሷን የማያካትት ከሆነ ይደብራታል። “በራ” ማለትን ትወዳለች። ግን ሁሉም ሆኖ የኑሮ ምላጭ ውጣ እየሸረካከታት ነው። አይ አዲስ አበቤ!! አይ አዲስ አበባ!! ስምሽ ደግ አዳርና ውሎሽ ቀለሙ የማይታወቅ….. አዱ ገነት ዥጉርጉር!!

እንደምን ከረማችሁ? ገና ነበር። በገና እሱ ተወለደ። ቦታ ጠፍቶ በረት ውስጥ ተገኘ። አዋቂዎች፣ አጥባቂዎች፣ መምሮች፣ ባለጠጎች፣ አገልጋዮች፣ የተከበሩ… እያሉ ለእረኞች ተከሰተ። ንጉሱን እረኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ሰገዱለት። ለተከበሩት ለነዛ ምናምንቴዎች ንጉሱን አበሰሩ።ከሁሉም መርጦ ለነሱ ተገለጠ!! ብስራቱን በእረኞች በኩል አደረገው… ይገርማል። ደቀ መዝሙሮችን ልኮ ያቺን፣ ያቺን የተገፋች፣ ” የመንጻት ህግ” የሰለጠነባት ሳምራዊ አገኘ። አናገራት። ጠየቃት። በመጠየቅ አዳናት / ነፍሷን!! አይሁድ ከሳምራዊ ወሃ ለመነ። “እኔ ነኝ” አላት። ስለ እራሱ መናገር ባይወድም ለእርሷ እሱነቱን ገለጠላት። ከዛም ሰበከችው። የተናቀችው አዳኙን አወጀች… መታደል!!  ገና- ሽብሸባ፣ ድግስ፣ ጋጋታ፣ እስክስታ፣ ቀረርቶ… አይደለም። ጥሞና ነው።  እሱ በቤታችሁ፣ በልባችሁ፣ በህሊናችሁ የተወለደ ታድላችኋል። በልታችሁ ያገሳችሁ ተሸውዳቹሃል። ደስታው ደግ ቢሆንም ያን ዘመን ለሚያስቡ ገና መወለጃ ቦታ የሚፈልግና፣ እንዲወለድ ለሚፈልገው ቦታ በሚፈቅዱ መካከል የሚደረግ ቃል ኪዳን ነው!! በቃ!!

ያበደው ቀና። እረኛ ወይም ሳምራዊቷን መሆን ተመኘ። አይሁድ በመጠየቀ ይፈውሳል። በመጠየቅ ውስጥ ፈውስ አለ።  እሱ ሲጠይቅ የማንሰማ “ቴሌዎች” በዛንና ህይወት የሌለው ድግስ አድማቂ ሆን… ያበደው የተነሳበትን ረሳው። አዲስ አበባ ” ተኝታለች” ይላሉ። አዲስ አበባ በማንኮራፋት ሳይሆን በኩርፊያ ውስጥ እንዳለች ግን ሳታሳብቅ አላረፈችም። ኑሮ ልጆቿን እየለበለበባት ነው። ቦሰና እያለቀሰች የሰማችውን ተረከች። ” መማር ከንቱ” ስትል መሬት ጫረች። አዲስ አበባ የአንዱን ልጇን የኑሮ መልክ አሳየቻትና “አዬ” ስትል አንጋጠጠች። “የገናው ንጉስ አንተ መላ ፈልግ እንጂ” ስትል በየዋህነት የእናቶቻችን ልቡና ማመልከቻዋን ወደ አርያም ላከች።

ለጁ ተመራቂ ነው። ዘመዷ!! ባለ ዲግሪ ነው። አሁንም ጡረተኛ ነው። እየሰራ የሚጦር!! አዲስ አበባ የሰራተኛና የስራ አልባ ጡረተኞች፣ የእድሜ ጡረተኞች፣ የተፈጥሮ ጡረተኞች…. ብዙ አይነት ጡረተኞች ተሸክማለች። ቦሰና የተፈጥሮ ጡረተኞች የምትላቸው በጸሎት በልተው፣ በጸሎት የበሉትን ከፍለው፣ በጸሎት ማረፊያ ፈልገው፣ በጸሎት ላረፉበት ከፍለው፣ ሲነጋም ሲመሽም ሁሌም አዲስ ነገር የማያዩ… እንዲሁ ኖረው፣ ኖረው እድር በሳጥን አድርጎ በደማቅ ስነስርዓት የሚሸኛቸውን ነው። ከቁም ኑሯቸው ሞታቸው የሚስብ!! አይ እኛ… ከኗሪ ለሟች የምናነባ፣ የምናዝን፣ የምንነፈርቅ፣ ደረት የምንደቃ፣ በቃ ከቆመው፣ ከሚወለደው፣ መኗሪው ይልቅ ለአስከሬን የምንዘምር፣ የምንገበር፣ ኢንቨስት የምናደርግ ጉዶች!! ግን ሁላችንም አይደለንም!!

ቦሰናን አሁን አንጀቷን የበሏትና ያሳሰባት “እየሰሩ የሚጦሩት” ናቸው። ይህ ዘመዷ 2000 ብር ያገኛል። 2000 የተመራቂዎች የመነሻ ደሞዝ ነው። ደሞዙ የተተመነው ኑሮውን አጉኖ እላይ የሰቀለው የሃይለማርያም፣ ይቅርታ የእነ መለስ፣ አሁንም ይቅርታ የእነ… አስተዳደር ነው። የአገራችን ኢኮኖሚ በድርብ አሃዝ አደገ ሲባል ” ሌሊት ሌሊት ህዝብ ሲተኛ ነው?” ብሎ መጠየቁን ቦሰና አትረሳም። አንዳንዴ ሲነሽጣት ” ይሄ እድገት አይታይም” ትላለች። ኪስ ውስጥ ካልገባ “ምን ዋጋ አለው?” ለማለት ነው። እናም ይህ ዘመዷ 2000 ይጣልለታል። ትራንስፖርት ችሎ ፣ በልቶ፣ ጠጥቶ፣ ለብሶና ተጫምቶ አይበቃውም። መዝናናት አይታሰብም። ፍቅረኛውን በሻይ ሲቀቀላት ጥላው ሄዳለች።

ለካ ክህደቱ፣ ማምታታቱ፣ ስርቆቱ፣ የቀደመው ፈሪሃ እግዜሩ የከሰሙት በዚሁ የተነሳ ነው። አዎ አዲስ አበባ ኑሮ ባደመባቸው ስለተሞላች እምነትና መተማመን ሸሽቷታል። ምን ይደረግ ጠኔ አደገኛ ነው። እያዩ መሞት የለ፤ መመነተፍ ነው። “አዲስ አበባ የሁሉም ነች” ሲባል እንዚህንም ያካትታል። የፍቅር መሰረቱ ሆድ ሆኗል። የትዳር መሰረቱ ገቢ ሆኗል። የሌለውን ማን ይፈልገዋል። ምኞት ለያውም የተፈጥሮ ደግሞ አባይ/ አቅል የለውም። ራስን ያስረሳል። እናም ….. ግን አዲስ አበባ መቼ ነው የትራንስፖርት ወረፋ የሚቀረው? ያበደው ጠየቀ? ለነገሩ የሁሉም ጥያቄ ነው።

ነገርን ነገር ያነሳዋልና ፣  ባቡር ተዘረጋ ፣ አውቶቡስ ተጨመረ፣ የከተማ ውጪ ሚኒ ባሶች በተደራቢነት ተመደቡ፣ ችግሩና ስልፉም የዛኑ ያክል ያድጋል። ለምን? አሃ ኑሮ አድጎ በመኪና የሚሄዱ በዙ። በግር መሄድ ቀረ። ስኳር ሲጠፋ “ገበሬው ሁሉ ስኳር መብላት ጀመረ” እንደተባለው። ጤፍ ሲወደድ ” ገበሬው ጤፍ መብላት ስለጀመረ” እንደተባለው… ሚኒ ባስ ቢባል አሁን ያሉት ሚኒባሶች እንዴት ነው ምርመራ የሚያልፉት? ከርክሰዋል። መብራት እንኳን በወጉ የሌላቸው አሉ። መቀመጫቸው በጊዜ ብዛት ራሱን ወደ ታጣፊነትና ቆርቋሪነት የቀየረ፣  እንዲህም ሆኖ የትራንስፖርት ችግር የሚቀረፈ አልሆነም። ሳናድግም፣ አሁን ” አድገንም” ችግሩ ሲሰፋ እንጂ ሲጠብ አይታይም። … ያበደው ሃሳብ በዝቶበት አንዱን እያነሳ ሌላውን  ጣለ። ቤት ተከራይቶ የሚኖር የ2000 ሺህ ብር ጡረተኛ ይቅርታ ደሞዝተኛ እንዴት ይኖራል? አባት ልጆቹን እንዴት እንዳሳደገ ሲጠየቅ ” በታምራት” እንዳለው ካልሆነ በቀር።

አንድ ተራ ሽሮ 30 ብር  ነው። 2000 የሚያገኝ ሰው ቤት ተከራይቶ 30 ብር ከፍሎ ሽሮ የመብላት ድፍረት የለውም። ዲግሪ ይዞ ሽሮ ለመበላት የሚሸማቀቅ ሰራተኛ፤ ከበላም የግድ ” ኪራይ ስብሳቢ” ሆኗል ማለት ነው።  እና አሁን አሁን “ስራ አለኝ” ማለት ደባሪ … በወሩ መጨረሻ ስንት ስንት ይጨመር የሆን? የደሞዝ ጭማሪ በወሩ መጨረጫ እንደ ጸበል እንደሚረጭ ተነግሯል። ያበደው አንድ መልዕክት አለው። ደሞዝ ሲጨመር የሽሮውን ዋጋ ፍሬን ግጥም አደርገው እንዲይዙት!! እንደው የሰራተኞቹ ጉዳይ ተነሳ እንጂ አዲስ አበባ በየስርቻው ያቀፈቻቸው የተማሩ ስራ ፈቶች እንዴት ይኖሩ ይሆን? አሳሳቢ…

ቦሰና ዘመዷ ጠዋት ተጣጥቦ፣ በቆሮቆንዳ የታጠበ ሸራ መስሎ ወደ ሰራ ሲሄድ የሚሰማውን ነግሯት ውስጧ አዝኗል። እሱ ብቻ አይደለም ሰሞኑንን አደገኛ ወሬ ለቃሚ ሆናለች። ቀረጥና ታክስ አደገኛ ጉዳይ መሆኑንን ሰማታለች። የሂሳብ ሰራተኛ ሲሳሳት ባለቤት ወደ እስር ቤት ይቅርታ ” ወደ መመረቂያ” ቤት ይላካል። ማስተማር የለም። ” ተሳስቷልና አስተካክለህ አምጣ” አይባልም። አንዳንዶች በመቶ ሺህ የሚቆጠር በጀት እያላቸው በሚሊዮን ታክስ ይጣልባቸዋል። እንዲህ አይነት ስህተት የሚሰሩ ምንም አይባሉም። አምስት መቶን አንድ ዜሮ ጨምሮ ያሳሳተ አለቀለት!! ይህም የመልካም አስተዳደር ሳይሆን የመልካም አስተሳሰብ ችግር ነው።

አዲስ አበባ አሁን አንዳንዶቹን አራዳ እያደረግች ነው። ንቃቷን እያካፈለቻቸው ነው። ቤት ለጋራ መከራየት ተጀምሯል። ጠበሳ ሲኖር በስምምነትና ” በመፈቃቀር ላይ በተመሰረተ” ይከናወናል። እቅድ ይወጣል። …. በተጻራሪው 2000 እየወሰዱ የሚሊዮን ኑሮ የሚኖሩ አሉ። የቶጀሩ አሉ። ኑሮን ሌሎችን ሲያንጠባጥባቸው ኑሮን የሚያንቀረቅቡ አሉ። የጥልቁ ተሃድሶ ዘመቻና የአዲስ አበባ መዥጎርጎር በቀለም የሚገለጸው አይደለም። አዱ ገነት የገንዳ፣ የገዳም፣ የጎዳና፣ የቱቦ ውስጥ፣ የህንጻ ላይ… ሁሉም አይነት ህይወት ይፈስባታል። አዲስ አበባ ብትነፍርም አላመጸችም። የአመጹ አይነት የተስማማት አትመስልም። ጎሳና ጎጥ ውስጥ መወሸቅ አትወድም። ንቃቷ ይህን አይቀበልም። ብችግር የምትነፈረው አንሷት በጎሳና በቀበሌ አሳብ መናጥ አልመረጠችም። በሄርና ጎት ውስጥ መቀርቀር አልፈለገችም።

ያበደው ” እመኑኝ” ይላል። አዲስ አበባን የሚመቻት በልኳ የሚሰፋ ፖለቲካና ፍልስፍና ከልተበጀ  አትነቃነቅም። ሁሉን ስላቀፈች ለሁሉም ቤት እንዳትሆን ለሚጎትቷት መልስ የላትም። የሁሉ እናት ሆና በረከቱን ስላየች ጎንደሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ኦጋዴን፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግሬ… በሚሉ ሃይሎች ለመበለት አትፈቅድም። ግን ለውጥ ትፈልጋለች። መለወጥ ያምራታል። ሁሉንም ታውቃለች። አትሸወድም። ንቃቷ ከሁሉም በላይ ነው። ችግር ቢያንተከትካትም ” ብልኬ” ባይ ነች። ልኳ የሁሉም ቤት ሆኖ የመኖር እምነቷ ነው። እምነት !! በቦስና ቋንቋ  ማተቧ አብሮነት ነው!! ቸር እንሰንበት!! ገና የገባችሁ ተባረኩ። ያልገባቹህ ድፎ ጋግሩ፣ ድግስ አድምቁ፣ ንጉሱ ከመወለጃ ስፍራ እንጂ ከግር ግር ጋር ጉዳይ የለውም!! አሜን!!አሜን ጌታ ቦታ ላዘጋጁለት ተወልዷል። ለሚወዱት ሁሉም ቀን ልደቱ ነው። አሜን ሁሌም !!

2017ም ለእርስ በርስ ፍልሚያ ወደፊት!!

አዋጁ አንዲህ ነበር ፤ የኢትዮጵያ ዘመን ያሳስባል። አሁን ጊዜው ራስንና ህሊናን የመግዛት ነው። የመነጋገር ነው። የመደማመጥ ነው። የመስማማት ነው። ያልሆነላችሁ አቁሙ። ቢቻላችሁ ” አልሆነልኝም” በሉና ንስሃ ግቡ። ለማትችለቡበት የምትዘባርቁ ” እኔ እየረበሽኩ ነው” በማለት ውጡ፤ በስድብ ፖለቲካ የተለከፋችሁ ተመለሱ፣ “ያለ እኛ አገር አትመራም የምትሉም” አለዝቡ፣ ህዝብን በተስፋ የምትሞሉ ይብቃችሁ፤ ታመነም አልታመነም ታመናል። ይብቃ!! በቃ !! በክብር!!

ዘመን ይሄዳል፣ ዘመን ይተካል። አዲሱ አሮጌ ይሆናል። ሌላ አዲስ ዘመን ይመጣና ያረጅብናል። በአዲስ ዓመት አቅደው የሚከውኑ ጥቂቶች እንዳሉ ሁሉ በየዓመቱ ያቀዱትን በከበርቻቻ አጅበው የሚነጉዱ እቅድ አልባዎች የትየሌሌ ናቸው። ራሱ ማቀድ የሚባለው ጉዳይ ሳይገባቸው እንዲሁ በልማድ የሚኖሩ… ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም ዓይነት ነዋሪዎች አዲስ ዓመትን ተቀብለዋል። 2017!!
ያበደው በውጪ አገር አዲስ ዓመት ለሚያከብሩ እንኳን አደረሰችሁ ይላል። ” እንኳን ደረስን ” የምትሉ ስልጡኖችም ካላችሁ ይሁንላችሁ። እግዚአብሄርን ማወቅና ማምለክ ለተምታታባቸው አዲሱ ዓመት እንዲገልጽላችሁ ያበደው ጸሎቱ ነው። በራስ በጎ ፈቃድ የሚከናወነውን ሁሉ ለፈጣሪ አደራ እየሰጡ በዝግ አእምሮ ለሚኖሩ ያበደው ያዝናል። ስሜትን ሁሉ ” እምነታዊ ጥላ” በመስጠት ፈጣሪ ፊታቸውን አጥቦ፣ ቁርስ ሰርቶ እንዲያጎርሳቸው የሚመኙ ፣የተለየ ባል/ ሚስት ጠፍጥፍፎ እንዲሰራላቸው የሚጓጉ፣ ስርዓት እንጂ እምነት ባጠገባቸው ያልዞረ… ደረቆች!! አዋቂ ነን ባዮች!! የልምድ ባሮች!! ማስተማር ወይም መማር የማይችሉ…ራሳቸውን ችለው የማይቆሙ፣ በልመና ሌላውን መስለው የሚኖሩ፣ ትህትናና “ፍቅር” መለየት የማይችሉ፣… ተንታኝ የሚመስሉ፣ እንደ ከበሮ የሚጮሁ፣…. ያበደው ይህን ሁሉ መታዘቡ ቀፈፈው። የዚህ ዘመን” ነብስ ያለው ሃውልቶች” የሚባሉትን አሰበ። ደንቁረው የሚያደነቁሩ…. እሱ አንዱ ፈጣሪ ፍቅርና ሩህሩህ እንደሆነ ያልገባቸው ደርቅ አሶች… እንዲህ ዓይነቶች ካልገጠሙዋችሁ ከብክነት ድናችኋል!! ያበደው ብዙ የሚረግማቸው አጋጣሚዎች አሉ!!
ቦሰና ስለ እምነት ክርክር አትወድም።” ሁሉም በገባው መጠን” የሚለው አካሄድ ይመቻታል። ንትርክ ደስ የሚላት ፖለቲካ ሲሆን ነው። እምነት ራሱ የፖለቲካ ያህል ቀኝና ግራ እንደሆነ ተመራምራ አልደረሰችበትም። ያበደው … ከሃሳቡ ሲነቃ የ2016 ያለመቻቻልና ያለመደማመጥ ጉዞ ታወሰው። በዳያስፖራ ዓለም ውስጥ ያለው የፖለቲካ አዙሪትና የደመ ነፍስ ጉዞ መቼ እርቃኑንን እንደሚቀር ናፈቀው።
የራስን ሰራ ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ መቧቀስ፤ ከመነጋገር ይልቅ እንደ ጋለሞታ አደባባይ ወጥቶ መዣለጥ፣ ከመመካከር ይለቅ ቦታ እንኳን ሳይመርጡ መታኮስ… ያበደው የስህተቶች ደራሽ ጎርፍ ናላውን ይንደው ጀመር። ምን ያልተበላሸ ነገር አለ? ጠየቀ!! ሰዎች ቁጭ ብለው መነጋገር የማይችሉት ለምንድን ነው? መልስ የሌለው ጥያቄ!! መነጋገር ካልቻሉ ለምን ልዩነታቸውን አክብረው የራሳቸውን ስራ አይሰሩም? ለዚህም መለስ የለም!! ካልሆነ ለምን አይተውትም!! ያበደው ጮኸ….
ላብ አደር- ውዝ አደር፣ እናቸንፋለን – እናሸንፋለን… ምሊኒየም- ሚሌኒየም… በአንድ ቃል ስንት ውዝግብ ነበር። ተሸክሞ የሚኖር ወዝ አደር ተባለ ላብ አደር… ሰዎቸ ከዘይትና ከአሳ የቱ እንደሚመርጡ ድምጽ በሚሰጡበት ዓለም … እኛ ገና በስያሜ እንናረታለን። ያበደው አቅለሸለሸው። በእምነት ደጅ ውዝግብ፣ “እዛኛው ቤት ያለው እየሱስ ይቅርብህ፤ እዚህ አዲስ እየሱስ አለ ና፣ ነይ፣ ኑ..” ምዕመኑን ዥጉርጉር ማድረግ!! “የእነ እገሌ ብሄር ደብር አትሂድ፣ አትሂጂ፣ አትሂዱ…” መላዕክትን በብሔር በልቶ አምነት፤ ፖለቲካው ” እኔን ተከተል፣ አትተንፍስ፣ አትቃውም፣ አትጠይቅ…” የሚል አባዜ የተጠናወተው አመራሮችና ጋሻ ጃግሬዎች የተሰገሰጉበት፤ ለመተቸት የሚሞከሩም ሲገኙ – ዝንጠላ፣ ስድብ፣ አብረው ሲሰሩ የሰሙትን ማዝረክረክ፣ ጥላቻ፣ ክፋት….
አሁን 2016 አለቀ። 2017 ተጀመረ፤ “እስኪ ወደ ልቡናችን እንመለስ” ትላለች ቦሰና። ቦሰና የእምነተዋን ማተብ እያማተበች ” እናቴ አስቢን” አለች። አዎ!! ብንታሰብ ደግ ነበር። ግን ለመታሰብም የሚያደርስ ልቡና ይኖረን ይሆን? ያበደው ጠየቀ!! ምን አልባትም አሁን የደረስንበት ደረጃና አገዛዝ ” የሚገባን ይሆን?” አሰበ። ከተቀመጠበት ተነሳ…. “አዋጅ… አዋጅ…. አዋጅ ” አለና በፍጥነት እየተራመደ ለፈለፈ። አንድ ወዳጁን አገኘ!! እንዲረጋጋ ተንገረውና እያጉረመረመ ዝም አለ። ተፋ!! አረፋ የሚመስል…..
አዋጁ አንዲህ ነበር ፤ የኢትዮጵያ ዘመን ያሳስባል። አሁን ጊዜው ራስንና ህሊናን የመግዛት ነው። የመንጋገር ነው። የመደማመጥ ነው። የመሰማማት ነው። ያልሆነላችሁ አቁሙ። ቢቻላችሁ ” አልሆነልኝም” በሉና ንስሃ ግቡ። ለማትችለቡበት የምትዘባርቁ ” እኔ እየረበሽኩ ነው” በማለት ውጡ፤ ብስድብ ፖለቲካ የተለከፋችሁ ተመለሱ፣ ያለ እኛ አገር አትመራም የምትሉም አለዝቡ፣ ህዝብን በተስፋ የምትሞሉ ይብቃችሁ፤ ታመነም አልታመነም ታመናል። ይብቃ!! በቃ !! በክብር!!
የአገሪቱን ፖለቲካ ወደ እርቅ እንመራለን ለሚሉና ሃሳብ ላላቸው በር ይከፈት፤ የሚበጀው እርስ በርስ መነጋገርና በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፈታት ነው። አሁን የተያዘው የቅርጫ ጉዞ የትም አያደርስም። ተበጣጥሰናል፤ ተበልተናል፤ ተነጣጥለናል፤ ተፈረካክሰናል፤ በተስቦ ውስጥ ነን፤ ተስቦው ማጭድ ሳይጀምር የተዘራውን የቂም ዘር እናጽዳ… ያበደው ጥሪው አንድ ነው… የመንፈስ ልዕልና ይሏል ይህንን መረዳት ነው። ገዢ ተገዢ ሳይባል ሁሉም ልብ ይበል… ታመናል፤ ከታመምን ቆይቷል፤ ሀመሙ የጸና ነው፤ ገጀራም ሊኖርበት ይችላል፤ ኢትዮጵያ ለሁሉም ቤት ትሆን ዘንድ ሃላፊዎቹ ሁሉም ናቸው!! ያበደው እንባው ቀረረ አገር… አገር… እስኪ ልቡና ይስጠን፣ እስኪ የእርስ በርስ ፍልሚያ ይቁም ….  በ2017 ለእርስ በርስ ፍልሚያ ወገባችሁን ያጠበቃችሁ ግፉበት… ለሁሉም  መልካም አዲስ ዓመት!!

እስረኞች ” ተመራቂዎች ” ሆኑ!! ኮማንድ ፖስቱ እድሜው ይራዘም!!

ያበደው ሳቀ። ደስ አለው። አዲስ ነገር ሰማ። እስረኞች አዲስ ስም ወጣላቸው። ” ሰልጣኞች” ተባሉ። ሰልጠና ብቻ አይደለም ምርቃትም ተደርጎላቸዋል። የመረቋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። አቶ መለስ ይህንን ወግ አላገኙም። አስረው ለማሰለጠንና ለማስመረቅ ሳይበቁ እጣ ወጣባቸው። ያበደው አሁን መለስ ላይ ቢፈትል አይፈራም። ራሱ ህወሃት ” አብሎቹን ሰብስቦ ” መለስ እያላችሁ አታላዝኑ” መባሉን ሰምቷል። ይህ እድገት ነው….. “አሻም አሻማ” ትላለች ቦሰና!!
“ በፍፁም፣ አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ ህገ መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚሉ ኮርሶች ወስደዋል አሉ ታሳሪዎቹ፤ ይቅርታ ” ሰለጣኞቹ ተመራቂዎች” ያበደው ሃሳብ አለው። ኮማንድ ፖስቱ እንዲህ ዓይነት ትጋትና የስራ ቅልጥፍና ካለው የኢትዮጵያ ህዝብ በየተራ ስልጠና እስኪጨርስ አስቸኳይ ጌዜ ይራዘም። ኮማንድ ፖስት የማይነቀል የመንግስት ማዕረግ ይሰጠው። በክፉ የሚያነሱት…
ነውጠኞችን አስሮ፣ ገርፎ፣ አድቅቆ፣ አራግፎ፣… እስር ቤት የሚደረገውን ሁሉ አደርጎ… የማስመረቅ ፓኬጅ የሚፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ። ኢህአዴግ በነካ እጁ ሲሪያ ገብቶ ” ያመጹትን ቢያሰለጥንና ቢያስመርቃቸው” ስትል ቦሰና ሃሳብ አቅርባለች። አዋጪ የኢንቨስትመንት መስክ ሊሆን ይችላል። ጋቦን፣ ኮንጎ፣ ሊቢያ፣ ናይጀሪያ… ዳግም ከተሳካ ሶማሌ ይህንን አገልግሎት እንደሚፈለጉት ቦሰና ታይቷታል።
ሰላም ወገኖች። መልካም ዜና አስፈነደቀኝና ሰላምታ ዘነጋሁ። ቦሰና ” አይደገምም” የሚለው ኮርስና ቃለ መሃላ ተመችቷታል። ደጎል ምንም እንኳ ውሻ ቢሆንም ” አይደገምም ” የሚለው ንግግር አልገባውም። ምኑ ነው የማይደገመው? አመጽ፣ ሽብር፣ ተቃውሞ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ መሰብሰብ፣ መደራጀት፣ መታገል፣ ማታገል፣ ማሳመጽ… አቶ ሃይለማርያም ” ህገ መንግስቱ በደምና በአጽም የተጻፈ ነው፤ ዋጋ ተከፍሎበታል” ብለዋል ለካ!!
ያበደው አሁን ጥያቄ አለው። “ህገ መንግስቱን መጣስ አይደገምም” መባል አለበት። ሰዎች የመናገር ተፈጥሯዊ መብታቸው ከተከበረ፣ መምረጥ፣ መመረጥና ሾመው ማውረድ ከቻሉ፣ መሰብሰብ፣ መሰለፍ፣ መቃወም፣ ማውገዝ፣ መደራጀት፣ ማደራጀት… ህገ መንግስቱ ላይ ያለው ሁሉ ከተከበረላቸው ለምን ያምጻሉ? ለምን ንብረት ያወደማሉ?…… ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ሰዎች ድምጻቸውን ሲሰረቁ ቢያምጹ ጥፋተኛው ማን ሊሆን ነው? ያበደው ሰነድ አየ። ወደ ሁዋላ አሰበ። ” ድምጽ ሰርቀን እንጂ ተሸንፈን ነበር” ሲሉ ምስክር የሆኑትን አደመጠ። እናም በሰላማዊ መንገድ መርጠው፣ በህጋዊ ተቋም አማካይነት ሰዎች ድምጻቸው ከተሰረቀ ምን ያድርጉ? ያበደው አሁንም ይጠይቃል፤ ስልጠናው የህገመንግስት ኮርስን ያካተተ ነበር። ታዲያ አሁን ” ሰልጥነው የተመረቁት” እንደ ቀድሞው “ህገ መንግስት ይከበር ቢሉስ?” እንደውም አቶ መለስ ባሉበት ነብስያቸው እንድትፋፋ ” እስከመገንጠል” ድረስ የሚሄዱ ቢነሱስ?… አይደገምም!! ያበደው ደጎልን መሆን ተመኘ።
የኢትዮጵያ ነገር ግራ ያጋባል። ግራ ያልገባችሁ እድለኞች ናችሁ። ያበደው በእናንተ ይቀናል። ሌላም ነገር አለ። አሁን በየቦታው ቃል እየተገባ ነው። በብዛት ቃል ሲገባ ይሰማል። ስራ መስጠት፣ ገንዘብ መስጠት፣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር…. ወዘተ… ይነጋል። ይህ ወጣት ነገ ይጠይቃል። ድሆች ነን። ገና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በቀን አንዴ መብላት ያልቻሉባት ደሃ አገር ይዞ ተስፋ ደግ አይደልም። ከጥልቅ ተሃድሶ የዘለለ መሃላ ሊኖር አይችልም። ከዚህ ሁሉ የፖለቲካውን ሜዳ ሰፋ ማድረጉ፣ አማራጭ አለን ለሚሉ እድል መስጠቱ፣ መመካከሩና ተጋግዞ መስራቱ ይመራጣል ሲል ያበደው ጥሪ ያሰማል።
ግልገል ጊቤ ተመረቀ የሳምንቱ ዜና ነው። ሃሪፍ ዜና ነው። ያበደው ጸሎት አለው። ” ግልገል ጊቤን አንድዬ በተዓምርህ ጠብቀው፣ ዝናብ ይፈልጋልና ሙላው፣ ግን አታጥለቅልቀው፣ ቅድሚያ ለወገኑ ያበራ ዘንድ እርዳው፣ ቅድሚያ ለጎረቤት ብሎ እንዳይሸፍት ልቡና ስጠው… አሜን” መልካም ነገር ሲሰራ ደስ ይላል። የሚከፋችሁ ካላችሁ ታከሙ። ታስራችሁ ” ተመርቃችሁ” ለወጣችሁት ኮንግራ!! እነሱን ተክታችሁ ወደ ” ስልጠና ማዕከል” ለምትጋዙ… ያበደው ከንፈሩን መጠጠ። ብዙ አይነት ብርሃን ታየው። የሚያቃጥል፣ የሚነተከተክ፣ የሚለበለብ… ግን እንስማማ። ዳግም ጀማሪ፣ አፍርሶ አዳሽ፣ አውድሞ ጠጋኝ ከመሆን ይጠብቀን። የሰላም ቀን ያምጣልን፤ አሜን!! ያበደው ተነሳ፣ ደጎል ጭራውን ቆላ፣ ቦሰናም ሸብረክ አለች። “ድንግል ሆይ” ስትል እንደ ልማድዋ አነባች። አገሪቱ ” በሚያነቡ” ጸሎት እንዳለች የታመነ ነው!! በስድስት ኮርስ ፓስተር፣ ነብይ፣ ዲያቆን፣ መምህር… በመሆን ጥበብ የትም አይደረስም። አቋራጭ… ሰላም ሁኑ!! መልካም የጌቶቻችን ገና!! እስኪ እናንተ ልበ ብርሃኖች ጸልዩ ለኢትዮጵያችን !! የዋሃንን ይሰማልና!! በድጋሚ አሜን አልን!! አሜን!!

“ታላቋ ትግራዋይ”

ያበደው እንግድነት በተቀመጠበት ቤት ዙሪያውን ያማትራል። ገና ከመቀመጡ የጥያቄ መዐት አንጎሉን እየበወዘው ነው። ቤቱ የአንድ “ልማታዊ ድሃ” ምሳሌ ነው። በአራቱም መአዘን ግድግዳ ላይ ምስሎች አሉ። መለስ በትልቁ ጉብ ብለዋል። ጣታቸውን ቀስረው የ “ወደፊቷን ኢትዮጵያ” ያመላክታሉ። ሌላም ትልቅ ስዕል አለ። ስዕሉ ካርታ ነው። ካርታው ማብራሪያ አለበት። ከካርታው ላይ ያለው ጽሁፍ “ ታላቋ ትግራዋይ” ይላል። አዎ “ ታላቅ ነበርን ዳግም ታላቅ እንሆናለን” ድንገት “ የተሰውት” የመለስ መፈክር!!

የጥሩ “ልማታዊ ደሃ” ቤት ገና ሲገባ ቤቱን መተናፈሻ የሚያሳጣ ዳንቴል ጣል ጣል ያለበት ሶፋ ይገኛል። ሶፋው በጨርቅ ይሸፈናል። አንዳንዴም የሶፋውን ቀለም ባለቤቶች ይረሱታል። የጅማን ደን ያወደም ቡፌ፣ አልጋና ቁምሳጥን አለ። ቤቱ በሲሚንቶ ሊሾ ይደረግና የላስቲክ ምንጥፍ ይለብሳል። ቦርጫሙ ቴሌቪዥን ቀን ከሆነ ልብስ ለብሶ ይታያል። ስልክ በሳጥን ውስጥ ተከርችሞባት፣ ዳንቴል ይደረበባታል። አዲስ ልሳን፣ ራእይ፣ ዘመን፣ ጽጌሬዳ፣ ሃትሪክጋዜጦች ከሶፋው ስር አይጠፉም። ከሳሎኑ ግርጌ የኤሌክትሪክ ምጣድ አይጠፋም። ቆጣሪው የቤተሰቡ አባል ይመስል አንገቱን አስግጎ ይታያል። ግድግዳው የፎቶ አልበም ነው የሚመስለው። የፊልም አክተሮችም አይታጡም። አንዳንዶቹ ለፋሲካ የሚወጣ የሽንኩርት መፍጫ አላቸው። ፍሪጅም አይታጣም።

ያበደው በካርታውም ሆነ በማብራሪያው አላዘነም። አልተከፋም። እንደውም ፎክር ፎክር አለው። “ ታላቋ ትግራዋይ”!! እትት፣ ዘራፍ፣ ዘራፍ … ቢል ምንኛ ደስ ባለው! ጋባዥ አንድ እናት ናቸው። ልክ እንደ ቦሰና እናት ያው የአበሻ እናት…. የሚበላ ለማቅረብ ጎንበስ ቀና ይላሉ። ሰው በልቶ የሚጠግብ አይመስላቸውም። ተጫዋች፣ ሩህሩህ፣ ተግባቢናቸው። ያበደው በላ ጠጣ። ከዛም ቀስ ብሎ ጨዋታ ጀመረ። ስለ ካርታው ጠየቃቸው።

ከየት አመጡት” ዋይሳቁ። “ ምኑን?” አሉ በፈገግታ ግድግዳቸው ላይ የተገጠገጠውን ስዕል እያዩ። ያበደው ተነሳና አሳያቸው። ወሬ ተጀመረ። ካርታቸው በደምና በአጥንት የተገነባ እንደሆን አብራሩ። “ ትግራዋይ” ታላቅ ሆና ሳያዩ ፈጣሪ እንዳይገላቸው የዘወትር ምኞታቸው እንደሆነ ወደላይ አማተቡና ተናገሩ። ያበደው ፈገግ አለ። ስማቸውን ጠራቸውና “ በቃ ከኢትዮጵያ ልትለዩ? እንደ ኤርትራ ልትገነጠሉ? አክሱም የሚባል ብር ልታሳትሙበቃ ልንለያይ ?”

ምን?” ሲሉ ጠየቁ። አከሉና አጠገባቸው ያለውን ደብር ስም ጠርተው አማተቡ። ቢሞቱ ከአዲስ አበባ ንቅንቅ እንደማይሉ አረጋገጡ። “ ታላቋ ትግራይ ስትመሰረት እኮ አንድ አገር ነው የምትሆኑት፣ ልክ እንደ ኬኒያ፣ ኤርትራ.፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ….” ከት ብለው ሳቁ። ደጋግመው “ አሜሪካ” አሉ። ወደ ቀልባቸው ተመለሱና “ እንደዚሁ እየኖርን ታላቅ መሆን አንችልም?” ሲሉ ጠየቁ። አሁን ያበደው መረር ማድረግ እንዳለበት ገባውና “ የሌሎችን ፈቃድ ማግኘት ግድ ነው” አላቸው።

መፈክር ሳይገባቸው ተሸክመው የሚኖሩ አሉ። ገብቷቸውም እንደ ማተብ አንገታቸው ላይ አድርገው የሚኖሩ አሉ። ያበደው ባየውና በሰማው አላዘነም። ግን ታላቋ ኦሮሚያ፣ ታላቋ አማራ፣ ታላቋ ሶማሊ ክልል፣ አፋር፣ ታላቁ የደቡብ ህዝቦች ሪፐብሊክታላቋ ጋምቤላ፣ ታላቋ ቤኒሻንጉል፣ ታላቋ ኦጋዴን….. ሁሉም ጋር ግን ያልተፈታ እንቆቅለሽ አለ። ያልተመለሰ ጥያቄ አለ። ወደ ጸብ አረንቋ የማምራት ምልክት አለ። አሁን በታሰበው መንገድ የመቀጠሉ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ነው። ኢትዮጵያን የሚያከስመው ጥርጊያ መንገድ በፍጥነት አስፓልት ሆኖ ዘየት እየተረጨበት ይመስላል። ሁሉም “ጠቦ፣ ታላቅ መሆን ” ተመኝቷል። ያበደው ክልሎች ታላቅ ቢሆኑ ጸብ የለውም። ኢትዮጵያን የሚያመነዥግ ታላቅነት ግን አይገባውም።

አሁን ባለው እውነታ “ የታላቅነት” የመጨረሻ ግብ አገር አልባነት ነው። የአርነት ንቅናቄዎች በዝተዋል። ራሱ ገዢው ህወሃትም የሚጠራው “አርነት” ተብሎ ነው። ኢትዮጵያዊነት ላይ አተኩረው የሚሰሩ ልሳናቸው እየተዘጋ ነው። ሰለው ወደ መጥፋት እያመሩ ነው። አማራም “ ራሴን ላድን” ብሎ በጠቅላይ ግዛትና በወንዝ ተደራጀ። ኢትዮጵያ የቀራት ነገር ቢኖር የሚሰራባት ድራማ ሲጠናቀቅ ማየት ነው።

ያበደው እምባው መጣ። አገሩ አሳዘነችው። አዎ ኢትዮጵያ ታማለች። እሳት ላይ ተጥዶ በሚንተከተክ ማሰሮ ተመስላለች። ማሰሮው ውስጥ ያለው ህዝብ ነው። ህዝብ እየነፈረ ነው። ፖለቲከኞች “ታላቅ” እንሆናለን በሚል ህልም ከውስጥም ከውጭም ማገዶ ይጨምራሉ። ማሰሮው ይንተከተካል። ማገዶ የሚቀንስ፣ እሳቱን የሚያጠፋ፣ ክዳኑንን ከፍቶ የሚያስተነፍስ የለም። የታፈነው ማሰሮ አማራጩ መገንፈል ነው። ከገነፈለ ገነፈለ ነው።

እኚህ እናት “ ታላቅነት” በመገንጠል ሳይሆን በአንድነት ውስጥ ነበር የሚመስላቸው። እንደ እሳቸው አስተሳሰብና እምነት ከሆነ “ ታላቅ” መሆን ለሌላውም ኩራት ነው። ሳይረዱ እኚህን እናት የሚጠሉ አሉ። እሳቸውም ሌሎችም ሳይገባቡ ይኖራሉ። አንዱ ሌላው ላይ ሳይገባው ጥርስ ነክሶ ይኖራል። የመለስ ራዕይ እየዋለ ብዙ ያሰማናል። አሁናሁን ህወሃትም ሰለቸው መሰል “ መለስ መለስ እያላችሁ አታላዝኑ” ሲል አሳስቧል። ትክክል ነው። ቢቻል የመለስን ውጥን ሁሉ ብታፈራርሱና “ ዳግም ኢትዮጵያን ታላቅ እናድርግ” በሚል መፈክር ብትነሱ መከላከያ፣ ኮማንድ ፖስትአስቸኳይ አዋጅ…. የሚባል ነገር እንደማይኖር ያበደው ማረጋገጫ የሰጣል!!

ያበደው ቦሰና ያለችው ታወሳው። ቦሰና ለኢትዮጵያ መፈትሄ አላት። በየክልሉ ህዝብ የሚወዳቸው ድርጅቶች አሉ። ህዝብ ለሚወዳቸው ክብር አለው። ለሚወዳቸው ይታዘዛል። ስለዚህ በሚወዳቸው እንዲተዳደር ሊፈቀድለት ይገባል። ምርጫው የራሱ እንጂ የሌሎች መሆን የለበትም። ትላለች። የዚያኔ ያበደው “ ሲያምርሽ ይቅር” ይልና ያሾፍባታል። እሷ ግን የምሯን ነው። ካልሆነ አደጋው ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል። ባለሜንጫዎች አጋጣሚው ይሳካላቸዋል። … “ቦሰና ጆሮ ቢሰማ ዋጋ የለውም” ትላለች። ንጉሱ ምክር ገፉ፣ መንግስቱ ምክር አጣጣሉ፣ አሁንም ምክር የሚሰማ የለም። እስር መፍትሄ አይሆንም። የሚያኮርፉ ወገኖችን ማራባት አይጠቀምም። ቆም ብለን እናስብ። ከጥላቻ እንውጣ!! ሃውዜኖች እየበዙ ነው!!

ፖለቲካ ሸፍጥ ቢሆንም፣አይን ያወጣ የፖለቲካ ሽፋጥ ይቁም!! መንግስት ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ጎራውም ከማምታታት የታቀበ ይሁን። ህዝብ በሚሰማው ተሰላችቷል። በሁሉም ወገኖች ዘንድ መደማመጥ የለም። የመታገል የጥበብ መጀመሪያ መዘላለፍ ሆኗል። ጸያፍ ስድቦችን ያበደው ሰሞኑንን አይቷል። አማራን ነጻ አወጣለሁ የሚለው ሰው “ እናትህ ምናምን ትሁን ብሎ…”

አሁን ያበደው ደክሞታል። ደጎል ይጠብቀዋል። ደጎልን ከማዝናናትና ከእሱ ጋር ከመሆን በላይ ያበደውን የሚያስደስት ነገር የለም። “ ኢትዮጵያን ዳግም ታላቅ እናድርግ” የምትሉ ተባረኩ። ኢህአዴግ እስኪ በዚህ ሃሳብ ሞክር!! ሰላም ሰላም … ቸር እንሰንበት!!

“በጥልቀት…” ወይም ወደጥልቁ!!

ሜንጫ፣ ሜንጫ፣ ሜንጫ፣ ሜንጫ፣ ሜንጫ… ህብረት፣ ህብረት፣ ህብረት፣…. ውህደት፣ ውህደት፣…. መነጣጠል፣ መነጣጠል፣ መነጣጠል…. አመጽ፣ አብዮት፣ የሽምቅ ጦርነት፣ የገሃድ ጦርነት፣ የድረ ገጽ ጦርነት፣ ሃስብን በነጻነት የመግለጽ ማእቀብ… ያበደው ተምታታበት። ውጥረት፣ ግምደላ፣ የሰለለ እውነት፣ የፋፋ ቱፋ፣ ህልም፣ ቅዠት፣ ክዳት፣ክፋት……ጥላቻ፣ መለያየት፣ ከያቅጣጫው ይዘንባል። ህዝብን ያበሰብሳል። የሚያስጠልል የለም። ከውስጥም ከውጭም ያፈሳል፣ ፈሳሹ አሁን አሁን ዶፍ እየሆነ ነው። ሟርት አይደለም። ሟርት ብሎ ነገር የለም። በሁሉም አቅጣጫ ሳስቷል። ሰከን፣ ሰከን፣ ሰከን፣ ሰከን….. ያበደው ዘፈን ባይወድም ዘፈነ!!
ሰላም ለናንተ ይሁን። ለተሰፋዬ ዲንቃ ነብስ ይማር። ቦሰና ለቤትሰቦችዎ መጽናናትን ልካለች። 10 ቢሊዮን ብር ” ባስቸኳይ ለታዘዘላችሁ ስራ ፈጣሪዎች” መልካም እድል። አትፍሩ ሶስት ሶስት ሆናችሁ ተደራጁና ይቅርታ “ተጠርነፉና” ተበደሩ። አምስት ዓመት ረዥም ነው። አምስት ዓመት ብሉ… ካላተረፋችሁም አትጨነቁ… ግን ተበደሩ፣ ሞክሩ፣… ከሚቀጥለው ምርጫ በሁዋላ ደግሞ ሌላ ፓኬጅ ይመጣል። ብድር ስረዛ!! አለያ አመጽ ይቀጥላል። ኢህአዴግም እንደገና ከ”ጥልቅ ተሃደሶ” ወደ ጥልቁ ይገባ ይሆናል። ባይገባም ስሙን ቀይሮ “ልታደስ” ማለቱ አይቀርም። የዛኔ የብደር በጀቱ ይጨምራል። እዳ ስረዛ … ያበደው ፈገግ አለ። መታደስ፣ በጥልቅ መታደስ… ከዚህ ሁሉ ከገቡበት ጥልቅ ህዝብ ጎትቶ እንዲያወጣቸው … አሁንም ያበደው ፈገገ!!
” ህዝብ ጭራ ነው” የሚሉ ታወሱት። አዎ ቀና መሪዎች፣ ህዝብ የሰየማቸው መሪዎች፣ ሲፈልግ የሚያወርዳቸው ሲሆን፣ አዎ!! ህዝብ ጭራ ነው። ይመራል። እንደውም ይነዳል። ህዝብ መርጦ ያላቆማቸው መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ገዢዎች… ሲሆኑ፣ ህዝብ ወዶና ፈቀዶ ጭራ አይሆንም። በግድ ግን ጭራቸው ይሆናል። ከጭራም ዝቅ ብሎ እትቢያ ላይ ይንከባለላል። በየጊዜው ደሙን እየገበረ ይኖራል። ይህ የኢትዮጵያ አዙሪት ነው። ” የለምንም ደም ብለው” ጀምረው፣ በደም ተጨማለቀው ኖሩና…. ከዛም ” የሰፊው ህዝብ ብሶት የወለደው” መጣ… ብሶት እነሱን ብቻ ወልዳ የመከነች አድርገው የሚቆጥሩ፣ ወይም ሌሎች ብሶት የማይሰማቸው፣ ወይም ብሶት የሚባል ነገር በነሱ ያበቃ፣ ወይም የብሶት ትርጉሙ የጠፋባቸው ሆኑና ስራቸው ለማመን አዳገተ።
ያበደው አንድ ጥግ ቁጭ አለ። የከብቶች በረት እያየ ሃሳብ ጠለፈው። የእንሦች እርሻ … ሁሉም እንሰሳቶች እኩል ናቸው…. ያበደው ሳቀ። ሳቁ የደስታ አልነበረም። ቦሰና ስለዚህ ጉዳይ በማይም አንደበቷ ጥያቄም መከራከሪያም አላት። ” ህወሃት” ትላለች። እንደውም “ወያኔዎቹ” ነው የምትላቸው። እዚህ ላይ ያበደው ጥያቄ አለው። ” ወያኔ” ሲባል የሚናደዱ አሉ። ስማቸው እንደሆነ አሁን ድረስ ግልጥ ነው። እነሱ ያልቀየሩትን ስም ማን ይቀይርላቸው? ስማቸው የነጻ አውጪ ነው። ድሮም፣ ዛሬም… እናም ወዳጆቻቸው ወያኔ ሲባሉ ለምን ያማቸዋል። ግልጽ አይደለም። ያበደው በዚህ ጉዳይ ከቱባዎቹም ጋር አውርቶ ነበር። ምላሽ የለም። እናም ሲቀይሩት ፣ በቀየሩት ስም ልንጠራቸው ቀጠሮ እንይዛለን!!
ቦሰና ”ጥፋቱ የወያኔዎች ነው” እንደሆነ ሁሌም ትናገራላች። ሁሉም ክልል በፈለገውና በወደደው ድርጅት ሊመራ ይገባል። “መመራት ምርጫ ነው” ትላለች። ቦሰና የሚጠቀሱ አባብሎች አሉዋት። ያበደው አንጎልዋን ይወደዋል። ተደላድለው ማውራት ሲጀምሩ ብዙም ሳይቆዩ አጀንዳ ይቀየራል። መረፌና ክር ነው የሚሆኑት። ሰዓት አይመርጡም። ሲነሳባት እንደ ፉከራ ነገርም ይቃጣታል። ተደስታ ታስደስታለች። ሃፍረት አታውቅም። ነጻ ናት። ወሲብን ራስዋ የፈጠረችው ነው የሚመስለው። ጠረኗ ሁሉ ይቀየራል። መዓዛዋ … ሰለሜ ሰለሜ…
ኢህአዴግ ህዝብ በተቆጣ ቁጥር ” ተሃድሶ”!! ለኢትዮጵያ በልኳ የተሰፋላት ብቸኛ ድርጅት፣ “የዘላለም ገዢ” ተብሎ ቅባት ከላይ የተደፋበት ይመስል … አቶ በረከት እንዲህ በለወ ነበር ከወራት በፊት ” የኢህአዴግ የመጨረሻ ደስታ መጥፋት ነው”!!!! ” መጥፋት?” ምን ማለት ይሆን? መጥፋት…. ወዴት? እንዴት? በምን መልኩ? እንደነማ? ያበደው ራሱን አመመው። አጋዥ ፈለገ። ወዴት ነው የሚጠፋው? ወይስ ፋና ስብሰባውን ሲቆራርጠው እንደ መረራ ንግግር የሳቸውንም ቆምጦት ይሆን?
ህም!! መጥፋት፣ መሄድ፣…. ምላሽ ያስፈልገዋል። ንግግራቸውን በሜንጫ ጀምረው ነጻ ሊያወጡ የሚነሱ ተባዮች አሉ። አንገታችንን እንደሚሉን ሚዲያ ከፍተው ባደባባይ ያሽካካሉ። መልሰው የሌሎች ትግል ደረጃ መዳቢ ሆነው ይታያሉ። ችግሩ የሁሉም ነው። ዳያስፖራ ለማንገስ አንደኛ ነው። ለመኮነንም ፈጣን ነው። ዳያስፖራ የጅግና ረሃብተኛ፣ የመረጃ ረሃብተኛ!! አገር ወዳድ ህዝቦች። ዳያስፖራ … አሁን ጊዜ የለም። ደጎልን ማናፈስ ግድ ነው። ደጎል በዙ መርጃ አለው። አይቸኩልም። አይንጣጣም። ለሁሉም ጊዜ አለው። ጊዜ ውል አለው።አንዱ አባታችን ስራውን ሲጀምር በጊዜ ነው። አንደኛ ቀን፣ ሁለተኛ ቀን…. ስድስተኛ ቀን… ከዛም በመጨረሻው ቀን አረፈ!! አዎ እሱ የጊዜ አምላክ ነው። ” ነገሮችን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው” አሜን!!
እስኪ እንረፍ። እስኪ ሰከን እንበል። የ ” ጦርነት ኮፒራይት” ውዝግብ ይቁም። እስኪ ተነጋገሩ። እስኪ ተወያዩ። ማንም ማንንም ሊያፍነው አይችልም። ዛሬ ብዙ መተንፈሻ በሮች አሉ። ጉዳያችሁን በግል ጨርሱ። በየአደባባዩ መዛለፍ ምን ይጠቀማል? ያለ ነቀፌታ ትግል የለም ያለው ማን ነው? ይቀፋል።ያሳዝናል። አገርቤት የርስ በርስ ጸብ፣ በውጪ ጸብ፣ ለሰሚው ግራ ነው። ምንድን ነው የሚያሻኩታችሁ? የአገራችን ፖለቲካ በምቧደን፣ እርስ ብርስ በማባላት ማጥ ውስጥ እስከመቼ? ለዩነት ያለ ነው። መነጋገር፣ መስማማት ካልተቻለ መቷቷውና የራስን ስራ መስራት። ህዝብ ማዥጎርጎር ምን ይጠቀማል? ኧረ ሁሉ በርጋታ ይሁን!! ያበደው የሰንበት ምክሩን ወረወረ። ቦሰና ቡናዋን ዝርግታለች። አሁን ቡና ነው። ደጎል ቡና ሲዘረጋ አይመቸውም። ትኩርት ያጣል። ቡና፣ ከቡና በሁዋላ ጨዋታ፣ ጨዋታ፣ ጨዋታ….. አንድ መሆን!! መዋሃድ፣ በቃ መሞቅ!! ቦሰና!! ሰላም እንሰንበት!!

የጀግናዋ – ምህላ ” ፈቀድኩለት – አልደፈረኝም”

… ይሸታል። ይቀረናል። ይገማል። ይቀፋል። ያስጠላል። ዛሬ ፍቅር ነገ ጸብ። ቀልብ የለውም። ውርጃ ነገር ነው። ግልቢያ ነው። እንደውም ግልብ ነው። ችግር ያለው ሁሉም ጋር ነው። “የዝንጀሮ ቆንጆ እንዲሉ” ትላለች ቦሰና። መዘላለፍ፣ መሰዳደብ፣ መካሰስ፣ መካካድ፣ አለመቻቻል፣ ተቀምጦ መነጋገር አለመቻል። ጣጣ ይዘው አደባባይ… የሚታገሉትን ገላጋይ አድርገው ጉዳቸውን ማፍረጥረጥ… እነሱ ሳይስማሙ ከሌላው ጋር… የእኛ አገር ፖለቲካ!! ያበደው ተወራጨና ከተቀመጠበት ተነሳ። ክፉ ስድብ ልቡናውን ሞላው። ወዲያው የጀግናዋ ምህላ ታወሰው።
ሰላም ለናንተ ይሁን!! በቅርቡ ሽንፈታቸውን ለተቀበሉት አፍሪካዊ መሪም ሰላም። ቦሰናና ደጎልም ሰላምታ አላቸው… ያበደው ስለ ጀግንነትና ጀግኖች አሰበ። ” አሁን ከዚህች ጀግና በላይ አለ?” ሲል ጠየቀ። ያልተነገረላቸው ጀግኖች መዘከር እንዳለባቸው አመነ። ራሳቸው ለሌሎች አሳልፈው የሚሰጡትን አሞካሸ። አዎ!! ጀግንነት ራስን ለህዝብ ማቅረብ ነው። በቃ ታምኖ መሞት!! ቦሰና ቆፍጠን ስትል ” ሞት አይቀር፤ የምን መርመጥ ነው” ትላለች።
ያበደው የሚያውቃት ጀግና 16 ዓመት ቢሞላት ነው። ጡቶቿ ገና አልበቀሉም። ሰውነቷ የጫጫ ነው። የፈዘዘ ውበት ይታይባታል። ያወቃት በድንገት አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ነው። አስተናጋጅ ነች። መጠጥ ታሻሽጣለች። ራሰዋንም ተገበያለች። ከወዲያ ወዲህ ስትል ድንገት ተለካ የመጣች እንጂ የመሸታ ቤት ሰራተኛ አትመስልም።
ፋንታ ይዛ ከያበደው ጋር ተጫወቱ። ምን መሸታ ቤት እንደወረወራት ነገረችው። ያበደው ተክዞ ይቀዳት ነበር። እየተግባቡ ሲሄዱ ልጅት አንደበቷ ተዘረጋ። ማብራሪያዋ የልብ ምታት የሚጨምር ሆነ። እንዲህ ነው ታሪኩ።
ሁለት ወንድሞች አሉዋት። የ 6 እና የ 4 ዓመት ናቸው። አባቷ የሉም። አባቷና እናቷ ተለያይተው ሳለ እሷ ከአባቷ ጋር ነበረች። ሲሞቱ ሌላኛዋ የአባቷ ሚስት / ያበደው እንጀራ እናት፣ አባት ማለት አይወድም/ አሰናበተቻት። እናም ወደ ቀደመው መንደሯ ስትመለስ ሁለት ወንድሞቿና እናቷ እንዳልሆኑ ሆነው አገኘቻቸው። እንደ እሷ አባባል መኖር አቁመው ነበር። ሚቦካ፣ ሚጋገር፣ ሚወጠወጥ፣ የለም። ሌማትና ቡሃቃ ስራ አቁመዋል። በቃ እንደ ነገሩ መሽቶ ይነጋል።
ያበደው አሁን ካለበት ሆኖ እምባ አቆረዘዘ። የውስጥ ሱሪ ከገዙ 32 ዓመት የሞላቸው እናት ትዝ አሉት። ” እንዴት ሆነው ይሁን?” … ስንቱን ማሰብ ይቻላል። መለስ መናገር ይችላሉ። ” ትልቁ ጠላታችን ድህነት ነው” ያሉት እውነት ነው። አምስተኛ ጀርባ… ያበደው ተወው። ዝምታን መረጠ። ፖለቲከኞቻችን እንዲህ ያለውን ህዝብ ነው ” ወክያለሁ” የምትሉት።….
የቤቷና የቤተሰቦቿ ኑሮ ጤና የነሳት ልጅ አቋራጭ ፈለገች። ጉለበት ስለሌላት የቤት ሰራተኛ መሆን አይቻላትም። እናም በደላላ መሸታ ቤት ገባች። ” የቤተሰቤ ጀግና ሆንኩ” ስትል ስለውሳኔዋ ማሳያ ታቀርባለች ” ስለባድመ ጦርነት ሰምተሃል” ስትል ያበደውን ጠየቀችው። አዎ !! ባድመ ደም የጠገበ ምድር ነው። ” ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በፈንጂ የታጠረውን ክልል ማለፍ ግድ ነበር። እናም ሌሎች የፈንጂ ወረዳውን አልፈው ውጊያ እንዲገጥሙ፣ ሌሎች በፈንጂው ላይ መረማመድ ነበረባቸው” አለች። ያበደው ያዳምጣል።
“እናም ሌሎች እንዲያልፉ፣ ሌሎች ፋንጂ ላይ ሮጡ፤ ህይወታቸውን ለሌሎች መንገድ ጠረጉበት። እነሱ በጠረጉት መንገድ ስራ ተጀመረ። ጠላትን መግደለና ማሸነፍ የተቻለው ከዛ በሁዋላ ነው” ቀጠለች ” እነዛ መንገድ የከፈቱት ናቸው ጀግኖች” አለችና ” እኔም የቤተሰቤ ጅግና ነኝ፣ እራሴን ለነሱ አሳልፌ እሰጣለሁ” በማለት ኤድስ የሚባለውን የፈንጂ ወረዳ ልትረማመድበት እንደወሰነች ገለጠጭች። ስትጨርስ ደረቅ ፈገግታ አሳይታ ቅንድቧን ወደላይ ሰብስባ መለሰችው።
ያበደው በሰማው ተገረመ። ለመምከር አልሞከረም። ግናባሩን በመነቅነቅ አሳማኝ ማብራሪያ ስለመስማቱ ማረጋገጫ ሰጠ። የመጀመሪያ ቀን ያጋጠማትን …. ሰውየው ሾፌር ነው። ከጀቡቲ እንደጫነ ይመጣና እሷ ያለችበት መሸታ ቤት ለማደር ይወስናል። እናም አስተዳዳሪ ያስፈልገው ነበርና ጠራት። ትልቅ ሰው ቢሆንም ሲያያት ሰውነቱ ሞቀ። የምትፈልገውን ሰጠና ተያይዘው ወደ መኝታቸው ገቡ።
ልጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንድ ጋር በእንዲህ መልኩ ማደርዋ ነበርና ፈራች። ይህንኑ ስትነግረው ይበልጥ ቀነዘረበት። አንዳንዶች እንዲህ ያለውን አጋጣሚ የድል ያህል ይቆጥሩታል። ማታብ መውሰድ ከዲግሪ በላይ ክብር መስሎ ይታያቸዋል። አንዳንድ ሴቶችም ቢሆኑ ” እሰካሁን ተሸክሜው” እያሉ ሲመጻደቁና ሰው ሲመርጡበት ጊዜ ሞቶባቸው ይስልክ እንጭት ዘመን ላይ ይደርሳሉ።
እየፈራች እየተንቀጠቀጠች ከትልቁ ሰውዬ ጋር ተኙ። እብብቱ ውስጥ አስገብቶ ሲይዛት ጥላ መሰለችው። በማይታመን ሁኔታ ተሰፈንጥሮ ተነሳና አነባ። ቁጭ ብሎ ታሪኳን ይሰማ ጀመር። ነጋ። ጠዋት አንድ ኩንታል ጤፍ፣ ትልቅ ጀሪካን ዘይትና ከሰል ከመኪናው አስወርዶ በጋሪ አስጫነላት። አንድ ሺህ በር ሰጣትና ሄደ። በቀናት ልዩነት ተመልሶ መጥቶ መላ እንደሚፈለገላት ቃል እንደገባላት… ልጅት ስለሰውየው ስታወራ ቃላት ያንሱዋታል። ደግ መሆኑንን ስትናገር ….
ከሰል፣ ጤፍ፣ ዘይት፣ ሌሎች ማጣፈጫ ገዛዝታ “ስራ ” በገባች በማግስቱ ወደ ቤቷ ሄደች። የተሰቀሉ የማብሰያ ቁሳቁሶች ወረዱ። ቤቱ ተጫጫሰ። እናት ተዋከቡ። ጤፍ ተነፋ፣ ተፈጨ፣ ቦሃቃ ሊጥ ገባበት… ወንድሞቿ ቆርሰው ጎረሱ። እስኪጠግቡ በሉ። እናት አነቡ። እሷም አነባች።…. ልጅት በፈንጂ ወረዳው ላይ ትሩጥ አትሩጥ ያበደው መረጃ የለውም። በተለያዩ አገራት በስደት ለቤተሰቦቻቸው የሚቀልጡ አሉ። ለቤተሰብ ሲሉ ራሳቸውን የረሱ አሉ። ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ እንደባከኑ የሚኖሩ አሉ። የኑሮ ግብግብ የስልክ እንጨት ዘመን ውስጥ ከቷቸው ወግ ማረጉን ሳያዩ ሌጣ ሆነው ተፈጥረው ፣ ሌጣ ሆነው የቀሩ ብዙ ናቸው። ያበደው እነዚህን ” ያልተነገረላቸው ጀግኖች” ይላቸዋል። ቴዲ አፍሮ ” ምን ይዤ ልመለስ፣ ወደ እናቴ ቤት…”
ያበደው ከሄደበት ነቃ። ያለው አንድ ማስታወቂያ ፊት ለፊት ነው። ማስታወቂያው የምርጫ ነው። “አዎ መምረጥና መመረጥ መብታችሁ ለሆነ … ” አለና ምራቁን ተፋ። ነጮቹ ይኖራሉ። እኛ በ20 ክፍለ ዘመን ገና መነጋገር አልጀመርንም። ያ – ጥቁር ሰውዬ የሚሰማው ቢያገኝ ደግ ነበር። ” መጀምሪያ እርስ በእርስ እንነጋገር” ሲል ጀምሮ ነበር። ያ-ገራችን ፖለቲካ…. !! ኢትዮጵያ ትቅደም። አቆርቋዧ ይውደም። አሁን ተሲይት ነው። የነጯ ቦሰና ጨዋታ ያስፈልጋል። ያበደው ሊከንፍ ነው። ሰዓት የለም። እዚህ መቀለድ የለም። ደጎልም ይናፍቃል። ሰላም ሁኑ፣ በየደቂቃው አዲስ ነገር አለ። አዲስ ነገር ይሁንላችሁ። ድህነትን ለማጥፋት ብንረባረብስ? ኢህአዴግም ብቻህን የድህነት አባራሪ አርበኛ እሆን ብለህ ጣጣህን ከምታይ ” እርዳታ” ጠይቅ። ብንረዳዳ ምን ይለናል? የቤተሰቦቿ ጀግና በሆነችው አንድ ፍሬ ልጅ ታሪክ ያበደው ይማጸናል። ይብቃ!! ሞትና ድህነት ላይ ወደፊት!!

የአንድ ሰዓት ትዝታ – ከሞት መልስ

የዛሬ ዓመት በዚህ ሳምንት፣ የሰማይ ኩስ ድፍን ሳር ቅጠሉ ነጭ አድርጎታል። የቅዝቃዜው መጠን አይታወቅም። ሰማይና ምድር በበረዶ ተጣብቀዋል። ፍጡራን ጭራሹኑ የሉም። ጸጥ ረጭ …. ብቻ ሰማይ እዳሪውን ያለማቋረጥ ይለቀዋል። በረዶ እንደ ባዘቶ ጥጥ በውሽንፍር ተመስሎ እየበነነ ይነሰሰነሳል። አንዳንዴም ይጋረፋል። ሲኦል ለምን በእሳት ተመሰለ ያሰኛል። በደፈናው የቅዝቃዜ እቶን ነው። ክፉ ቀን ነበር። ማስታውስ የሚቻለው ከሞት በፊት ያለውን ብቻ ነው። ኦፕላንድ ፣ ዎላ የስደተኞች መጠለያ!! ተራራ ላይ የተሞሸረ ማቀዝቀዣ!!

ሰላም ሻሎም … ያበድው ለሁሉም ሰላምታ አለው። ግን ለሰላምታ እንዲያመች በብሄር ብትደራጁ ደስተኛ ነው። በፌስ ቡክ “የነጻነት አርበኞች” ለናንተም ሰላም። ከድል በሁዋላ ቢያንስ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ” የጥቃቅን ጉዳዮች ሃላፊ ሚኒስትር” እንድታደርጉት ያበደው ከወዲሁ አደራ ይላል። “መከሩ ጥቂት ሰራተኛው ብዙ” አለ መጣፉ!! ያበደው እየተቅለሰለሱ” ሰላም ይብዛላቹህ” የሚሉትን ያልፋቸዋል። ሳኡዲን አስቦክተው ለተመለሱት፣ 20 የመዝናኛ አውሮፐላኖችን ላገቱት ሃይለማርያምም አሻም!! ያበደው ሰው ረሳ ” አብዮታዊ ይሁን ጀሃዳዊ” በውል ለማይታወቀው አዲሱ መሪ ጁሃር መሃመድ በገ ጅርቱ !! ለአርበኛ ብርሃኑም ሰላም!! ማን ቀረ?? ራሱ ፈጣሪ፣ ሁሉን ቻይ !! ከሞት ወደ ህይወት የመለሰ!! ያበደው ከጌታው ጋር የሚግባቡት በከንፈር አይደለም።3653823749_2776862a

ያበደው ባለመሞቱ ማስታወሻውን መከተብ ቻለ። እናንተዬ በረዶ ወረደ ብሎ መጨፈር ምን ማለት ይሆን? ያበደው በረዶን የሰማይ ኩስ ይለዋል። የሰማይ እዳሪ ይለዋል። እዚህ አውሮጳ ያበደው በተዛወረባቸው አገሮች  ምድር አረንጓዴ ለብሳ አይቷል። ውሃ ኩል መስሎ  ሲንጣለል አስተውሏል። ይህንን ውበት ሊያከስል በረዶ ኩስ ሆኖ ሲመጣ ጭፈራ… ያን የመሰለ እርንጓዴ ምድርና ደን አክስሎ ጸያፍ የሚያደርገውን የሰማይ ኩስ ማምለክ… ስለ አረንጓዴ ምድር ሲነሳ ያበደው ያቅለሸልሸዋል። ሳይኖረን በመዝሙር መኖራችንን ያበደው ይረግማል። ” ለምለም መስክሽ፣ ተራራሽ፣ አየርሽ፣ ሸንተረርሽ… ሲባል ያበደው ተፈጥሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ይመስለው ነበር። ያበደው ተናደደ “በመፋክርና በመዝሙር መኖር” አለና ምራቁን ተፋ። በባዶ ቂጥ ጉራ!! አገሩ አልወቀሰም። ቦሰና ” አገሪቱ ምን ታድርግ” ትላለች። እውነቷን ነው። ያ ሁሉ ወንዝ እያለ ውሃ ይጠማናል። ወንዝ የሚያስጠልፍልን መሪ አጥተን በቆሎ አሮብናል። በቀን ሶስቴ መብላት ቀርቶብን አንዴውም ቅንጦት ሆኖብናል። ረሃብ መሳቂያና ማልቀሻ አድርጎናል። ችጋር ቤቱን ገንብቶብን በሄድንበት “ረሃብተኛ” እንባላለን… ያበደው አለቀሰ። ከዚህ በሽታ ተረዳድተን እንዳንወጣ የራበው ገበሬ፣ የራበው ወንድሙን ገበሬ ጨቆነ እያልን እናላዝናለን። ኤጭ!!

ከእግዜሩ ቀጥላ ኢትዮጵያ ሁሉን ቻይ ናት። መሪዎቿና አዋቂዎቿ ሳይጨምሩላት ያላትን እየቆረጠሙ እዚህ አደረሷት። ራቁት አደረጓት። ሌሎች ከባዶ ተነስተው ሲመነጠቁ እኛ ያለንን እያወደምን እንፎክራለን። መሪ አልባ አገር። ያበደው ተቆጣ። አፉ ምራቅ አኮረፈ። አዎ እውነት ነው። መሪ የሌላት አገር። መሪ ያጣ ህዝብ። መምረጥ ያልቻለ ህዝብ። የመምረጥና የመሻር መብቱን ለዘመናት የተገፈፈ ህዝብ…. የተደፈረ ህዝብ፣ በባርነት የተያዘ ህዝብ፣ በማያውቃቸውና ባልመረጣቸው የሚመራ፣ ያበደው ጮኸ። ” ምንድን ነው የጎደለን” ሲል ጠየቀ… መልስ የሚሰጥ የለም። ከደም የምንጸዳው መቼ ይሆን?? ያበደው ጠየቀ። ደጎልን አየው። ደጎል ያበደው ሲናደድ ይገባዋል። “ ጌታው ሲናደድ “ አየና አይኑን ከፈት ዘጋ እያደረገ ጭራውን ቆላ። የለሆሳስ ድምጽ እያሰማ…

ያበደው ማስታወሻውን አየ። የዛሬ ዓመት እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር “ ሰው መኖር ያለበት አምላኩ እንዲኖር በፈጠረው ቦታ ብቻ ነው “ በዛ ቅዝቃዜ ያለ ከብርድ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ለብሶች ደርቶ ወደ ከተማ ለመውጣት ጋራ ላይ ከተተከለው መጠለያ ወረደ። አውቶቡስ ለማገኘት ቁልቁል 15 ደቂቃ ያስኬዳል። መንገዱ በረዶ ሞለቷል። ብርዱ ከታች ሽቅብ እየተነሳ ላንቃ ያደነዝዛል። አፍንጫ ያቆረዝዛል። ፊት እንደ እሳት ያቃጥላል። ጆሮ ፍጥረቱም አኞ ነገር ስለሆነ እንደ ሸክላ ይደርቃል። ጓንት ዘልቆ የሚገባው ቅዝቃዜ ጣቶችን ለይቶ ይገላቸዋል።

ያበደው ቁለቁለቱን ጨርሶ አውቶቡስ ማቆሚያ ደረሰ። አውቶቡስ የምትመጣው በየሁለት ሰዓት በመሆኑ 45 ደቂቃ መጠበቅ ግድ ነበር። መብራት አብርተው ውሽንፍራማውን በረዶ እየቀደዱ የሚሮጡ ውስን መኪናዎች ብቻ አልፎ አልፎ ውልብ ይላሉ። ከዚያ ውጪ የሚሆን ነገር አልነበረም። ሁሉም ነገር ሙት ነው። ፈጡራን ስራ ላይ ያሉ አይመስልም።  ያበደው እንቀስቃሴ አቁሞ አውቶቡስ ሲጠብቅ ቆፈኑ ቀስ እያለ ልቡን ነሳው። አይኑ ማየት ደከመው። ጣቶቹ ቀስ በቀስ እየደረቁ በድን ሆኑ። የአውቶቡሷ መምጣት የምጽአት ያህል ሆነበት። የእግሩ ጣቶች እየሞቱ ስሜት አልባ ሆኑ። ቀስ እያሉ እንቀሰቃሴ አቆሙ። ራሱን ወረረው። ምንም ነገር አስቦ የማድረግ አቅም ከዳው። ከንፈሮቹ ደርቀው መንቀሳቀስ አቁመዋል። ወገቡን ይሰማው የነበረው ስሜት ጠፋ… በየደረጃው ያበደውን በረዶ በላው። አሁን አውቶቡስ መጣች። ለመራመድ ሲሞክር አቃተው። እግሮቹ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የተጠቀጠቁበት መሰለው። የህልም ያህል ሾፌሩ ወርዶ እንደረዳው ያስታውሳል።

ከሶስት ሰዓታት በሁዋል ያበደው ሲነቃ በሚያምር ክፍል ውስጥ ነው። ክፍሉ ውስጥ የሚያስጠሉት ያበደውና ልብሶቹ ብቻ ናቸው። እንደ እንቁላል በሙቀት ያበደው ዳግም ተወለደ። በኢንኩቤተር ከሞት አፋፍ ተመልሶ ኖረ። ዛሬ በስድሰት ዓመቱ ላልሰሙ አሰማ።….. በረዶ አገራችን ቢኖር እንዴት እንሆን ነበር? በዚህ ስንፍናችን፣ በዚህ ሁዋላ ቀርነታችን፣ በዚህ ድህነታችን….. ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ሆነ። የጎዳና ተዳዳሪ ወንደሞቻችን የተባረካችሁ ናችሁ!!

ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ይህ ሆኖ ነበር። ዛሬ ያበደውና በረዶ ተላምደዋል። ብዙ ገጠመኞች አሉ። ያበደው አሁን ቦሰና ታስፈለገዋለች። ኪኒኑ ናት። ቦሰና ፍቅር ናት። ሲነሳባት ኤሌክትሪክ ናት። ነዝራ ታስነዝራለች። “አከሲ” ካለች አለቀ። ያበደው ፈገግ አለ። ከሞት ያመለጠበትን ቀን ሊቀልድበት ወስኗል። አከሲ!!የሰላሌ ቆንጆ!! ሰላም እንሰንብት!! መላካም ሰንበት!! ነገ ብቻ ሳይሆን ከሰኮንዶችና ደቂቃዎች በሁዋላም ብዙ ሌላ ነገሮች አሉ። ይኖራሉ… ሰው በተፈጠረበት ይኑር!! አበቃሁ… ለዛሬ!!

ቻርተር፣ የሽግግር ጊዜ፣ የሽግግር መንግስት፣ አገርህን አድን፣ ውህደት፣ ፍቺ፣ ቀለበት፣ ምህላ፣ የርስ በርስ ትርምስ..

የሰንበት ወግ

…አድማ፣ ባድመ፣ አኬልዳማ፣ ውሃ ማቆር፣ ወደፊት ፣ ወደ ሁዋላ፣ ግብርና መር፣ ውጤት ተኮር፣ ግምገማ፣ ውስወሳ፣ ጥርነፋ፣ ጎጥ፣ ማተራመስ፣ ማደናበር፣ ቆረጣ፣ አርበኛ፣ ማዕበል፣ ታሪክ ሰሪ፣ ታሪክ አዳሽ፣ አሸባሪ፣ ተሸባሪ፣ አቀነባባሪ፣ ያለምንም ደም..፣ተነሳ ተራ.መድ፣ ቦንድ፣ ግንድ፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣መታደስ፣ ጥልቅ ተሃድሶ… ……….ተጋድሎ፣ ስድብ፣ አብዮት፣ አክቲቪስት፣ ነፍጠኛ፣ ጠባብ፣ … .ያበደው መፈክር ጠሩ ነው…

ያበደው መናገር የሚፈልገው የህይወቱን ስንጣሪ ነው። ያበደው ለምን እንዳበደ ለሚጠይቁት ምንም መልስ የለውም። ያበደበትን ምክንያትም አያውቀውም። ግን አብዷል። በማበዱ አያዝንም። ደስተኛ ነው። ስለማበዱ ከንፈር የሚመጡለትን አጥብቆ ይጠላል። ጤነኞች ስለማይመስሉት!! እብድ አሰዳቢዎችን ይረግማል። አማኑኤል ሆስፒታል እየኖሩ “ከሚቀለቡት” እብዶች መካከል አብዛኞቹ የብሄር ፖለቲካ መጋኛ የመታቸው ናቸው ብሎ ስለሚያምን አያከብራቸውም። ሩቅ ሆነው በብሄር ቫይረስ የተነደፉት ይጸየፋቸዋል። ደም ዘሪዎች፣ የአገርና የትውልድ ውርጃዎች ይላቸዋል።

ያበደው አኗኗሪና አጋር የሚላት የትዳር ጓደኛ አለችው። ትዳር በመፈቃቀድ እየተካፈሉ መኖር እንጂ ውስብስብ ግንኙነት ስላልሆነ ማካበድ አይወድም። ፍቅርም ቢሆን ሰዎች ሲፈጠሩ የተሰጣቸው ነጻ ስጦታ እንጂ የራሳቸው ግኝት አይደለም ብሎ ያምናል። “ሰው”እነሱ አልጠቀምበት ሲሉ ተኖ የሚያልቅ በረከት እንጂ ታግለው የሚጎናጸፉት ባለመሆኑ ለማፍቀር ታምኖ መኖር በቂ ነው ባይ ነው። ብዙ ውዝግብ አይወድም። ሰው የፈለገውን ለመሆን ፈቃድ ሊጠይቅ አይገባውም ከሚሉት ወገን ነው። እንደውም የሰው ልጆችን ፍላጎት የሚገቱ ህጎች “እንዲወድሙ”ይመኛል። የአኗኗሪው ስም ቦሰና ይባላል። ቦሰናን ሲያስተዋውቅ “አኗኗሪዋ ነኝ” በማለት ነው። በቃ!!ቦሰና ጠባብ፣ አክራሪ፣ ዘር፣ ጎሳ፣… አታውቅም። ጽድት ያለች የፍቅር ምሶሶ ናት። ፍቅር ስትሰጥም ሃይለኛ ናት። ነገር አለሙን ታስረሳለች።

ደጎል ውሻው ነው። ያበደውና ደጎል ከፍቅራቸው የተነሳ በጥቅሻ ይግባባሉ። ደጎል ህልሙን ሳይቀር ልክ እንደሰው ይተርክለታል።ለፍቺው ቦሰና ትቀርባለች። ደጎል አሜሪካን ኤምባሲን ተቆጣጥሮ ስለሰራው ጀብድ ያጫወተውን ያበደው አይረሳውም። ለሊቱን ሙሉ ውሾች ስሪያ ሲያድሩ እሱ አሜሪካን ኤንባሲን ተቆጣጠሮ ነበር። ጊዜውን ጠብቆ ይተርካዋል። በነገራችን ላይ ስሪያ በየቦታው ነው። በውድቅት ለሊት መንገድ ላይ መገበያየት እዚህም አለ። እዚህ የሰለጠኑት አገር ውስጥ ወገን ወገኑን ይገበያያል። ያበደው መስመር ሳተ። ቸኮለ።

ያበደው በህይወት ዘመኑ ሊመለከታት የማይወዳት እንስሳ ድመት ነች። ያበደው ድመት አይወድም። ድመት ሲመለከት ቆዳው ይቆማል። ሰውነቱን ይወረዋል። አፉን ምራቅ ይሞላውና ሽቅብ፣ ሽቅብ ይለዋል። እድሜ ለጊዜ አሁን ግን ድመትን መሸሸ የማይችልበት ቦታ ነው። በጀት የሚመደብላቸው ድመቶች ከነሙሉ መብታቸው ይቀልዱበታል። ሊተሻሹት የሞክርሉ። ጉድ ነው !!ኑሮን እንደ ወረደ ሲቀበሉት የሚጠሉትን ባይወዱም መወደድ ግድ ነው። ለነገሩ የእኛ አገር ፓለቲከኞችም እንዲሁ ናቸው። ያልሆኑትን፣ ያላደረጉትን፣ እየቀባጠሩ ” ውደዱን” ይላሉ። በተቃዋሚ ” አውራ ፓርቲ” አመራሮች ዘንድ ያለው ይብሳል መሰለኝ። ለጊዜው ያበደው ዳታ ስላልሰበሰበ በዚህ ጉዳይ አይከራከርም። ግን ሕዝብ በውስጥና በውጭ አምባገነኖች መወጠሩን ያለጥርጥር ያምናል። ሞጋች ካለ አይፈራም።

ድሬደዋ 1985 ዓ ም ከጠዋቱ 5 ሰአት ግድም የአንድ ሰው መኖሪያ ቤት በሰዎች ተከቦ ይታያል። ያበደው ስለሁኔታው ለማወቅ ተጠጋ። ቤቱ ተሰብሮ ሲገባ የቤቱ ባለቤት ህይወቱ በራ ወደ መጣችበት ተመልሳ ኖሮ በድን ሆኗል። ወ/ሮ ስርጉት እያለቀሱ ይራገሙ ጀመር።ያበደው ርግማኑን ካየው ጉድ ጋር አዋህዶ ድመት ጠላ። ነገሩ እንዲህ ነው።

ሟች በመጠጥ የተለከፈ ነበር። ዘወትር ይጋታል፤ ይሰክራል። ሰክሮ እየተንገዳገደም ለድመቱ ስጋ ሳይዝ ቤቱ ገብቶ አያውቅም። አራት ልጆች ያፈራቸው ድመት እንደወትሮው ስጋ ተገዝቶላት ማታ ራቷን ከልጆቿ ጋር በልታለች። ምስክርም አለ። በቅምጥል ስለመኖሯ ጎረቤቶች ሲያሙ “አይጦቹ የሚደበቁት እሱ ቤት ነው። የሱ ድመት እንደሆነ ያለ ስጋ አትነካም። አይጥ ትጠየፋለች። ይሄ ሰካራም ሚስቱ ያደረጋት ይመስላል..”እያሉ ነው። እኛ እኮ ለማማት የተፈጠርን እኮ ነው የምንመስለው። “ሚስቱ ያደረጋት ይመስል”እያሉ በድመትም ያሙታል።……..እንደዚህ በንክብካቤ የተያዘች ድመት ማታ ቤቱ የደንቡን ይዞ ገብቶ እንደተኛ ያሸለበውን አሳዳሪዋን አጅሪት ከግልገሎቿ ጋር በመሆን ነግቶ በሩ እስኪከፈት ድረስ ሰፈረችበት። ከጆሮው ጀምረው ይከረክሙት ጀመር……

ያበደው ሌላም ታሪክ ያውቃል። ድመት ወልዳ ትበላለች። ወልደው የሚበሉ ሰዎችም አሉ። ወልዶ መጣል፣ ሳይወልድ ማስገደል፣ በሌሎች ቤተሰቦች ላይ ፈርደው ልጆችን የሚያሰቃዩ… ያበደው አመመው። በሆዱ ተራገመ። ፍርድን ጠየቀባቸው። ወደ ድመቲቱ / የወለደችውን አምጣ እንዳበቃች ትሰለቅጣለች። ለመብላት እየጎመጀች ታምጣለች። ያበላት ላይ ተንጠልጥላ ቆዳ ትገፋለች። ያበደው ድመት የሚጠየፈው ወዶ አይደለም። ሰው እንዴት ከድመት ጋር ህብረት ይኖረዋል? ብሎ ይጠይቃል። ለዓመታት ድመት ሲሸሽ ኖሮ ቤቱ ገባች፤ ሳይወድ በግዱ “ፒስ” ሲል ሰየማት። አወሮፓ!! ዶሮ ማነቂያ አቶ ኩማ ድሪባ ቢሮ ፊት ለፊት በሚኖርበት ወዶ ገብ ቤቱ አይጥ ተጨማሪ የኑሮ ሁከት ሆነበት ሰላሙን በድመት ያገኘውን ጓደኛውን አሰበና የድመትን ውለታ የሚቆጥሩ ታወሱት። የሚበላው ያጣ ድመት እንኳን አይጥ የራሱን ልጅ ይበላ የለ!!

ያበደው ወዶ ገብ ስለሆነበት ቤቱ ብዙ ታሪክ ለማውጋት ቃል ይገባል። በድመት አምሳያ የተፈጠሩ አውሬዎች እንዳሉ ያውቃል።ያበላቸውን የሚቧጥጡ፣ ያሳደገቻቸውን አገር የሚቆራርሱ፣ እናታቸውን መልሰው የሚበሉ፣ የሚገፉ፣ የሚያዋርዱ፣ የልጅ ልጆቻቸውን አልመው የሚቀነድቡ፣ የሚዘርፉ….”የናት አገራቸው የእንግዴ ልጆች…”

ሳትማር የተማረችው ቦሰና ማብራሪያዋ መሬት ጠብ አይልም። አዕምሮዋ ይመትራል። “በመሃይም አንደበቴ” እያለች ፖለቲካውን ትበልታለች። ፖለቲከኞችን ” ጅቦች” ትላቸዋልች። አዎ ትውልድን ከሚበሉ የዘመኑ ጅቦች ጋር እየተኖረ ነው። ያበደው ፍልስፍና ጀመረ። አዎ ጅቦች አለ። ጅብ እንኳን … ያበደው ሊያውዳድር አስቦ ተወው። “ተንስ፣ ተነስ፣…” ቀረርቶ፣ ባዶ.… ባዶ ተስፋ። ቻርተር፣ የሽግግር ጊዜ፣ የሽግግር መንግስት፣ አገርህን አድን፣ ውህደት፣ ፍቺ፣ ቀለበት፣ ምህላ፣ የርስ በርስ ትርምስ… ያበደው ቆሽቱ ሸተተው… በሌለ ነገር መባላት!!

ያበደው ግሩፕና የቡድን ፍረጃ አጥብቆ ይጠላል። አድማ፣ ባድመ፣ አኬልዳማ፣ ውሃ ማቆር፣ ወደፊት ፣ ወደ ሁዋላ፣ ግብርና መር፣ ውጤት ተኮር፣ ግምገማ፣ ውስወሳ፣ ጥርነፋ፣ ጎጥ፣ ማተራመስ፣ ማደናበር፣ ቆረጣ፣ አርበኛ፣ ማዕበል፣ ታሪክ ሰሪ፣ ታሪክ አዳሽ፣ አሸባሪ፣ ተሸባሪ፣ አቀነባባሪ፣ ያለምንም ደም..፣ተነሳ ተራ.መድ፣ ቦንድ፣ ግንድ፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣መታደስ፣ ጥልቅ ተሃድሶ… ………..ያበደው መፈክር ጠሩ ነው። ለትውውቅ ያህል ነው። ሰላም ሁኑ! ሰላም ክረሙ! ሰላም፣ ሻሎም፣ ሰናይ ሳምንት። ያበደው በሳምንት እሁድ የእሁድ ወግ ያቀርባል። እሁድን ከ-ያበደው ጋር

ህልም እልም ድሮ ቀረ

የህትመት ቅድመ ምርመራ ጉዳይ ሲገርመን፣ ሰካይፒና ያሆ በመጠቀም መነጋገር  ያስቀጣል የሚል ህግ ተከተለ፣ ብዙ ህጎች አሉ። ወደፊት የሚጨመሩም አሉ። የወጡ ህጎች የሚመለከቱዋቸውና የማይመለከቱዋቸው ተፈጥረዋል። ልዩነቱ በኑሮ ብቻ አይደለም። ህግ የበላይ የሚሆንባቸውና ህግ የሚሰግድላቸው መኖራቸው ነው። ልማታዊው መንግስታችን ይህንን ቢያስብበት መልካም ነው። የህግ የበላይነት ጥያቄ በየቦታው አለ። ያበደው ያልተከለከሉ ጉዳዮችን አሰላ። “የቀረውና የተፈራው ህልም ማየትና ህልም መፍታት እንዳይከለከል ነው” በማለት አንድ ወዳጁ የነገረው ታወሰው።    አዎ! ማን ያውቃል  ፀሃዩ መንግስታችን ለማለም መደራጀትን እንደ ግዳጅ፣ መጠርነፍን እንደ አማራጭ ሊያውጅ ይችላል። ያበደው ባሰበውና ባሳሰበው ጉዳይ ከት ብሎ ሳቀ። እውነት ነው ማን ያውቃል? እኒህ ባለ ሚጢጢ አይኖች ህልም የሚያሳብቀውን ጅኒም ይሰሩት ይሆናል። ያበደው ቦሰና ሰለነሱ የምትናገረው ትዝ አለው። ግድግዳ በስታ ምናምን ስትቸረችር  ዱቤ ይወስዱ ነበር። አንዱ በተለይ ወዳጇ ነበር። እዳው ሲበዛና ተጨማሪ ሲጠይቃትና ስትከለክለው  በቻይንኛ አማርኛ ” ማያምን” እያለ ይምል  ነበር ። እነሱ ሲያውቁን፣ እኛ ተረሳሳን!! የኑሮ ውድነት ቅዠት ውስጥ የጣላቸውን ቤት ይቁጠራቸው። መንገድ ላይ ቆመው የሚያልሙ ለቁጥር ይታክታሉ።ጤነኞችም በሽተኞችም አላሚዎች ሆነዋል። የረሃብ ህልም ቅጥ የለውም። ከዚህም ከዚያም የህልም ፈቺ ችግር አለ። አቶ መለስ ጥሩ ጥሩ ህልም ተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል። እሳቸው ሁሉንም ነገር ህልም  በህልም ስላደረጉት ህልም እንደማያዩ ያበደው በሹክታ ሰምቷል።

በወታደራዊው መንግስት ወቅት ያየትን ህልምና ገራፊ እያዩ ዛሬ ድረስ የሚደነብሩ አሉ። ያኔ በዱላ ብዛት በግድ ህልም ይታይ ነበር አሉ። አንድ የሀደሬ ሰፈር ነዋሪ በዛን ዘመን ስለገጠመው የእስር ቤት ታሪክ ሲያወጋ፣ ቦሰና አለቀሰች። ነጠላዋን እየበላች “ አይ ጊዜ ” አለች። “ታንክ ጓሮ ቀብረናል” ብሎ ጀጎልን ያስቆፈረ ነበር። ያበደው ባለቤቱ ቦሰናን “አትነፍርቂ” ብሎ መቆጣቱን ያስታውሳል።  እንግዲህ ድሮም ዛሬም አሳላሚና አላሚዎች አሉ። ቅብብሎሽ መሆኑ ነው። ለድጋፍም ይታለማል፣ ለተቃውሞም ይታለማል። አገር በሪፖርት፣ በህግ ብዛትና በህልም ቀደመች። የኢትዮጵያንና የወደፊቱን ትውልድ ህልም  መፍታት የሚችሉ ማፈላለግ ግድ ነው። አስተካክሎ የሚፈታ !!

አማኑኤል ሆስፒታልም ሆነው የሚያልሙ አሉ። ያበደው መረጃ ባያሰባስብም የእብዶች ህልም ፍቺ እንደሌለው ሰምቷል። እብዶች የሚፈልጉትን ባደባባይ ስለሚናገሩ ህልምና ህልም ተረጓሚ አይፈልጉም። ሲነጋም ቢሆን ትዝ አይላቸውም። የተጣሉት በውን ከሚያዩት ዓለም ጋር በመሆኑ ከማያውቁት ዓለም ስሜት ጋር ግብ ግብ አይገቡም። ያበደው የረሳቸው ብዙ ጉዳዮች ታወሱት። አንድ ጊዜ ህልም ይሁን ቀልድ ባይታወቅም እንዲህ ሆኗል፤

አንድ እብዶች የሚታከሙበት ቦታ ነበር አሉ። መታከሚያው በረጅም ግምብ ዙሪያው ታጥሯል። እዚሁ ቦታ ለህክምና የሄደ አንድ ሰው ክልሉ ውስጥ እንደገባ ጫጫታ ይሰማል። ጫጫታው ድምጹ እንጂ ከየት ሆነው እነማን እንደሚንጫጩ ለማየት አጥሩ ይከለክላል። ታካሚው ድምፁን ለመስማት ተረጋጋ። ጆሮውን አሾለ። አዳመጠ። አስራ ሶስት፣ አስራ ሶስት፣ አስራ ሶስት…. እያሉ ነበር የሚጮሁት። የእብድ ቀልድ !!

ግራ የተጋባው ታካሚ፣ “ አስራ ሶስት፣ አስራ ሶስት…” እያሉ የሚጮሁትን ለመመልከት ዙሪያውን ሲማትር ቆይቶ አንድ ሽንቁር ቀዳዳ አገኘ። አጮልቆ ባንድ አይኑ በሽንቁሩ ሲመለከት ጩኸቱ ተቀየረ። “ አስራ አራት፣አስራ አራት፣አስራ አራት…” እያሉ መጮህ ጀመሩ !! አሰራ  አምስት፣ አስራ ስድስት፣ …………. ሃያ፣ ሃያ አንድ፣ ሃያ…… ሃምሳ ?  እንዲህ ያለ ነገር ህልም ባይሆንስ? አይን እያጠፉ እንደ ቅርጫት ኳስ ጎል ማሽካካት፤

ሰው በውኑ፣ እያወቀ፣ ሳይተኛ፣ ሳይታመም፣ በማያውቀው ጉዳይ ገብቶ ይፈርዳል። በማያውቀው ጉዳይ ይመሰክራል። ፍጹም መረጃ በሌለው ጉዳይ ሌላውን ይቀባል። ምንም ነገር መሆን ያንድ ሰው መብትና ፍላጎት እንደሆነ የሚዘነጉ አሉ። በእንደዚህ አይነቱ መንገድ  “ አይናቸው የተደነቆለ ” ለማን አቤት ይላሉ? ያበደው ጠየቀ ? መልስ ማግኘት ባይችልም ድርጊቱ አስገረመው።  የሰለጠነ ምድር ላይ በዚህ መሰል ችግር የተጠመዱ ካሉ ያሳዝናሉ።

 አዎ!! ብዙ ሊያቀራርቡና ሊያላልሱ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ። ግን እንዴት ተደርጎ? መለስና ፓርቲያቸው በሚወቀሱበት ጉዳይ ሳናስበው ተዋናይ የሆን አለን። የፖለቲካ ጨዋታ ዋና አላማ ደጋፊ ማብዛት ሳይሆን ደጋፊ መቀነስ ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል። በስድብና በቀድሞ አስተሳሰብ የሚሮጡ አሉ። እጃቸው የገባውን እየገፈተሩ አዲስ የሚናፍቁ አይታጡም። የበረገጉትን የሚሰበስብ ሲመጣ አስቀድሞ “ እገሌ ማን ነው ” ሚል ህልም ቢጤ ይደረስለታል። አዲስ ሃሳብ ብቅ ሲል እድል አይሰጠውም። እድል ታላቅ ነገር ነው። አለመታደል መረገም ነው። የታደላችሁ አመስግኑ!! ያበደው በታደሉ ይቀናል።

አጠገባችን፣ እጎናችን፣ እጉያችን፣ ያልተጠኑ፣ ያልተጎበኙ፣ ያልተዳሰሱ፣ ያልተዘከሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ። የካምፕ ህይወት!! ስደት ራሱ፣ አገር አልባ መሆን፣ ማንነትን፣ ባህልን፣ ወግን፣ ወገንን፣ እናትን፣ ልጅን፣ አባትን፣ ጓደኛን ማጣት፣ አብሮ አደግን መክሰር፣ ያበደው እንባው ቀረረ። “ ሰው በቂጣ ብቻ አይኖርም ” ያለው ጌታ ታወሰው። ” አንተን አስፈቅጄ ባልሰደድም እኔንና ወገኖቼን እርዳን። ምድራችንን  …… ” ያበደው ፀሎቱን አቋረጠ። ብዙ ጉድለት። ጎዶሎ ህይወት። ይህ ሁሉ ሳያንስ አለመስማማት። እንደ ሸቀጥ መመዳደብ!! የበሰለ እያለ ለቃሪያው መሻማት፣ መቧቀስ፣….

ብዙ አይነት ህልሞች አሉ። የውን ህልም ምኞት ነው። የፈጠራ ህልም ድርሰት ነው። የወግ ህልም ትዕቢት ነው። ቦሰና የምታየው አይነት የየዋሆች ህልም አለ። የካፌ ቤት ህልም አድማ ነው። ሁሉም ህልም ክፋት የለውም። ማለም መብት ነው። ለራስ ብቻ መቃዠት አይጎዳም። የቅዠትም  መብት መገፈፍ የለበትም። የተሳሳተ ፍቺ ግን አደጋ አለው። ስቶ ያስታል። ያበደው ስለህልም የሰማውን መልሶ እየለፈለፈ ….. ድንገት  ትዝ ሲለው ባለበት አገር መጮህ ክልክል ነው። ስርዓት ጠብቆ መናገር ግን ይቻላል። ስርዓት የማይጠብቁትንም  ህግ ፊት ማቅረብ ቀላል መሆኑ ታወሰው።

በህልም፣ በተስፋ፣ በጉራ፣ በአማላጅነትነት፣ በሰብአዊነት ….. ቆረጣ የሚጫወቱ አሉ። የቆረጣ ነገር ለሚገባቸው ይገባቸዋል። ስካይፒ ኢኮኖሚ ይጎዳል ሲባል ቆረጣ ነው። መረጃ መቀባበልን በህግ ለመዝጋት የተፈጠረ ድርስት ይመስላል። አገራችን በአፋኝ ህጎች እየመራች ነው። ብቻ ላስተዋለ ምልክቱ የመወጣጠር ነው። ከዚያም ከዚህም ውጥረት አይሏል። የአራት ኪሎ  አጉሟል። የአውሮፓን ክረምት መስሏል።

ይህንን አደርጋለሁ፣ ይህንን አደርግልሻለሁ፣ ይህንን እናደርጋለን፣ ይህንን ያደርጉላችሁዋል፣ … ወዘተ በማለት የማይጨበጥ፣ እንደ ጉም የሚተን ተስፋ ከዚህም ከዚያም ይሰማል። ቀናነት ራሱ ህልም ሆኗል። በቀናነት የማይሆን ነገር ይሰብራል። የቁም ህልም ክፉ ነው። እንዲህ ያለ ህልም በዝቷል። እንዲህ እደረጋለሁ፣ እናደረጋለን ማለት ብቻውን አልሰራም። ህልም ነው። እንደውም ቅዠት ነው። ቅዠት ገለባ ነገር ነው። ከሃያ ዓመትና ከሃያ ዐመት በፊት በህልም ኖርን። መንግስቱ ስለ ዳቦ ቅርጫት፣ መለስ ስለ ሶስቴ መብላት  አስረግጠው የነገሩን ህልም ነው። ከህልም ስንነቃ “ዋይ ዋይ”  እያልን ነው። ቅንጅት መንፈስ ነበር……መንፈስ ሆኖ ሆኖ  በብልጠትና በስርዓቱ  ርኩስነት ….. ያበደው “ህዝብ ምን ተጠቀመ” ሲል ጠየቀ። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው!! ያበደው ዘለለ። የሰማቸውንና ያያቸውን ዋቢዎቹን አሰበ።

የራሳቸውን ህልም የሚፈቱ አሉ። ለነዚህ ሰዎች “ህልም እንደፈቺው ነው” የሚለው ተረት አይገባቸውም። ለራሳቸው ያልማሉ። ለራሳቸው  ይፈታሉ። “ህልም እልም” ሲሉ አይሰማም። ስላለሙትና ስለፍቺው ለሌሎች ሲናገሩ ፍፁም አዋቂ ሆነው ነው። “ይመስለኛልን” ሰምተው “ይመስለኛል” እያሉ ህልምን በህልም ሲፈቱ የኩራትና የመጀነን ስሜት ይታይባቸዋል። ያበደው ህልምና ፊልም አዘውትሮ ያየው፣ የራሳቸውን ህልም የሚፈቱትን በተመስጦ ለማዳመጥ እድል ያገኘው ሙታክ ውስጥ ነው። ሙታክ የስደተኞች መኖሪያ ካምፕ!! ያበደው አጥወለወለው  ለሙታክ ነዋሪዎች መፍትሄ የሚፈለገው እንዴት ነው?  ሰማዩና ምድሩ የዞረባቸው ምርጥ ምርጥ ልጆች አሉ። ዝም ብለው ውለው፣ ዝም ብለው የሚያድሩ አሉ። ሰው መሸሽ የጀመሩ አሉ። ከዚያም የባሰባቸው ….. እናስ ? አይ ስደት ኩራት? አይ ተሰዶ ትልቅነት? ሰው ብንሆን ከዚህ በላይ ሊያፋቅር የሚችል ምን ይኖራል? ያበደው ያላቸውን የሚያካፍሉ፣ በስጋም በነብስም የሚያረጥቡትን፣ ስራዬ ብለው ወገኖቻቸውን የሚያስቡትን፣ ለተቸገሩ በረው ከተፍ የሚሉትን….. ምርጦች አስታወሰ። ምርጦች በየፈርጁ አሉ። አለም ዥጉርጉር ነች።  ሁሉን አግበስብሳ ትበራለች።

ሙታክ!! ውበት የለቀቀባቸው፣ ውልውል ብለው የሚያብረቀርቁ ማገዶ የማይፈጁ ያሉበትን ያህል፣ እንደ አቦል ቡና ቀደም ቀደም የሚሉትን፣ በብርሃን ፍጥነት ካልበረርን የሚሉትን፣ ቀልጣፋ ነኝ …. የሚሉትን አርግቦ ስም የሚያስለውጥ ገዳም ነው። ኢዮቦች!! ሙታክ ውስጥ ቀኑን በለሊት ተክተው፣ በለሊት እየቆሙ፣ በቀን የሚተኙ ብዙ ናቸው። በተለይ ብዙ የቆዩት ….. ያበደው ማስታወሻውን ከፈተ። ቀንና ለሊትን አደባልቀው ከሚኖሩ ከየአቅጣጫው የሰበሰበውን ተመለከተ። የሌላውን ዓለም  ነዋሪዎችን ህልም በይደር አስቀመጠው። ቦሰና ዛሬ ድረስ “ ህልም እልም ” ትላለች። ህልም እልም ባትልም ህልም ራሱ እልም እንደሚል ቢነገራትም ሊገባት አልቻለም። ዛሬም “አናሎግ” ነች። ያበደው ደክሞታል። አሁን ማረፍ አለበት ሲነጋ ሰንበት  ነው። በሰንበት ዋናው ፋጣሪም እረፉ ብሏል። እንረፍ፤ ቢያንስ ከቀኑ ክፋት እናመልጣለን!! “ብሄር ብሄሮችን ያማከለ አንድነት ይስጠን ” የዘመኑ ለማኞች ምርቃት ነው። የሚሰጣቸውን ስለሚያውቁ ሰጢውን ማስደሰት ግድ ይላል። ሲርብ ችግር ነው። ግን እኮ እውነት ነው። የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ የታተመበት ጉዳይ ነው። በብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ ህልም እልም ብሎ ነገር እቃ እቃ የመጫወት ያህል ነው። ለምሳሌ ኦሮሞዎች ብዙ ናቸው። በህልም መሆኑ ቀርቶ በውናቸው አስተዳዳሪ ቢሆኑ ጸብ የለም። ቀጥሎ አማራ ነው። ቀጣዩ ….. ተወደደም ተጠላም እውነቱ ይህ ነው። ይህንን ያልተቀበሉ ከዘላለም እንቅልፍ አልነቁም። መለስም ላይጨርሱ ጀምረው ያንጠለተሉት ጉዳይ  ነውና!! ያበደው  የሚያውቃቸው የአዲሱ አንድነት ኬሚስትሪ ያልገባቸው ብዙ ናቸው። ህልም እልም ይሏል ይሄ ነው። ሰላም !!

ማሳሰቢያ- ቀደም ሲል ከጻፈኩት ለማላመጃ የመረጥኩት